ፈልግ

ከእኛ የሚበልጡትን እንመልከት ከእኛ የሚበልጡትን እንመልከት  (©khanchit - stock.adobe.com)

ከእኛ የሚበልጡትን እንመልከት

በሥጋችን ነገር ከበላያችን የሚገኙትን ማለትም ሀብታሞች፣ ምሁራን፣ ባለሥልጣኖች …..ወዘተ ስንመለከት እኛም ዕድላችን ቀንቶ እንደ እነርሱ እንድንሆን እንመኛለን፡፡ በንብረታችን ከእነርሱ ብዙ ባንበላለጥም መካከለኛ ቢሆንም እንደሰትም፡፡ ያለንን ንቀን እንደ እነርሱ ለመሆን እንጥራለን፡፡ ከእኛ የሚያብሱና በብዙም የምንበልጣቸው ብዙዎች አሉ፡፡ ነገር ግን እነርሱ ትተን ከእኛ የሚበልጡትን እናያለን፡፡ ከእኛ ጋር እኩል ያሉትን ወይም የሚያንሱትን ትተን ከሚበልጡት ጋር ለመወዳደር እንመኛለን እኩል መሆንን እንፈልጋለን።

የእዚህ ዝግጅት አቅርቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በመንፈሳዊ ነገር ግን የምናደርገው ተቃራኒውን ነው፡፡ በመንፈሳዊነት የሚበልጡንን ትተን ከእኛ ጋር እኩል የሆኑትንና ከእኛ የሚያንሱትን እንመለከታለን፡፡ ለክርስትና ሕይወታችን አርአያ የሚሆኑንን በጥሩ መንፈስ ሕይወታቸውን የመሩ፣ ቅዱሳንን መመልከት ትተን ደካማና ኃጢአተኛ የሆኑትን ክርስቲያኖች እናያለን፣ እንከተላለን፡፡ እነዚያ በምሳሌነት የሚጠቀሱ፣ አብነት የሚሆኑንን ክርስቲያኖችና ቅዱሳን ሰዎች በመመልከት ፈንታ በመንፈስ ደካማ የሆኑትን ሰዎች መመልከት እንጀምራለን፡፡

ሕይወታችን ከብርቱዎች ጋር ከመወዳደር ይልቅ ከደካሞች ጋር ይወዳደራል፡፡ ለምሳሌ እውነተኞችና ትጉዎች መንፈሳውያን ክርስቲያኖች መከተል ትተን የሰነፎችንና የደካማ ክርስቲያኖችን አብነት እንከተላለን፡፡ ይኸውም እንደ እኛ ደካሞች ወይም ከእኛ የባሱ ደካሞች ክርስቲያን ጋር የሚወዳደር ስለሆነ መንፈሳችን ከእነዚያ ጠንካሮች ክርስቲያኖች አንሶ መገኘቱ አያሳዝነንም፡፡ ከእነርሱም ጋር ተወዳድረን በጥሩ መንፈሳዊነት ያለን ይመስለናል፡፡ በዚህም ተጽናንተን ወደ ፊት መራመድ ቀርቶ ወደ ኋላ እንመለሳለን፡፡ “ስንት ከእኛ የባሱ አሉ?” እያልን በዝቅተኛ ደረጃ በመቆም ሕይወታችንን እንደሰታለን፡፡ በቂና ጥሩ መስሎን ይታየናል፤ ካለንበት ከፍ ማለትና በመንፈሳዊነታችን ወደፊት መቀጠል አናስብም። ከብርቱ ክርስቲያኖች ጋር ከመቆጠር ይልቅ ከሰነፎች ጋር እንዳመራለን፡፡ እነዚያ ከእኛ ጋር በደረጃ እኩል የሆኑትን የጉዞ ጓደኞች አድርገን እናስባቸዋለን። ልክ እንደ እነርሱ ባለው ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራችን እንደሰታለን፡፡

ከእኛ የሚበልጡትን መንፈሳውያን ክርስቲያኖች መመልከት አንፈልግም፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ጸሎት የሚያደርጉ ምስጢራትን የሚያዘወትሩ ብዙ መንፈሳውያን ክርስቲያኖች ከቤተክርስቲያን፣ ከጸሎት፣ ከሚስጢራት የማይለዩ፣ የተጋድሎ፣ የትዕግሥት፣ የትሕትና የፍቅር፣ የንጽሕናና የሃይማኖት ቅናት ያላቸው ሰዎች ያጋጥሙናል።እነዚህ ነገሮችን ሆን ብለው የሚከታተሉ በሥነ ምግባራቸው እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናቸውን ያንፀባርቃሉ። ግን በመንፈሳዊ ቅናት ተነሣሥተን በመከተል ፈንታ «ይህን ደግሞ እንዴት አድርጌ እችለዋለሁ? ከባድ ነው፣ የቅዱሳን ብቻ ነው፣ ለመዳን ደግሞ የግድ የሚያስፈልግ አይደለም» እያልን በስንፍናና በከንቱ እምነታችን በመጽናናት መንፈሳዊ ደካማነታችንን እናጠናክራለን፡፡ «ወንድሞቼ ሆይ! የእኔን ምሳሌነት ለመከተል ተባበሩ፡፡ የእኛንም ምሳሌነት የሚከተሉትን ሁሉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ»(ፊል. 3፣17) እያለ ቅዱስ ጰውሎስ ያበረታታናል፡፡

ከእኛ እጅግ የባሱ ደካማ ክርስቲያኖች ቸልተኞች ጋር አንወዳዳር፣ አብነታቸውንም አንከተል፣ አለበለዚያ እንጠፋለን፡፡ የእነዚያን ብርቱዎችና እውነተኛ መንፈሳዊያን ክርስቲያኖች አብነት፣ ምሳሌና ፈለግ እንከተል፡፡ በእግዚአብሔር መንገድ ከፊት ለፊታችን የሚጓዙትን እንመልከት በአረማመዳቸው በጐ ቅንዓት በልባችን አሳድረን ከእነርሱ ጋር እንፎካከር ከእነርሱም ጋር ለመሆን ጥረት እናድርግ፡፡

 

23 August 2023, 16:15