ፈልግ

የ2015 ዓ.ም. የዓለም ወጣቶች ቀን ፥ በሊዝበን የ2015 ዓ.ም. የዓለም ወጣቶች ቀን ፥ በሊዝበን  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

የዓለም ወጣቶች ቀን የሊዝበን ጎዳናዎችን የዓለም ጎዳናዎች ሆነው እንዲሰነብቱ አድርጎ ነበር ተባለ

በሊዝበን የምትገኘው የቫቲካን ዜና ዘጋቢ የሆነችው ፍራንሲስካ ሜርሎ ዘንድሮ የተከበረውን የዓለም ወጣቶች ቀን አከባበርን እንዲሁም ወደፊት ዬት እና ምን ክብረበዓላት እንደሚከበሩ ዳሰሳ አድርጋለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ፍራንሲስካ እንደምትለው የዓለም ወጣቶች ቀን ሲጠናቀቅ አንዱ ምዕራፍ አብቅቶ ሊሆን ይችላል ፥ ነገር ግን ያለፉትን ስድስት ቀናት ሊዝበን ከተማ ያሳለፉት ወጣት መንፈሳዊ ነጋዲያን ትውስታቸውን በደማቁ ለመጻፍ እና ለማስታወሻነት ብዙ ቁሳቁሶችን ይዘው ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል። በአዲስ የተስፋ ስሜት፣ በጠንካራ እምነት እና በህይወት ዘመናቸው ከነሱ ጋር የሚኖር ትዝታ ይዘው ጉዞ ወደ ቤታቸው ጀምረዋል።
እንደነዚህ ዓይነት ልዩ ክብረ በዓላት ፍጻሜያቸው ብዙውን ጊዜ ቶሎ በመድረሱ የሚያሳዝኑ ሊሆኑ ይችላሉ ፥ ነገር ግን ሁሉም መልካም ነገሮች የሆነ ቦታ ላይ ማብቃት አለባቸው። የዘንድሮው የዓለም ወጣቶች ቀን በእውነቱ “ጥሩ” ነበር። በመልካምነቱ ምንም ጥርጣሬዎች በጭራሽ አልነበሩም። የሃምሌ የመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ የሊዝበን ጎዳናዎች ደማቅ ሆነው ነበር የሰነበቱት ፥ በፍጹም አሰልቺ ጊዜ አልነበሩም። ሃምሌ 27 2015 ዓ.ም. ዕለተ ሐሙስ ላይ መንፈሳዊ ነጋዲያኑ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በኤድዋርድ ሰባተኛ ፓርክ በደማቅ ሁኔታ አቀባበል ሲያደርጉላቸው ነው ውሃውን ለመጀመሪያ ጊዜ የቀመሱት።

ፍቅር እና ተስፋ

በእነዚህ ቀናት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ካስተላለፏቸው መልእክቶች መሃል ‘ፍቅር እና ተስፋ’ የሚሉት ዋነኞቹ አንኳር መልዕክቶች ነበሩ። ወጣቶቹ መንፈሳዊ ነጋዲያን እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ ፣ በዚህች ዓለም ፈተና ሲደክሙ እርስ በርሳቸው እንዲረዳዱ ፣ ከተስፋ መቁረጥ መውጣትን ፈጽሞ እንዳያቆሙ እና በአዲስ ጅማሬ ተነስተው የሕይወትን ጉዞ እንዲቀላቀሉ መክረዋቸዋል። ይህም በቤተክርስቲያኒቷ ውስጥ ለእያንዳንዱ ሰው በቂ ቦታ እንዳለ ሁላችንንም አስታውሷል። 800,000 መንፈሳዊ ነጋዲያን በተገኙበት ባለፈው አርብ ዕለት ከሠዓት በተደረገው የመስቀል መንገድ ጸሎት ላይ ብጹዕነታቸው "ሁሉም ሰው፣ ሁሉም ሰው፣ ሁሉም ሰው" በማለት ወጣቶቹ ቃሉን ደግመው እንዲያስተጋቡ አድርገዋል። ይህ አጽናኝ አባባል የመጣው የተለያዩ የዓለም ክፍላትን የሚወክሉ ወጣቶች በተገናኙበት ወቅት ነው። በዓለም ወጣቶች ቀን ላይ ከተሳተፉት አብዛኛዎቹ አስከፊ ጦርነት ከሚካሄድባቸው፣ ከድህነት፣ ከረሃብ፣ ከአየር ንብረት አደጋዎች እንዲሁም ከተለያዩ የሁከት እና ግጭቶች እውነታዎች በየቀኑ ከተጋረጡባቸው ስፍራዎች የመጡ ሲሆኑ ፥ በሌላ መልኩ ሌሎቹ ደግሞ አንፃራዊ ሠላም ካሉባቸው ቦታዎች የመጡ ናቸው። በሊዝበን እነዚህ ሁለቱ ዓለማት ናቸው የተገናኙትና አንድ የሆኑት። በወጣትነት እድሜህ ላይ ሆነህ ካንተ በባህልም ሆነ በአኗኗር ዘይቤ ፣ በአለባበስ ፣ በአነጋገር ፣ በአመጋገብ እና በአስተሳሰብ በእጅጉኑ ከሚለይ ሰው ጋር ተገናኝተህ እና በፍቅር አንድ ላይ ሆነህ ማሳለፍን የመሰለ እጅግ ጠቃሚ ልምድ ከዬትም አይገኝም። ይህ አዲስ የተመሰረተው ጓደኝነት ብዙዎቹን ወጣት መንፈሳዊ ነጋዲያን በእነዚህ ሰፊ ልዩነቶች መካከል ምንም ልዩነት እንደሌለ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል።

