ፈልግ

የነሐሴ 07/2015 ዓ.ም ዘክረምት 7ኛ እለተ ሰንበት ቅ. ወንጌል እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ የነሐሴ 07/2015 ዓ.ም ዘክረምት 7ኛ እለተ ሰንበት ቅ. ወንጌል እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ  

የነሐሴ 07/2015 ዓ.ም ዘክረምት 7ኛ እለተ ሰንበት ቅ. ወንጌል እና የቅ. ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ምንባባት

1.      1ቆሮ 8፡ 1-13

2.     1ጴጥ 4፡ 1-5

3.     ሐዋ 26፡ 1-23

4.    ማቴ 12፡ 38-50

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ማረጋገጫ ምልክት ስለ መሻት

ከዚያም አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንና ፈሪሳውያን፣ “መምህር ሆይ፤ ከአንተ ታምራዊ ምልክት ማየት እንፈልጋለን” አሉት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይጠይቃል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ ዐንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ቈየ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በምድር ሆድ ውስጥ ይቈያል። የነነዌ ሰዎች በፍርድ ዕለት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው  ፈርዱበታል፤ እነርሱ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና። እነሆ፤ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።

በፍርድ ዕለት የደቡብ ንግሥት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና። እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ። “ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ ዕረፍት ለማግኘት ውሃ በሌለበት ደረቅ ቦታ ይንከራተታል፤ የሚሻውን ዕረፍት ግን አያገኝም። ከዚያም፣ ‘ወደ ነበርሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል። ከዚያም ይሄድና ከራሱ የባሱ ሌሎች ሰባት ክፉ መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ እነርሱም ሰውየው ውስጥ ገብተው ይኖራሉ። የዚያም ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድም ላይ እንዲሁ ይሆንበታል።”

የኢየሱስ እናትና ወንድሞች

ኢየሱስ ለሕዝቡ ሲናገር ሳለ፣ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር። አንድ ሰውም፣ “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው። ኢየሱስም፣ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰለት። በእጁም ወደ ደቀ መዛሙርቱ እያመለከተ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው፤በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ ወንድሜ፣ እኅቴና እናቴም ነው።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

 

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል በኢየሱስ እና በጊዜው በነበሩት የሕግ መምሕራንና ፈሪሳዊያን መካከል የተደረገውን ውይይት ያቀርብልናል። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምልክት እንዲያሳያቸው የጠየቁት የሕግ መምሕራንና ፈሪሳውያን ናቸው። ኢየሱስ ብዙ ምልክቶችን አድርጓል፤ ለምጻሙን ፈወሰ (ማቴ 8፣1-4)፣ የመቶ አለቃው አገልጋይ ፈውሷል (ማቴ 8፣5-13)፣ የጴጥሮስ አማች ፈውሷል (ማቴ 8፣14-15)፣ የታመሙትንና የከተማይቱ ሰዎች ፈውሷል (ማቴ 8፡16)፣ ማዕበሉን ጸጥ አድርጓል (ማቴ 8፣23-27)፣ አጋንንትን አስወጥቷል (ማቴ 8፣28-34)፣ ደንቈሮውና ዲዳ የነበረውን ሰው ፈውሷል (ማርቆስ 7፡31-37)፣ ዐይነ ሥውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ፈውሷል (ዮሐንስ  9፡1-12)፣ በቤተ ሳይዳ የተደረገው ፈውስ (ዮሐንስ 5፡1-14)፣ በቤተ ሳይዳ የተፈወሰው ዐይነ ስውር (ማርቆስ 8፡22-25)፣ ኢየሱስ ዐይነ ስውሩን በርጤሜዎስን ፈውሷል (ማርቆስ 10፡46-52)፣ የመቶ አለቃው አገልጋይ ፈውሷል (ሉቃስ 7፡1-10)፣ ኢየሱስ የመበለቲቱን ልጅ ከሞት አስነስቷል (ሉቃስ 7፡11-15)፣ ኢየሱስ አንዲት ጐባጣ ሴት በሰንበት ቀን ፈውሷል (ሉቃስ 13፡ 10-17) ወዘተ ... ሌሎች ብዙ ተአምራትን አድርጓል። ሕዝቡም እነዚህን ምልክቶች የያዌ አገልጋይ በሆነው በኢየሱስ አማካይነት እንዲያውቁ ተደረጉ “እነሆ፤ የመረጥሁት፣ የምወድደውና በእርሱ ደስ የሚለኝ አገልጋዬ፣ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍትሕን ያውጃል” (ማቴ 8፣17፤ 12፣17-21) የሚለው ቃል ተፈጻሚ ሆነ። ነገር ግን አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንና ፈሪሳውያን ኢየሱስ ቀደም ሲል የሰጣቸውን የብዙ ምልክቶች ትርጉም ሊገነዘቡ አልቻሉም። የተለየ ነገር ፈለጉ።

