ፈልግ

የር.ሊ.ጳ. መልዕክተኛ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ስታኒስላው ዲዚዊስ በፖላንድ ኮዴን ከተማ በተከበረው በዓል ላይ። የር.ሊ.ጳ. መልዕክተኛ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ስታኒስላው ዲዚዊስ በፖላንድ ኮዴን ከተማ በተከበረው በዓል ላይ።  (Fr. Marek Weresa)

ፖላንዳዊው ካርዲናል ዲዚዊዝ ‘በዩክሬን ያለው ደም መፋሰስ ይብቃ!’ ማለታቸው ተነገረ

በፖላንድ የምትገኘው ቤተክርስትያን የኮዴን እመቤት ፣ የፖድላሴ ንግሥት እንዲሁም የአንድነት እናት የሆነችዋን የቅድስት ድንግል ማርያም ምስል አክሊል የተጫነበት 300ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ የተገኙት ብፁዕ ካርዲናል ስታኒስላው ዲዚዊዝ አጎራባች ሃገር በሆነችው ዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት እየደረሰ ያለው ደም መፋሰስ እንዲቆም ተማጽነዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብፁዕ ካርዲናል ስታኒስላው ዲዚዊዝን መልእክተኛ አድርገው የሾሙበት ልዩ ደብዳቤ ላይ ፥ በኮዴን የምትገኘው ቤተክርስቲያ የእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን የተአምራት ቦታ እንደሆነ ፥ ብዙ ሰዎች ለመጸለይ የሚመጡበት እና ሕይወታቸውን ለማርያም አደራ የሚሰጡበት ቦታ እንደሆነ ገልፀዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የፖድላሴ ንግሥት ፥ የአንድነት እናት የሆነችውን የቅድስት ድንግል ማርያም ምስል አክሊል የተጫነበት 300ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ የክራኮው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ዲዚዊስን ጳጳስ አድርገው ሰይመዋቸዋል።
የቀድሞው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ዲዚዊስ ፥ ማክሰኞ ዕለት በተደረገው ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ባደረጉት ስብከት ፥ የበፊቱ ካርዲናል ካሮል ዎጅቲላ የሮም ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ከመመረጣቸው በፊት ወደ ኮዴን ለመንፈሳዊ ጉዞ መጥተው እንደነበር ተናግረዋል።
"ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የሰዎችን ትኩረት የክርስቶስ እናት ወደ ሆነችው ቅድስት ድንግል ማሪያም ይስባሉ ፥ እመቤታችን የእግዚአብሔርን ህዝቦች አንድ ታደርጋለች ፥ እናም እኛ እራሳችንን ያገኘነው ይህ የእግዚአብሔር ህዝብ ውህደት ውስጥ ልዩ ታሪካዊ ትርጉም ባለው ምድር ላይ ነው። በተጨማሪም የተነጣጠሉት አብያተ ክርስቲያናት ማለትም የምዕራቡ እና የምስራቁ አቢያተ ክርስቲያናት ስብሰባ የተካሄደው እዚህ ነበር” በማለት ተናግረዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ዲዚዊዝ አክለውም ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ምስራቅ ፖላንድ ፥ በፖድላሴ ክልል ውስጥ በምትገኘው ኮዴን ከተማ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት እንደተናገሩት “ከተማዋ እናት የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማሪያምን ትፈልግ ነበር ፥ አንድነት የምትፈጥር ፥ ፖላንድኛ ቢናገሩም፣ ሩትኛ ቢናገሩም ወይም ሊቱዌኒያ ቢናገሩ ሁሉንም ልጆችዋን ለይታ የምታውቅ እናት ይፈልጉ ነበር” ብለዋል።

