ፈልግ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን  

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለአገር ሰላምና ደኅንነት ጾምና ጸሎት እንዲደረግ መልዕክት አስተላለፈች

ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለአገራችንና ለሕዝቦቿ ሰላምና ደኅንነት ጾመ-ፀሎት እንዲደረግ ለካቶሊካውያን ምዕመናን እና በጎ ፊቃድ ላላቸው ሁሉ የተላለፈ መልዕክት፥

ጌታ ሆይ ፀሎታችንን ስማ፤ ጩኸታችንም ወዳንተ ይድረስ፤በመከራችን ቀን ፊትህን ከእኛ ወዲያ አትመልስብን!  አሜን።

“ኑና እንዋቀስ” ይላል ጌታ፥ “ኃጢአታችሁ እንደ ዓለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤

እንደ ደም ቢቀላም እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል።” (ኢሳ 1፤18)

ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ሕዝብ ያላት ጥንታዊትና ታሪካዊት ሀገር ነች። የሰው ልጅ መገኛ ብለን የምንኮራባት፣ የተለያዩ ህዝቦችና የተለያዩ እምነቶች የሚገኙባት የአብሮነት ምሳሌ ሆና የቆየች የምንወዳት ሀገር ናት። በረከቶቿ ብዙ ቢሆኑም ሀገራችንና ሕዝቦቿ በተለያዩ ጊዜያት ከጦርነት አዙሪት መውጣት አልቻንም፤ ከድህነትና ጉስቁልና መላቀቅ አቅቶናል። አረጋውያን፣ እናቶችና ህፃናት ከመከራ ጩኸት ነፃ መውጣት አልቻሉም። የሕዝባችን ደም በከንቱ ይፈስባታል፤ ነፍስም በተማዕጽኖ ወደ አባቷ ትጮሃለች። ብዙ ወጣቶቻችን በየጦር ሜዳው ተሰውተዋል። በሀገራችን ችግሮችን በንግግር፣ በውይይትና በእርቅ መፍታት መገለጫ ባህላችን ሆኖ እያለ ለተለያዩ ብሶቶቻችን ግን ጦርነትን እንደ አማራጭ መውሰድ ልማድ እየሆነ የመጣ ይመስላል፤ ሆኗልም።

ሀገራችን ሌሎች ሥልጣኔዎች የደረሱበት እንድትደርስ እንመኛለን፤ ይህንንም በብዙ መስኮች በተደረጉ እንቅስቃሴዎችና መሻሻሎች ለመረዳት ያስችለናል። በተቃራኒው ግን የመኖር ተስፋችን በዚያው ልክ እየደበዘዘ በፍርሃትና ተስፋ በመቁረጥ ተውጠናል። ለዚሁም ማሳያው በዘመናት ካየናቸው አስከፊ ጦርነቶች በተለይም በቅርቡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተካሄደው ጦርነት በውይይት ልዩነቶችን መፍታት ሲቻል ወደ ጦርነት ተገብቶ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ወገኖቻችን ረግፈዋል፣ ብዙዎች ቆስለዋል፣ የስነ ልቦና ጉዳትም ደርሶባቸዋል፤ ብዙዎችም ተሠደዋል፣ ብዙ ንብረትም ወድሟል። ይህ ክስተት ለዘመኑ ሥልጣኔና ዕድገት ለምትዳክር ሀገርና ሕዝብ ባይመጥናትም ዘግይቶም ቢሆን በውይይት ሠላም እንዲሰፍን መደረጉ እጅጉኑ አስደስቶናል፤ ሕዝባችንም እፎይታ አግኝቷል፤ እናቶችም ከሀዘን ስብራት አርፈዋል። ይህ የሚያመለክተው ሕዝባችን ምን ያህል ጦርነት እንዳንገሸገሸውና ኑሮውንም እንዳጎሳቆለው ማሳያ ነው። ጦርነት የመሸከም አቅማችን ተሟጧል። ሰለሆነም የአገራችን የሰላም እጦትና ጊዜውን እየጠበቀ የሚከሰተው የግጭቶች መፈራረቅ ጉዳይ በእጅጉ ያሳስበናል፤ በመሆኑም አገራችን ኢትዮጵያ ከወትሮውም በላይ ሰላም የሚያስፈልጋት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

