ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት  

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ለ2015 ዓ.ም የፍልሰታ ማርያም በዓል ያስተላለፉት መልእክት

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት የ2015 ዓ.ም የፍልሰታ ማርያም በዓል አስመልክተው ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልእክት

«ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባስ ወርቅ ዑጽፍት ወኀብርት፣ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፍና ነግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች»(መዝ. 45፣10 )

የተከበራችሁ ብፁዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ደናግላን፣ ዲያቆናት፣ ምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

እንኳን ለ2015 ዓ.ም ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የፍልሰታ ማርያም በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን!

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን የፍልሰታ በዓል ዛሬ እያከበርን እንገኛለን። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች” (ሉቃስ 1፡46-47) በማለት ውዳሴ ታቀርባለች። በዚህ ጸሎት ውስጥ “ከፍ ከፍ ታደርገዋለች እና ሐሴት ታደርጋለች” የሚሉትን ሁለት ግሶች እንመልከት። ሐሴት የምናደርገው በሕይወታችን ውስጥ በጣም ውብ የሆነ ነገር ሲከሰት፣ እንዲሁ በውስጣችን ያለውን ደስታ በቀላሉ በመግለጽ ሳይሆን፣ ነገር ግን ነፍሳችንን እና መላው ሰውነታችን ተሳታፊ በሚሆኑበት ሁኔታ በተቀናጀ መልኩ ሐሴት በማድረግ ለመግለጽ እንፈልጋለን። የማርያም ሐሴት የመነጨው ከእግዚአብሔር ነው። እኛም በሕይወታችን ውስጥ በጌታ ተደስተን ደስታችንን በሐሴት ገልጸን ሊሆን ይችላል፣ በአንድ ነገር ውጤታማ በምንሆንበት ወቅት ተደስተን ሊሆን ይችላል፣ መልካም የሆነ ዜና ሲያጋጥመን ደስታችንን ገልጸን ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን ዛሬ ማርያም በጌታ እንዴት ሐሴት ማድረግ እንደሚቻል ታስተምረናለች፣ ምክንያቱም እርሱ “ታላላቅ ነገሮችን አድርጎልናልና”።

በሕይወታችን ውስጥ የሚገጥሙን ታላላቅ የሚባሉ ክስተቶች ደግሞ ታላቅ ነገር ያደረግልንን ፈጣሪ ከፍ ከፍ እንድናደርግ ያነሳሳናል። በእውነቱ ከፍ ከፍ ማድረግ ማለት ለታላቅነቱን፣ አንድ ታላቅ የሆነን ነገር በእውነቱ ከፍ ማድረግን የሚያመልክት ሲሆን ለታላቅነቱ እና ለውበቱ እውቅና በመስጠት እርሱን ከፍ ከፍ ማድረግ ማለት ነው። ማርያም የጌታን ታላቅነት ከፍ ከፍ ታደርጋለች ፣ በእውነት ታላቅ ነው ብላ አመስግነዋለች። በህይወት ውስጥ ታላላቅ ነገሮችን መሻት አስፈላጊ ነው ፣ አለበለዚያ በብዙ ትናንሽ ነገሮች እንወሰዳለን። ሕይወታችን ደስተኛ እንዲሆን ከፈለግን፣ በሕይወታችን ውስጥ ለእግዚአብሔር ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን ማርያም ታሳየናለች፣ እርሱ ብቻ ታላቅ እንደ ሆነ ታስምረናለች። እነዚህን ታላላቅ የሚባሉ ነገሮችን ወደ ጎን በመተው ብዙ ጥቅም የማይሰጡ ነገሮችን ለምሳሌም ጭፍን ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ብጥብጥ ፣ ምቀኝነት ፣ ከልክ በላይ በሆነ መልኩ ለቁሳቁሶች ያለንን ፍላጎት . . .  ወዘተ የምንከተልባቸው ብዙ ወቅቶች አሉ። በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ስህተት እንፈጽማለን። ማርያም ጌታ በእርሷ ውስጥ ያከናወናቸውን “ታላላቅ ነገሮች” እንድንመለከት ዛሬ ትጋብዘናለች።

