ፈልግ

የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሐዘን የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሐዘን 

የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሐዘን

እግዚአብሔር ያቺ ከሁሉም የበለጠች ፍጥረቱን እንደ ሁሉም ሰው በኃጢአት ቆሻሻ እንድትነካ ባይፈቅድም በምድር ለሚኖሩ ለሰው ልጅ ሁሉ ከሚደርሰበት ሐዘንና ስቃይ ነጻ እንድትሆን ግን አልፈቀደም። እንደ ማንኛውም ሰው እንድትሰቃይ ተዋት። እመቤታችን ማርያም ከሌሎች የበለጠ ሐዘን መከራና ስቃይ ተቀበለች። በስቃይ በኩል ከኢየሱስ ሌላ የሚበልጣት የለም። የቅዱሳን ሰማዕታት የከፋ መከራ እንኳ ከእመቤታችን ማርያም ጋር ሊወዳደር አይችልም። እርስዋ ከልጇ ከኢየሱስ ጋር በመሆን «እናንተ መንገድ የምታልፉ ሁሉ በእኔ ላይ እንደ ተደረገው የሚመስል መከራ እንዳለ ተመልከቱ» (ሰቆ. ኤር. 1፣12) እያለች ታሳስበናለች።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ሰለዚህ ቅዱሳን «ሰማዕተ ሰማዕታት፣ ንግሥተ ነግሥታት» እያሉ ይጠሯታል። የማርያም ሰማዕትነት ከሌሎች ሰማዕታት የሚበልጠው በሥጋዊ ስቃይ ሳይሆን በመንፈሳዊ በኩል እንደሆነም ይናገራሉ። ይህም ስቃይ እንደ አንድ የተሳለ ሰይፍ ልቧን ይሰንጥቀው እንደነበር ቅዱሳኖቹ ያውቃሉ። ቅዱስ በርናርዶስ «የማርያም ሰማዕትትነት ከብረት የጠነከረ ነው» ይላል። ኢየሱስ እንደ ተወለደ የእርሱ ስቃይ ወዲያው ጀመረ። የእርስዋም ስቃይ በዚያው ጀመረ። የልጇን ስቃይና ውርደት በማሰብ በመሰቃየት ልቧ በሐዘን ይወጋ ነበር። ቅዱስ አልበርቶ «የጽዮን ልጅ ድንግል ሆይ የሐዘንሽን ጥልቀትና ስፋት እንደ ባሕር ነው” (ሰቆ. ኤር. 2፣12) የሚለውን የሰቆቃው ኤርምያስን ጥቅስ ለእመቤታችን ማርያም ይደግመዋል። እመቤታችን ማርያም ይህ ሁሉ ሐዘን የሚደርስብን በእርስዋ ላይ በተደረገው ስቃይ ሳይሆን በኋላ በልጇ ላይ ስለሚደርሰው መከራ በማሰብ ነበር።

እንግዲህ ሐዘኗን ብቻ ከሚያስተነትኑ አፍቃሪዎች ጋር በመሆን እነዚህን ሰባት ነጥቦች ቀስ ብለን እናስብ፣

1.    ኢየሱስን ወደ ቤተመቅደስ ስታቀርበው ነቢዩ ስምዖን «እነሆ የብዙዎች ልብ ሐሳብ ይገለጥ ዘንድ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል። በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል»(ሉቃ. 2፣34) ሲላት ልቧ በሐዘን ተሞላ። ይህ የመጀመሪያ ሐዘኗ ሆነ።

2.    መልአክ ቅዱስ ዮሴፍን «ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልጋልና ተነሥ ሕፃኑንና እናቲቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ» (ማቴ. 2፣13      ) ባለው ጊዜ የእመቤታችን ልብ በድጋሚ በሐዘን ተነካ። ከማናቸውም በደል ነፃ የሆነው ንጹሕ ልጅዋን ሰዎች ሊያላግጡበትና ሊገድሉትና ሊያጠፋበት መሆኑን በማሰብ በፍጹም አዘነች።

3.    ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሆኖ በቤተመቅደስ ከወላጆቹ ጠፍቶ በነበረው ጊዜ እርስዋ በጣም አዝና ከቅዱስ ዮሴፍ ጋር «ነፍሴ የወደደችውን አያችሁትን?» (መኃልየ መኃልይ 3፣3 ) በማለት ፈለገችው፤ ስታገኘውም «ልጄ ሆይ ለምን እንዲህ አደረግኸን? እነሆ አባትህና እኛ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበር» (ሉቃ. 2፣49) አለችው።

4.     በቀራኒዮ ኮረብታ ልጇ መስቀል ተሸክሞ ደሙ እየተንጠባጠበ ስታገኘው እንደገና ሐዘኑ በረታባት ሰዎቹም ሲያፌዙበት፣ሞት ተፈርዶበት ደፋ ቀና እያለ ስታየው ሐዘን ተሰማት።

5.    እንደ ወንጀለኛ በሌቦች መካከል ተሰቅሎ ከብዙ ጣር በኋላ ሲሞት አይታ እጅግ አዘነች።

6.    ኢየሱስ ጐኑን በጦር ከተወጋ በኋላ ከመስቀል አውርደውት እርስዋ ስታቅፈው ልቧ በሐዘን ተናወጠ።

7.    ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ወደ መቃብር ሲወርድ ባየችው ጊዜ በጣም ሐዘን ተሰማት። ይህ ሁሉ ሐዘን በንጹሕ ልቧ ሲገባ በጣም ጐዳው።

ይህን ሐዘኗን እኛም እንድናሰበውና ስቃይዋን ስቃያችን እንዲሆን ይገባናል። ምክንያቱም እናታችን ከመሆኗ በላይ ልጇ ይህን ሁሉ ስቃይ የተቀበለው ስለ እኛ ኃጢአት ምክንያት ነው። ጥበበ ሲራክ እንደሚለው እንግዲህ የእናታችንን ሐዘንና ለቅሶ አንርሳ እናጽናናት በልባችን እናትመው። እርስዋንና ልጇን እንደገና የሚያሰቃያቸውን ኃጢአት እንጥላ።

 

 

18 August 2023, 11:12