ለሰላም እጦታችን ደግሞ ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ለመፍታትና ጠንካራ ሕዝባዊ ትስስርንም ለመፍጠር በየጊዜው የሚነሱ ብሶቶችን በውይይት መፍታት ከመቸውም በላይ በጣም አስፈላጊ መሆኑን እንረዳለን። በተቃራኒው ግን በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች የሚደረጉ የጦርነት እንቅስቃሴዎች ያለፈ ታሪካችንን ቆም ብለን እንድናስብ ይጋብዙናል። ከጦርነት ያተረፍነው ነገር ቢኖር የሕይወት መስዋዕትነትና ውድመትን እንዲሁም ቀዬን ጥሎ መሰደድ ነው። ለዚህም ምክንያታችን አሁንም ችግሮቻችንን በብልሃት፣ በጥበብ፣ በጸሎትና በመነጋገር እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን በመስማት መፍታት አለመቻላችን ነው። በፅሞናና በጥንቃቄ መደማመጡ ቀርቶ መቆጣጠር ወደማንችላቸው …ፍልሚያ ውስጥ ገብተናል። በሰዎች መሃከል ያለው የአስተውሎት ተግባቦቶች በችግር ላይ ወድቋል፤ የፈለግነውን ብቻ የምንፈበርክበትና መቆጣጠር የማንችለውን ወደጐን የምንልበት አዲስ የሕይወትና የተግባቦት ዘይቤ ‹ፈብርከናል›። (ፍራንቸስኮስ፣ ፊራቴሊ ቱቲ ቁ. 49)።

ስለዚህ አውዳሚና አስከፊ እንቅስቃሴዎቻችንን ቆም ብለን በማሰብ ራሳችንን እናውጣ፤ ዳግም ሞትና ውድመት ውስጥ መግባቱ ይቅርብን። ጦርነት ለየትኛውም የፖለቲካዊ ችግር መፍትሔ ሆኖ አያውቅም። ፖለቲካዊ ችግር መፈታት ያለበት መከባበር ባለበት የጋራ ጥቅም በሚያስቀድም ሁኔታ በሚደረግ የፖለቲካ ውይይት ነው። ውይይቱም ብሶት የወለዳቸውን ምሁራንን፤ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ ወጣቶችንና ሴቶችን ጭምር ያካተተ ቢሆን የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን ሙሉ እምነታችን ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ የመንግሥት የፖለቲካ ፈቃደኝነት በጣም አስፈላጊ እንደሚሆን ይሰማናል። ምክንያቱም መንግስት ከሁሉም በላይ እኛ በብዙ መልኩ ወንድማማችና እህትማማች የሆነውን ኢትዮጵያውያንን በጋራ የማምጣት አቅም አለው ብለን እናምናለን።

ስለዚህም የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ በሀገራችን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ባስቸኳይ እንዲቆምና በውይይት ችግሮች እንዲፈቱ መንግስትንና ተፋላሚ ወገኖችን አጥብቆ ይማፀናል። በዚህም በፍልሰታ ጾም ጸሎት ወቅት ልቦናችንን ወደ እግዚአብሔር እንድንመልስ፣ ስለ ሰላም፤ ስለ ፍትህ፤ ስለ ውይይት እንድንጸልይ ለምዕመኖቻችንና በጎ ፊቃድ ላላቸው ወገኖቻችን ሁሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

እግዚአብሔር ለሀገራችንና ለሕዝቦቿ ሰላምን ያውርድልን። አሜን!

 

08 August 2023, 17:31