ፈልግ

የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ በሀይፋ ከሚገኙ የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ጋር የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ በሀይፋ ከሚገኙ የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ጋር   (Latin Patriarchate of Jerusalem)

የእስራኤሉ ፕረዚዳንት በሃገሪቷ የሃይማኖት ነፃነትን ለማስጠበቅ ቁርጠኝነቱ እንዳላቸው አረጋገጡ።

በእየሩሳሌም የሚገኙ የላቲን እና የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርኮች በሃይፋ በተካሄደው እና የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት በእስራኤል የሃይማኖት እና የአምልኮ ነፃነትን ለማስጠበቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት ባረጋገጡበት ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የእስራኤል የወደብ ከተማ በሆነችው ሃይፋ የሚገኙ በርካታ የክርስቲያን ማህበረሰብ አባላት በቅርቡ የአይሁድ አክራሪ ቡድኖች ወደ ክርስቲያናዊ ቅዱሳን ቦታዎች በተለይም ወደ ስቴላ ማሪስ ገዳም እየገቡ የሚያደርሱትን ጥቃት በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል። በነዚህ ቦታዎች እና በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ የእስራኤል ፕሬዝዳንት የሆኑት አይዛክ ሄርዞግ በሃይፋ የሚገኘውን የቀርሜሎስ ገዳም ስቴላ ማሪስን መጎብኘታቸው እጅግ ጠቃሚ ነበር። ባለፈው ነሃሴ 3/ 2015 ዓ.ም. ፕሬዝዳንት ሄርዞግ ከባለቤታቸው እና ከጥቂት የባለስልጣናት ልዑካን ጋር ያካሄዱት ይህ ጉብኝት በተፈጥሮው ግላዊ ነበር።
የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት በጉብኝታቸው ወቅት እንደተናገሩት “የሁሉንም ሃይማኖት ተከታዮችን ማክበር አለብን ፥ ከመጀመሪያው ጀምሮ በዚህ ጉዳይ ላይ ቁርጠኛ ሆነን እየሠራን እንገኛለን ፥ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ብለዋል።
ፕረዘዳንት አይዛክ ሄርዞግ አክለውም “ከቅርብ ወራት ወዲህ በቅድስት ሀገር የክርስቲያን ቤተ እምነቶች ላይ እየደረሱ ያሉ አፀያፊ ክስተቶችን አይተናል። ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የሆኑት ክርስቲያን ዜጎች በጸሎት ቦታቸው፣ በመቃብር ቦታቸው እና በጎዳናዎች ላይ ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይህ ጽንፈኛ የሆነ ያልተለመደ ድርጊት በሁሉም ረገድ ተቀባይነት እንደሌለው አምናለሁ። ይህ ድርጊት መወገድ አለበት ፥ የሃገሪቱ ፖሊስ እና ሌሎች የህግ አስከባሪ ኤጀንሲዎች ጉዳዩን በቁም ነገር ስለወሰዱት አመሰግናለሁ። እነሆ በዚህ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሰላማዊ እና ውብ ሆኖ ለኖረ ማህበረሰብ ውስጥ አሁንም ያለምክንያት የክርስቲያኑ ማህበረሰብ አባላት ስጋት ሊሰማቸው አይገባም” ብለዋል።
የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ሲያጠቃልሉ “በእስራኤል ለሚኖሩ ክርስቲያኖችም ሆነ በዓለም ዙሪያ ላሉ አማኞች የማስተላልፈው መልእክት የክርስቲያን ማህበረሰቦች ደህንነታቸው የተጠበቀ ፣ በሠላም እና በቅድስት ምድር በክብር የሚኖሩ መሆናቸውን ነው” በማለት ሃሳባቸውን ደምድመዋል። የሃገሪቱ የፖሊስ አዛዥ የሆኑት ያኮቭ ሻብታይ በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል።

የተመራጩ ካርዲናል ፒዛባላ ምስጋና

በኢየሩሳሌም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በቅድስት ምድር ያሉትን ሁሉንም የክርስቲያን ማህበረሰቦች ወክለው ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም የእስራኤል ፕሬዝዳንት እና የልዑካን ቡድኑ አባላት በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባርም ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው ፥ "በመካከላችን ያለውን የአብሮነት ውይይት እና ፍቅራችንን ለማጠናከር በጋራ መስራት አለብን" ብለዋል። በማከልም “የምንኖረው በአንድ ቦታ እና ጎን ለጎን ነው ፥ እናም በሰላም መኖር እንደሚገባን እንዱሁም የወደፊት ሕይወታችንን በጋራ መገንባት እና መደጋገፍ አለብን” በማለት በአጽንኦት ተናግረዋል።
ፕሬዘዳንት ሄርዞግ በበኩላቸው “አዎ ፥ ለሁሉም ሃይማኖቶች አስፈላጊው ነገር ይህ ነው” ሲሉ ፓትርያርኩም “ሁላችንም የአንድ አምላክ ልጆች ነን” በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
በእስራኤል የሚገኙ የዕብራይስጥ ካቶሊኮች ካህን የሆኑት አባ ፒዮትር ዜላዝኮ ስለተካሄደው ስብሰባ በቫቲካን ሬዲዮ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ፥ “የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት በክርስቲያኖች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን እና ችግሮችን ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠኝነትን ያሳያል። ከመንፈሳዊ መሪዎች እና ከተለያዩ ቤተ እምነቶች ተወካዮች ጋር በመገናኘት ያደረጉት ይህ ጉልህ እርምጃ የመቻቻል፣ የውይይት እና የአንድነት መንፈስን ለመጠበቅ የጋራ ቁርጠኝነትን የሚያጎላ ነው” ብለዋል አባ ዜላዝኮ። አክለውም “የእስራኤል ፖሊስ ዋና ኮሚሽነር የሆኑት ያኮቭ ሻብታይ በዚህ ውይይት ላይ መገኘታቸው የተስፋ ስሜትን ያመጣል ፥ ይህም የሰላም፣ የጋራ መግባባት እና ስምምነትን መሰረት ያደረገ አብሮ መኖርን ለመፍጠር አወንታዊ እርምጃን ያሳያል” በማለት አባ ዜላዝኮ ሃሳባቸውን ሲያጠቃልሉ ፥ "የተሻለ ሁሉን አቀፍ እና ስምምነት ያለው ማህበረሰብ ለመፍጠር ጥረቱ መቀጠል እንዳለበት እና በስቴላ ማሪስ ገዳም የተደረገው ጉብኝት ችግሮችን ለማሸነፍ እንዲሁም የበለጠ ሠላማዊ እና መግባባት ወዳለበት የወደፊት መንገድ ለማምራት የሚደረግ የጋራ ቁርጠኝነት ምልክት ነው” ብለዋል።
 

14 August 2023, 14:37