ዛሬ የምናከብራቸው “ታላላቅ ነገሮች” ናቸው። ማርያም ወደ ሰማይ ፈልሳለች፣ ትሑት የሆነች ማርያም ከሁሉም በፊት ከፍተኛ ክብርን ተቀበለች። እንደ እኛ ፍጡር የሆነች እርሷ በነፍስ እና በሥጋ ዘላለማዊ ትሆናለች። እናቶች ልጆቻቸው ከሄዱበት ቦታ ወደ ቤት እስኪመለሱ ድረስ እንደ ሚጠብቁ ሁሉ እርሷም እኛን በእዚያ በሰማይ ቤት ሆና ትጠባበቀናለች። በእርግጥ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሁሉ እርሷን “የሰማይ ደጃፍ” እያሉ ነው የሚያወድሷት። እኛም ወደ ሰማይ ቤት የምንጓዝ ምጻተኞች ነን። ዛሬ ማርያምን ቀና ብለን ወደ ሰማይ እንመለከታለን፣ በእዚያም የእኛ መዳረሻ የሆነውን ግባችንን እናያለን። አንድ እንደኛ ፍጡር የሆነች ከሙታን ወደ ተነሳው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር እንደ ተወሰደች እናያለን፣ ያቺ እንደኛ ፍጡር የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአዳኛችን እናት በመሆን ከጎኑ ትቀመጣለች። በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ አዲሱ አዳም የሆነው ክርስቶስ አዲሲቷ ሔዋን ከሆነችው ማርያም ጋር በጋራ በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ እናያቸዋለን፣ እኛም በእዚህ ምድር ምጻተኞች ሆነን በምንኖርበት ጊዜ ለእኛ ታላቅ የሆነ መጽናናትን እና ተስፋን ይሰጠናል።

የማርያምን የፍልሰታ አመታዊ በዓል በምናክብርበት በአሁኑ ወቅት ለሁሉም የሰው ልጆች በተለይም በጥርጣሬ እና በሐዘን ለተሰቃዩ እና ዓይኖቻቸው ወደ ታች ወደ ምድር አቀርቅረው ተክዘው ለሚገኙ ሰዎች ጥሪ ይቀርብልናል። ቀና ብለን ክፍት የሆነውን ሰማይ እንመልከት፣ ፍርሃት ሊያድርብን በፍጹም አይገባም፣ በጣም ሩቅ የሆነ ሥፍራም አይደለም፣ ምክንያቱም በሰማይ ደጃፍ ላይ የምትጠብቀን አንድ እናት አለችና። የሰማይ ንግሥት የሆነችው እርሷ የእኛም እናት ናት። እርሷ ትወደናለች፣ ፈገግታዋንም ታሳየናለች፣ ትንከባከበናለችም። እያንዳንዷ እናት ለልጆቿ የተሻለውን ነገር እንደ ምትፈልግ እና እንደ ምታስብ ሁሉ “በእግዚአብሔር ፊት ውድ ናችሁና፣ እናንተ የተፈጠራችሁት ትንንሽ የሆኑ የአለም ነገሮችን ለመፈጸም ሳይሆን፣ ነገር ግን እናንተ የተፈጠራችሁት ለሰማይ ታላቅ ደስታ ነው” በማለት ተናገረናለች። አዎን! ምክንያቱም እግዚአብሔር አስደሳች አምላክ ነውና።  እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እጃችንን ይዛ እንድትመራን እንፍቀድላት። በእያንዳንዱ ቀን መቁጠሪያችንን በእጃችን ይዘን የመቁጠሪያ ጸሎት በምናደርግበት ወቅቶች ሁሉ ሕይወታችን ወደ ላይ አንድ እርምጃ እንዲራመድ እናደርጋለን ማለት ነው።

በዛሬ ቀን የቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል ላይ ማርያም በሥጋ እና በነፍስ ወደ ገነት በማረግ ክብር ማግኘቷ ላይ እናሰላስላለን። ልጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስቃይ፣ በመከራ እና በመስቀል ላይ ሞቶ፣ በትንሳኤው ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሳ ሁሉ፣ እርሷም እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ እና በነፍስ ወደ ላይ በመፍለስ ሁለቱም እናት እና ልጅ ወደ ሰማይ እንደ ወጡ ከቅዱስ ወንጌል እንማራለን። ይህ በአጠቃላይ ሲታይ ያለ መስቀል ትንሳኤ፥ ያለ ጭንቀት፣ ሐዘን እና መከራ ፍልሰታ እንደ ሌለ እንማራለን። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወት የሚያሳየንም ይህንኑ ነው።

እግዚአብሔር ያቺን ከሁሉም የበለጠች ፍጥረቱን እንደ ሁሉም ሰው በኃጢአት ቆሻሻ እንድትነካ ባይፈቅድም ነገር ግን በምድር ለሚኖሩ ለሰው ልጅ ሁሉ ከሚደርስባቸው ሐዘንና ስቃይ ነጻ እንድትሆን ግን አልፈቀደላትም። እንደ ማንኛውም ሰው እንድትሰቃይ ተዋት። እመቤታችን ማርያም ከሌሎች የበለጠ ሐዘን መከራና ስቃይ ተቀበለች። በስቃይ በኩል ከኢየሱስ ሌላ የሚበልጣት የለም። ቅዱሳን ሰማዕታት ገጥሟቸው ከነበረው የከፋ መከራ እንኳን ከእመቤታችን ማርያም ጋር ሊወዳደር አይችልም። እርሷ ከልጇ ከኢየሱስ ጋር በመሆን ብዙ ስቃይ አሳለፈች።

