ፈልግ

መንፈሳዊ ነጋዲያኑ ወጣት ናይጄሪያዊያን በሊዝበን መንፈሳዊ ነጋዲያኑ ወጣት ናይጄሪያዊያን በሊዝበን 

የዓለም ወጣቶች ቀን በሺዎች በሚቆጠሩ መንፈሳዊ ነጋዲያን በተገኙበት በሊዝበን በሥርዓተ ቅዳሴ ተከፈተ

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የመጀመሪያ ሃይማኖታዊ ጉዞዋቸው በሆነውና የተለያዩ ልምዶችን የሚካፈሉበት 37ኛው የዓለም ወጣቶች ቀን የሊዝበን ሊቀጳጳስ በሆኑት ካርዲናል ማኑኤል ክሌሜንቴ በሚመሩት መስዋዕተ ቅዳሴ ተከፍቷል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በደስታ እና የሃሴት ስሜቶች የተሞላው የዓለም ወጣቶች ቀን የመጀመሪያ ቀን ጥዋት ላይ በመስዋዕተ ቅዳሴ ተጀምሮ ማምሻዉን በተለያዩ ሙዚቃዎች በመታጀብ ተጠናቋል።
ዕለተ ማክሰኞ ሃምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በሊዝበን ኤድዋርድ ሰባተኛ ፓርክ ውስጥ የተካሄደው የመክፈቻው ቅዳሴ ከሁሉም የዓለም ማዕዘናት የተውጣጡ ወጣት መንፈሳዊ ነጋዲያንን አንድ ላይ አሰባስቧል።
አዳና እና ፍራንሲስ የተባሉት ወጣቶች ሃገራቸው የሆነውን የናይጄሪያን ባንዲራ የሚያስታውስ በአረንጓዴ እና ነጭ ቀለማት ያጌጠ አምባር ለቫቲካን ዜና ዘጋቢዋ ሲሰጡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ፊት በመገኘታቸው በደስታ እና በጉጉት ስሜት ተሞልተው ነበር።
ከሌሎች መንፈሳዊ ነጋዲያን ጋርም የተለዋወጡትን መቁጠሪያዎችን ፣ የእጅ አምባሮችን እና የባንዲራዎችን ስጦታዎች ትርጉሞቻቸውን ለሌሎች አካፍለዋል። ለእነርሱ ከነዚህ ሁሉ ስጦታዎች የሚልቀው ግን ፥ ከጉዞው ያገኙት እውነተኛ መንፈሳዊ እና ሰብዓዊ ጥምረቶች ነበሩ።
አዳና እና ፍራንሲስ በኩራት ባህላቸውን ፣ ወጋቸውን እና በረከታቸውን ከሌሎች ጋር ለመካፈል ከትውልድ አገራቸው አምጥተዋል። ከተሰበሰበው ሕዝብ መካከል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ነጋዲያኑ እያንዳንዳቸው የየራሳቸውን ባህልና ወግ የሚያንፀባርቁ ባህላዊ ቁሶችን በመያዝ ቅዱስ ቁርባንን ተቀብለዋል።

የመክፈቻ የቅዳሴ ሥነስርዓት

የዓለም ወጣቶች ቀን የመክፈቻ ሥርዓተ ቅዳሴ መንፈሳዊ ነጋዲያኑን ለጸሎት፣ ለደስታ እና በሙዚቃ አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ያደረገ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ አገልግሏል ፥ በዚህ በጣም ልዩ በሆነው ክስተት ላይ ለመሳተፍ ከዓለም ዙሪያ የመጡበትን ልዩ ምክንያትም እርስ ለራሳቸው ሃሳብ ተለዋውጠዋል።
የሊዝበን ሊቀጳጳስ የሆኑት ካርዲናል ማኑኤል ክሌሜንቴ በኤድዋርድ ሰባተኛ ፓርክ ውስጥ የመክፈቻ ሥርዓተ ቅዳሴውን ሲያስጀምሩ “ቤም ቪንዶስ!” (እንኳን በሠላም መጣችሁ) በማለት ሁሉንም ሰው ሞቅ ያለ አቀባበል አድርገውላቸዋል። የዘንድሮው መሪ ቃል በሆነው እና “ማርያም ተነሥታ ፈጥና ሄደች” የሚለውን ርዕስ የስብከታቸው ማዕከል አድርገው ነበር።
ብፁዕ ካርዲናል ማኑዌል ክሌመንት አጽንኦት ሰጥተው እንደተናገሩት ምንም እንኳን የጉዞው ርቀት ፣ ግንኙነቶች እና የተለይዩ ወጪዎች ፈታኝ ቢሆኑም ሁሉም በዚህ ሥነ ስርዓት ላይ የተገኙት ‘መንገደኞች’ እንደሆኑ ገልፀዋል። ምንም እንኳን እነዚህ መሰናክሎች ቢኖሩም ፥ እያንዳንዱ ቀን አዲስ ልምድ ከሚሰጥበት የሕይወት ተመኩሮ ጋር በማመሳሰል እንዲህ ያሉትን ጉዞዎች የመጀመርን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ክሌሜንቴ በመክፈቻው ሥነ ስርዓት እንዳሉት “ሊዝበን በሙሉ ልብ እንኳን ደህና መጣችሁ ትላለች ፥ በፖርቱጋል ምድር ዉስጥ ያሉ ሃገረስብከቶች እንዲሁም ገናም የምታርፉበት ሌሎች አገሮችም እንዲሁ ከልብ ይቀበሏችኋል” በማለት አረጋግጠዋል።

እዚያ መሆን ላልቻሉት

ለብዙዎቹ ተሳታፊዎች ይህ በሕይወታቸው ዘመናቸው ውስጥ አዲስ እና ትርጉም ያለው ምዕራፍ እንደሆነ ያሳያል። አዳና እና ፍራንሲስ ወደዚህ ወደማይረሳው ሊዝበን ውስጥ በተከበረው ሥነ ስርዓት ፥ ባለው ርቀት እና ወጪ ምክንያት ከእነሱ ጋር መቀላቀል ያልቻሉትን ወጣት መንፈሳዊ ነጋዲያንን አስበዋል።
“ናይጄሪያ ሩቅ ናት ፥ የጉዞ ወጪውም ውድ ነው” ሲል አዳና ተናግሯል። ነገር ግን በአካል ወደ ሊዝበን መምጣት ያልቻሉት በመንፈስ እንደሚገኙ አጥብቀው እንደሚያምኑ እና ለደህንነታቸውም እንደሚጸልዩ ተናግረዋል። በአካል መገኘታቸው ምንም ይሁን ምን ሁሉንም ተሳታፊዎች ወደ እዚህ ስፍራ መምጣት ላልቻሉት ጸሎት እንዲያደርጉ እና ሁሉንም የሚያገናኘው ይህ ትስስር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትህትና ጠይቀዋል።
የዓለም ወጣቶች ቀን ሲከበር የአንድነት፣ የእምነት እና የባህል ልውውጥ ድባብ በዓለም አቀፍ ወጣቶች ማህበረሰብ መካከል ዘላቂ ትዝታ እና ወዳጅነት እንደሚፈጥር ጥርጥር የለውም።
የዓለም ወጣቶች ቀን ዋና መሰረት ከሆነው ከክርስቶስ ጋር የሚደረገውን ግንኙነት ወደየትኛውም የዓለም ማዕዘናት በማሸጋገር የርህራሄ ፣ የመረዳት እና የመደመር መንፈስ ከዚህ ልዩ ከሆነ ሥነ ስርዓት ወደ ሌሎች አከባቢዎች ያስተጋባል።
 

02 August 2023, 15:00