ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን  

ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የ2015 ዓ.ም. የፍልሰታ ፆም መግቢያን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት

“ከእሺታዋ የተነሣ የቅድስት ሥላሴ ውብ ቤተመቅደስ፣ የዳግማዊ አዳም ምድራዊ ገነት፣ የመንፈስ ቅዱስ ሙሽሪት፣ የመላእክት እሀት፣ የቅዱሳን እናት ሆነች”

ለሁለት ሳምንታት የሚቆየው የፍልሰታ ለማርያም ጸሎት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምድራዊ ሕይወቷን አጠናቃ ወደ ሰማይ የተወሰደችበትን ቀን በታላቅ ድምቀት ለማክበር ምዕመናን ልዩ የሆነ መንፈሳዊ ዝግጂት የምያደርጉበት ጸሎት ነው፡፡ “ፍለሰታ” የሚለው ቃል ፈለሰ ከሚለው ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ወይም ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ሥፍራ መሄድን ያመለክታል፡፡ ፍልሰታ ለማርያም ስንል ታዲያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምድራዊ ሕይወቷን አጠናቃ በነፍስና በሥጋ ወደ ሰማይ ተወሰደች ማለታችን ነው፡፡ የልጇ የኢየሱስ ሥጋ ከሞት በኋላ እንደማንኛውም ሥጋ በመቃብር ውስጥ በስብሶ እንዳልቀረ ሁሉ፤ የቅድስት ሥላሴ ሁለተኛ አካል ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋም ከመለኮታዊ ልጇ ሥጋ ጋራ ፍጹም ኅብረት ያለው በመሆኑ በመቃብር ውስጥ በስብሶ አልቀረም ማለታችን ነው፡፡ ይህ ለመለኮታዊ አሠራር ፍጹም ታማኝ፣ ታዛዥና ምቹ ለሆነችው ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር የተቸረ ልዩ ዕድልና ነጻ ስጦታ ነው፡፡  

በርግጥ በብሉይ ኪዳን ዘመንም ነቢዩ ኤልያስ እንዲያውም ሳይሞት ወደ ሰማይ እንደተወሰደ ከሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት (2፡ 1-18) እናነባለን፡፡ ሔኖክም 365 ዓመታት በዚህች ምድር ከኖረ በኋላ እግዚአብሔር እንደወሰደው ከኦርተ ዘፍጥረት (5፡ 24) እንገነዘባለን፡፡ እግዚአብሔር በሥራው ፍጹም ስለሆነ ይህን ለምን አደረገ ብለን ብንጠይቅ አእምሮኣችንን ሊያረካ የሚችል ሰብኣዊ መልስ ላናገኝ እንችላለን፡፡ ያልነበረውን ነገር መኖር እንዲችል ያደረገ አምላካችን ግን የፈቀደውን ሰው ከነነፍሱና ከነሥጋው ጋር ወደ ራሱ መውሰድ እንደማያቅተው አምነታችን ነው፡፡ አንድ እርግጠኛ መሆን የምንችለው እውነት ግን የእግዚአብሔር ሥራ ሁሉ ፍጹም ነው፤ የማይከለስ ነው፤ ትክክለኛ ነው፡፡ እርሱ ራሱ ፍትሕ ስለሆነ ኢፍትሓዊ ነገር አይፈጽምም፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመጀመሪያ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፍ በኃጢኣት ከወደቁበት ጊዜ ጀምሮ በእግዚአብሔር በማዳኑ እቅዱ ውስጥ እንደነበረች ከኦሪት ዘፍጥረት 3፡ 15 እንረዳለን፡፡ እግዚአብሔር ሁላችንንም ሲፈጥረን በዓላማ ነው፡፡ ለዓለማው መኖር ወይም አለመኖር ግን የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥር ከሌሎች ፍጥረታት ልዩ በሚያደርጉ በነጻነት፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ አስታጥቆት ነውና፡፡ ስለሆነም አንድ ሰው ለተፈጠረለት ዓላማ መኖር ወይም ያለመኖር የእርሱ ምርጫ ይሆናል፡፡ 