ደም መፋሰሱ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል

ካርዲናሉ በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በመጥቀስ ፥ በመላው ዓለም ፊት በአውሮፓ እየሆነ ያለው ነገር ተቀባይነት እንደሌለው ጠቁመዋል።
ጦርነቱ በዩክሬን የሚገኙ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መሬታቸውን፣ የመኖር መብታቸውን፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን እየነፈገ ፥ ሞትና ውድመት እየዘራ ነው። የስላቭ ወንድሞች (የስላቭ ቋንቋዎች የኢንዶ-አውሮፓውያን ቤተሰብ ናቸው ፤ በምስራቅ ሩሲያውያን፣ ዩክሬናውያን እና ቤላሩያውያን ፤ ምዕራብ ስላቭስ የሚባሉት ፖኦላንዶች፣ ቼኮች፣ ስሎቫኮች እና ዌንድሶች፣ ወይም ሶርብያዎች እና ደቡብ ስላቭ የሚባሉት በዋናነት ሰርቦች፣ ክሮአቶች፣ ቦስኒያውያን፣ ስሎቬናውያን፣ መቄዶኒያውያን እና ሞንቴኔግሮናዊያን ናቸው)
እርስ በርስ መዋጋት አይችሉም ፥ እርስ በርሳቸው መገዳደል የለባቸውም ፥ ጥፋትን መዝራት የለባቸውም ፥ እያየን ያለነውን የመከራ ብዛት ማባዛት የለባቸውም። የቃየን እጅ መቆም አለበት ፥ ይህን ጥላቻ፣ ብጥብጥ እና የወንድማማቾችን ጦርነት ማስቆም አለብን ፥ ደም መፋሰሱ ይብቃ!” በማለት በአፅንኦት ተናግረዋል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ልዑክ የሆኑት ካርዲናል በማከልም “ወንድም ህዝብ የሆናችው ስላቮች ፥ በሕዝቦቻችን መካከል የሚታየውን የወንድማማችነት እና አብሮ የመኖር ዕሴት ለዓለም ምሳሌ እንሁን እንጂ ጭፍን ጥላቻን አናሳይ። የኮዴኗ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ይህ ጦርነት የሚያበቃበትን እንዲሁም ዕርቅ እና ሰላምን የምናመጣበትን መንገድ እንድታሳየን እንለምን። ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር በመሆን ፥ የሰው ልጅን የወደፊት እጣ ፈንታ የሰላም ንግሥት በሆነችዋ በቅድስት ድንግል ማሪያም እጅ እናስቀምጣለን” ብለዋል።

የእመቤታችን ንግሥና መታደስ

ሃምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተደረገ ሥነ ስርዓት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የተባረኩ አዳዲስ አክሊሎች በማርያም እና በኢየሱስ ሥዕል ላይ ተቀምጠዋል።
በዚህም ሥነ ስራዓት ላይ በሲድልስ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃዚሚየርዝ ጉርዳ እና የመቅደስ ጠባቂ በሆኑት ‘ሚሽነሪ ኦብላቴስ ኦፍ ሜሪ ኢማኩሌት’ በተባሉ ገዳማዊያን በተደረገላቸው ግብዣ መሰረት እጅግ ብዙ መንፈሳዊ ተጓዦች በቦታው ተገኝተው ነበር።
በኮዴን ውስጥ ያለው ቤተ መቅደስ ታሪክ የሚነሳው በ 17 ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው። በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ኡርባን ስምንተኛ ግብዣ መሰረት ሚኮላጅ ሳፒሃ (የፖላንድ - ሉቲኒያ ንጉስ የነበረ) የጳጳሱ ቤተ መቅደስ ውስጥ በሚገኘው የጓዳሉፔ ወይም የግሪጎሪያን ሥዕል ተብሎ በሚታወቀው የእመቤታችን ምስል ሥር ተንበርክኮ ጸለየ። ከዚህ ጸሎት በኋላም ተፈወሰ።
ሳፒሃ ይተፈወሰበትን የእመቤታችንን ሥዕል በማጭበርበር ወስዶት የነበረ ቢሆንም እንደገና በ1631 ወደ ኮዴን አምጥቶ መልሶታል ፤ እስከ ዛሬ ድረስም ምስሉ በክብር በቤተ መቅደሱ ውስጥ አለ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ቅዱስ አባታችን ምስሉ እዚያው እንዲቆይ ፈቅደዋል።
ይህ የጌታች ኢየሱስ ክርስቶስ እናት የሆነችዋ ቅድስት ድንግል ማሪያም ምስል እ.አ.አ. በ 1723 በጊዜው በነበሩ ር.ሊ.ጳ.  አክሊል የተጫነበት ሲሆን ፥ ይህም በፖላንድ ግዛት ውስጥ የሚገኝ የመጀመሪያው እና ብቸኛው ምስል ያደርገዋል።
 

16 August 2023, 12:14