ፈልግ

የቬትናም ፕሬዝዳንት ቮ ቫን ቱንግ፥ በሆቺ ሚን ከካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ተገናኝተው ሲነጋገሩ የቬትናም ፕሬዝዳንት ቮ ቫን ቱንግ፥ በሆቺ ሚን ከካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ተገናኝተው ሲነጋገሩ 

የቬትናም ፕሬዝዳንት ከአገሪቱ ካቶሊክ ጳጳሳት ጋር በሆቺሚን ከተማ ተገናኙ

የቬትናም ፕሬዝዳንት አቶ ቮ ቫን ቱንግ በሆቺ ሚን ከተማ ውስጥ ከአገሪቱ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸው ታውቋል። ፕሬዝደንቱ ከብጹዓን ጳጳሳቱ ጋር ባደረጉት ንግግር፥ በቅድስት መንበር እና በቬትናም መንግሥት መካከል አዲስ ግንኙነት መመሥረቱን አብስረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቬትናም ፕሬዝዳንት ቮ ቫን ቱንግ፥ ሰኞ ነሐሴ 1/2015 ዓ. ም. በሆቺ ሚን ከተማ በሚገኘውን የጳጳሳት ጉባኤ ጽ/ቤትን በመጎብኘት ከአገሪቱ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ተገናኝተዋል። ፕሬዝደንት ቮ ቫን ቱንግ ከብጹዓን ጳጳሳቱ ጋር የተገናኙት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ቫቲካን ውስጥ ሐምሌ 20/2015 ዓ. ም. ተገናኝተው በቬትናም ነዋሪ የሚሆን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተወካይ እና የጽሕፈት ቤቱ ምሥረታ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ እንደሆነ ታውቋል።

ፕሬዝደንት ቮ ቫን ቱንግ ከብጹዓን ጳጳሳቱ ጋር ባደረጉት ከአንድ ሰዓት በሚበልጥ ስብሰባ፥ አሥር ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ዘጠኝ የቬትናም ካቶሊክ ጳጳሳት እና የሆቺሚን ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሴፍ ነውይን ናንግን ጨምሮ አምስት ካኅናት እና ሁለት ገዳማውያን ተገኝተዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ ከፕሬዝደንቱ ጋር ባደረጉት ንግግሮች መደሰታቸውን ገልጸው፥ “ግልጽ እና ቅን ውይይት ነበር” ሲሉ ገልጸውታል።

ፕሬዚዳንቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ተግባር አድንቀዋል

ፕሬዝዳንት ቫን ቱንግ በበኩላቸው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለቬትናም ማኅበረሰብ በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ያበረከተችው ከፍተኛ አስተዋፅዖ እና አገልግሎት መኖሩን አምነው፥ ከዚያም በቅርቡ በአውሮፓ ያደረጉትን ጉብኝት እና በተለይም በሐምሌ 20/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ያደረጉትን ጉብኝት በማስታወስ፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ቅዱስነታቸው በሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ ያደረጉትን ንግግር በማድነቅ እጅጉን አመስግነው፥ ቬትናምም በዚህ አቅጣጫ እየተጓዘች መሆኗን ገልጸዋል።

ሌሎችን በደንብ ለመረዳት እራስን በሌሎች ሰዎች ቦታ ላይ በማስቀመጥ የማዳመጥ አስፈላጊነትን በማስመልከት ቅዱስነታቸው ለተናገሩት ፕሬዝደንቱ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። የቬትናም ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት አባ ዳዎ ነውይን ቩ በመቀጠልም፥ በቬትናም ስላሉት ካቶሊካዊ ተቋማት አጠቃላይ ዕይታ ገለጻ አድርገው፥ የቬትናም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤቶችን ብቻ እንደሚያስተዳድር ከገለጹላቸው በኋላ ፕሬዚዳንቱ ጉዳዩን እንደሚመለከቱት አረጋግጠዋል።