ሰለዚህም ቅዱሳን «ሰማዕተ ሰማዕታት፣ ንግሥተ ነግሥታት» እያሉ ይጠሯታል። የማርያም ሰማዕትነት ከሌሎች ሰማዕታት የሚበልጠው በሥጋዊ ስቃይ ሳይሆን በመንፈሳዊ በኩል እንደሆነም ይናገራሉ። ይህም ስቃይ እንደ አንድ የተሳለ ሰይፍ ልቧን ይሰንጥቀው እንደነበር ቅዱሳኖቹ ያውቃሉ። ቅዱስ በርናርዶስ «የማርያም ሰማዕትነት ከብረት የጠነከረ ነው» ይላል። ኢየሱስ እንደ ተወለደ የእርሱ ስቃይ ወዲያው ጀመረ። የእርስዋም ስቃይ በዚያው ጀመረ። የልጇን ስቃይና ውርደት በማሰብ በመሰቃየት ልቧ በሐዘን ይወጋ ነበር። ቅዱስ አልበርቶ «የጽዮን ልጅ ድንግል ሆይ የሐዘንሽ ጥልቀትና ስፋት እንደ ባሕር ነው” (ሰቆ. ኤር. 2፣13) የሚለውን የሰቆቃው ኤርምያስን ጥቅስ ለእመቤታችን ማርያም ይደግመዋል። እመቤታችን ማርያም ይህ ሁሉ ሐዘን የደርሰባት በእራሷ ላይ በተፈጸመው ስቃይ ሳይሆን በኋላ በልጇ ላይ ስለሚደርሰው መከራ በማሰብ ነበር።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ እና በነፍስ ወደ ሰማይ ከመፍለሷ በፊት 7 የሐዘን ወቅቶችን በምድር ላይ አሳልፋለች።

1ኛ “ይህ ሕፃን በእስራኤል ለብዙዎች መነሣትና መውደቅ ምክንያት እንዲሆን፣ ደግሞም ክፉ ለሚያስወሩበት ምልክት እንዲሆን ተወስኗል፤ የብዙዎችም የልብ ሐሳብ የተገለጠ እንዲሆን፣ የአንቺም ነፍስ ደግሞ በሰይፍ ይወጋል” የሚለው የስምዖን ትንቢት (ሉቃስ 2፡32-35) የመጀመርያው ሐዘን የፈጠረባት ነገር ነው።

2ኛ ሄሮድስ ልጁን ለመግደል በፈለገበት ወቅት ወደ ግብፅ የተደረገ ሽሽት (ማቴዎስ 2፡13-) ሐዘን ፈጥሮባታል።

3ኛ ኢየሱስ በቤተመቅደስ ወስጥ በጠፋ ጊዜ ለሦስት ቀናት በድካም እና በሐዘን ዮሴፍ እና ማርያም እርሱን በፈለጉበት ጊዜ (ሉቃስ 2፡43-) እጅግ በሐዘን ተሞልተው ነበር።

4ኛ ኢየሱስ መስቀሉን ተሸክሞ በሚሄድበት ወቅት መውደቁን በተመለከተችበት ወቅት (ሉቃስ 23፡27-) እንደ እናት ሐዘን ገብቷት ነበር።

5ኛ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በተሰቀለበት ወቅት (ዮሐንስ 19፡18-) ልጇን በመስቀል ላይ ሆኖ ስታይ አዝና ነበር።

6ኛ ኢየሱስን ከመቀል ላይ ባወረዱት ጊዜ (ማርቆስ 15፡43-) በእቅፏ ውስጥ አስገብታ በማቀፍ ክፉኛ አዝና ነበር።

7ኛ የኢየሱስ ስርዓተ ቀብር (ዮሐንስ 19፡41-) ባየችበት ወቅት እጅግ አዝና ነበር።

ማርያም በእነዚህ ሰባት የሐዘን ጊዜያት ውስጥ ሕይወቷን አሳልፋ ነበር። በመጨረሻም ለመፍለስ በቅታለች።

ዛሬም ቢሆን የተወደዳቹ ውድ ሀገራችን ኢትዮጲያ እነዚህን የማርያም ሐዘኖች በሚመስሉ ሁኔታዎች ውስጥ እያለፈች ትገኛለች። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አገራችን አሁን በገጠማት የእርስ በእርስ ግጭት ምክንያት ከተከሰተው እና እየተከሰተ በሚገኘው መከራ እና ስቃይ እንዲያበቃ እና ሀገራችን ኢትዮጲያ በሰላም በፍቅር በአንድነት፣ በእኩልነት፣ በመከባበር የምንኖርባት ሀገር ትሆን ዘንድ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት እንማጸናለን።

 

መልካም የፍልሰታ በዓል ለሁላችን፡

እግዚአብሔር ሕዝባችንን እና አገራችን ኢትዮጲያን ይባርክልን! 

 

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፣ የኢትዮጲያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት

ነሐሴ 16 /2015 ዓ.ም

 

22 August 2023, 09:32