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰማይና ምድር ሊይዙት የማይችለው የእግዚአብሔር ልጅ እናት እንድትሆን ከአርያም በተጠየቀች ጊዜ፤ ጥያቄው በፍጹም ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን በሰው አስተሳሰብ የማይቻል መሆኑን ጠንቅቃ ብትረዳም ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር ምንም እንደሌለ ስላመነች ሰማያዊ ጥያቄን እሺ ብላ በእምነት እንደተቀበለች ከወንጌላዊ ሉቃስ መረዳት ይቻላል (1፡ 34-38)፡፡ ከእሺታዋ የተነሣ የቅድስት ሥላሴ ውብ ቤተመቅደስ፣ የዳግማዊ አዳም ምድራዊ ገነት፣ የመንፈስ ቅዱስ ሙሽሪት፣ የመላእክት እሀት፣ የቅዱሳን እናት እንደሆነች የቤተክርስቲያን ቅዱሳን አባቶች አበክሮ ተናግረዋል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የኖረችው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ብቻ ስለሆነ ምድራዊ ሕይወቷን በታማኝነት፣ በታዛዥነት፣ በንጽሕናና በአምነት ስታጠናቅቅ እግዚአብሔር በነፍሷና በሥጋዋ ወደ ራሱ መውሰዱ ለእርሱ ብቻ የኖሩትንና ፈቃዱንም በታማኝነት ለመፈጸም የተጉትን ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንደሚኖሩ የገባው የተስፋ ቃል ፊጻሜ ነው፡፡

አንዳንድ ሰዎች ሰለ ነቢዩ ኤልያስና ስለሔኖክ ወደ ሰማይ መወሰድ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ የማርያምን ግን በቀጥታ የሚናገር የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ የለም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ከሁሉ በቅድሚያ የአዲስ ኪዳን ዋና ዓለማ ስለ ዓም ሁሉ አዳኝ ልደት፣ ምድራዊ ኑሮ፣ ሐዋርያዊ ተልእኮ፣ ስለስቃዩ፣ ስለሞቱ፣ ስለትንሣኤው፣ ስለእርገቱ፣ ስለመንፈስ ቅዱስ መውረድና ስለ መጀመሪያቱ ቤተክርስቲያን አመሠራረት እንጂ የመጀመሪያ የክርስቶስ ተከታዮች ስለሆኑት ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ስለ ሐዋርያቶች ልደት፣ ሞት፣ ትንሣኤና እርገት መናገር አለመሆኑን ነው፡፡ አብዛኛው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ሐዋርያቶች ገና በሕይወት እያሉ ነው፡፡ ስለእነርሱ አኗኗርና አሟሟት የጻፉት የሐዋርቶች ተከታዮች የነበሩት እንደነበሩ ከገድሎቻቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ስለሆነም በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቀጥታ አልተጻፈምና ወደ ሰማይ አልተወሰደችም ብሎ ክርክር መፍጠር የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉበትን ዓላማ በትክክል ካለመረዳት የሚመነጭ ስሕተት ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ዋና ዓላማ ኢየሱስ ክርስቶስ መሲሕ የእዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምነን የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ የተጻፈ ነው እንጂ (ዮሐ 20፡ 31)፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ያደረጋቸውን ብዙ ነገሮችን ጭምር ያላካተተ (ዮሐ 21፡25) መሆኑን መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡

የተወደዳችሁ ምዕመናን 

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያናችን እመቤታችን ቅድስት ማርያም እንደ ልጇም ከሞተች በኋላ እግዚአብሔር ከነፍሷና ከሥጋዋ ወደ ሰማይ እንደወሰዳት ታምናለች፤ ታስተምራለችም፡፡ እኛም የፍልሰታ ለማርያም ጸሎት ላይ የምንሳተፍ ሁላችንም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወት የምንማረው ነገር ሁላችንም ለዓላማ የተፈጠርን መሆናችንን ነው፡፡ የተጠራንበትን ጥሪ የሚመስል፣ የሚያስከብርና የሚያስመሰግን ሕይወት ለመኖር ከተጋን እግዚአብሔር እኛም ምድራዊ ሕይወታችንን ካጠናቀቅን በኋላ ዘላለማዊ ሕይወት ወራሾች እንደሚያደርገን እናምናለን፡፡

ሁላችንንም የፍልሰታዋ በረከት ተካፋዮች ያድርገን! 

 † ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ  

ሊቀጳጳሳት ዘካቶለካውያን  

የኢትዮጵያ ካቶሊካት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዘዳንት

 

 የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ አዲስ አበባ

06 August 2023, 16:56