የዓለም ጎዳናዎች

የሊዝበን ጎዳናዎች የዓለም ጎዳናዎች ሆነው በሰነበቱበት በዚህ ጊዜ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጎዳናዎቹ ላይ አንድነትን አመጡ። 800,000 ወጣቶች በዝምታ ተቀምጠው እንባ እያፈሰሱ ፥ “በእርግጥ ብጹእነታቸው እኔን በቀጥታ እየተናገሩኝ ነው” የሚለውን ስሜት ይገልፃሉ ፤ ይህ በእርግጥም የተከሰተ ነገር ነው። በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ መገኘት በእያንዳንዷ ሰከንድ ሲደሰቱ ነበር። የመጨረሻው ቀን በነበረው ዕለተ እሁድ ፥ መንፈሳዊ ነጋዲያኑ በማለዳ በመነሳት ከቅዱስነታቸው ጋር ለሚያደርሱት የመጨረሻውን መስዋዕተ ቅዳሴ ለመካፈል በትዕግስት ተቀምጠው ይጠብቋቸው ነበር። በመጨረሻው ጠዋት እሳቸውም ልክ እንደ መንፈሳዊ ነጋዲያኑ ደክሟቸው ሊሆን ይችላል ፥ ነገር ግን ልክ በሁሉም አጋጣሚዎች እና ስብሰባዎች ላይ እንደሚያደርጉት በጥሩ ሁኔታ እና በደስታ ስሜት ነበር የደረሱት። በእውነት ለእሳቸውም ከዚህ የተሻለ ሌላ ቦታ ያለ አይመስልም ነበር ፥ ወጣቶቹንም ይሄው ስሜት ተሰምቷቸው ነበር ፥ እናም ይህ የፍቅር ትልቁ ማሳያ ነው።

ግብዣ

ምንም እንኳን ይህ ምዕራፍ የተጠናቀቀ ቢሆንም ፥ ለሁለት ታላላቅ ሁነቶች ሁለት የተለያዩ ሃገራትን በመምረጥ ነበር ያበቃው። እነዚህም እ.አ.አ. 2025 ላይ የሚከበረው የኢዮቤልዩ ዓመት በሮም እንዲሆን እና በ2027 የሚከበረው የሚቀጥለው የዓለም ወጣቶች ቀን ደግሞ በደቡብ ኮሪያዋ ሴኡል እንዲዘጋጅ ተወስኗል። እነዚህ ቀናቶች ምንም እንኳን አንዳንዶቹ ሁነቶች ቅርብ ፥ ሌሎቹ ደግሞ ሩቅ መስለው ቢታዩንም ሁሌም አንድ ጠቃሚ ነገር አሻግረን እንድናይ ያደርጉናል ፥ ይሄም ከተስፋ ጭላንጭል ይልቃል።
 

07 August 2023, 16:35