የቬትናም ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት አባ ዳዎ ነውይን ቩ፥ ርዕሠ መስተዳድር በአውሮፓ ባደረጉት ስኬታማ ጉብኝት መልካም ምኞታቸውን ገጸው፥ የሆቺሚን ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሴፍ ነውይን ናንግ፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በአገሪቱ የምታከናውናቸውን አገልግሎቶች አብራርተዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በመጨረሻም ለፕሬዝደንት ቫን ቱንግን ሁለት ስጦታዎችን ያበረከቱላቸው ሲሆን፥ የመጀመሪያው እሳቸውና ባለቤታቸው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በተገኛኙበት ወቅት የተነሱትን ምስል እና ሁለተኛ ወደ ቬትናምኛ ቋንቋ የተተረጎመ፥ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መሆኑ ታውቋል።

የቬትናም እና የቅድስት መንበር ግንኙነት

የቬትናም ፕሬዚደንት በቅርቡ በቫቲካን ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት፥ ሁለቱ ወገኖች በግንኙነታቸው ላመጡት ጉልህ መሻሻል እና የካቶሊክ ማኅበረሰብ በሀገሪቱ እስካሁን ላበረከተው አወንታዊ አስተዋፅዖ ታላቅ አድናቆትን ገልጸዋል።

በቅድስት መንበር እና በቬትናም መካከል የነበረው ግንኙነት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 1975 ጀምሮ ተቋርጦ የቆየ ቢሆንም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 1990 ዓ. ም. ጀምሮ አበረታች ክንውኖች ታይተዋል። በወቅቱ በቅድስት መንበር የፍትህ እና የሰላም ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የነበሩት ብፁዕ ካርዲናል ሮጀር ኤቸጋሪ ወደ ቬትናም በመሄድ የመጀመሪያውን ኦፊሴላዊ ጉብኝት ማድረግ መቻላቸውም ይታወሳል።

አዲስ ጅምር

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2007 ጠቅላይ ሚኒስትር ንጉዪን ታን ዱንግ ከቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ቤኔዲክት 16ኛ ጋር ከተገናኙ በኋላ ግንኙነቱ ይበልጥ የተሻሻለ ሲሆን፥ ይህም ከሰላሳ ዓመታት በላይ የቬትናም ርዕሠ መስተዳድር በቫቲካን የመጀመሪያ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉበት እንደነበር ይታወሳል።

በመቀጠልም በወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዝደንት የነበሩት ንጉየን ሚን-ትሪት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታህሳስ 11/2009  በቬትናም እና በቅድስት መንበር መካከል የጋራ ቡድን ለመመሥረት መንገድ መክፈታቸው ይታወሳል። የሥራ ቡድኑ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2011 ነዋሪነቱን በሲንጋፖር ያልሆነ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተወካይ (የአሁኑ ሞንሲኞር ማሬክ ዛሌቭስኪ) በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ እንዲሾሙ ካደረገ በኋላ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አገሪቱን በየጊዜው እንዲጎበኝ ፈቃድ እንደተሰጣቸው ይታወሳል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በቅርቡ የተደረሰውን የቅድስት መንበር እና የቬትናም ስምምነት የግንኙነት መስመር ጫፍ ሳይሆን፥ በግንኙነታቸው የመከባበር እና የመተማመን ምልክት ያለበት አዲስ ጅምር” ሲሉ ገልጸውታል።

በቬትናም የካቶሊካዊ ምዕመናን ቁጥር ከጠቅላላው ሕዝብ ቁጥር ዘጠኝ በመቶው የሚሆነውን የሚሸፍን ሲሆን፥ ይህም የአገሪቱን ግማሽ ሕዝብ ከሚወክለው ከቡዳ እምነት ቀጥሎ ሁለተኛው ትልቁ የሃይማኖት ተቋም እንዲሆን ማድረጉ ታውቋል።

 

10 August 2023, 17:22