“ከዚያም አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንና ፈሪሳውያን ‘መምህር ሆይ፤ ከአንተ ታምራዊ ምልክት ማየት እንፈልጋለን’ አሉት” (ማቴዎስ 12፣ 38) ኢየሱስ ተአምር እንዲያደርግላቸው ይፈልጋሉ ስለዚህ እነሱ ባሰቡት እና በፈለጉት መሰረት ኢየሱስ ከእግዚአብሔር የተላከ መሆኑን ወይም አለመሆኑን አረጋግጠው መመርመር ፈለጉ። ሊያዩት ይፈልጋሉ። ኢየሱስን ከመሲሐዊ ዕቅዳቸው ጋር ለማስማማት እንዲችሉ ለእነርሱ መመዘኛዎች ማስገዛት ይፈልጋሉ። በእነርሱ ውስጥ ሊኖር የሚችል ውይይት ስሜት አልነበራቸውም። ኢየሱስ ስላደረገው ነገር ምንም አልተረዱም።

በቅዱስ ወንጌል አንደተጠቀሰው የኢየሱስ መልሰ የሚከተለው ነበር “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይጠይቃል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ዮናስ ምልክት በስተቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ በዓሣ ዐንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ቈየ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በምድር ሆድ ውስጥ ይቈያል” (ማቴዎስ 12፡39) በማለት ይመልሳል። ኢየሱስ የሐይማኖት መሪዎች ላቀረቡት ጥያቄ አልተገዛም፣ ምክንያቱም ከልብ የቀረበ ጥያቄ አይደለምና። ጠማማና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይፈልጋል፤ ነገር ግን ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም በማለት ይመልሳል። እነዚህ ቃላት የሕግ መምህራን እና  ፈሪሳውያንን በተመለከተ በጣም ጠንካራ ፍርድ ያመለክታሉ። “ለልጆቿ አልራራላቸውም፤ የምንዝርና ልጆች ናቸውና”

 በማለት እነርሱ ታማኝ ያልሆነችና የአመንዝራ ሚስት ልጆች ናቸው ብሎ በመክሰስ ሕዝቡን የሚወቅሰውን የሆሴዕን ቃል አስተጋብተዋል (ኦሴ 2፡4)። የማርቆስ ወንጌል እንደሚገልጸው ኢየሱስ የፈሪሳውያንን ጥያቄ በሰማ ጊዜ “እርሱም በመንፈሱ እጅግ በመቃተት፣ “ይህ ትውልድ ምልክት የሚፈልገው ለምንድን ነው? እውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ምልክት አይሰጠውም!” (ማር 8፡12) በማለት መለሰ። ምናልባት በዚህ ታላቅ ዓይነ ስውርነት ፊት በመጸየፍ እና በማዘን ይሆናል ይህንን የተናገረው። ምክንያቱም ዓይናቸውን መግለጥ በማይፈልጉ ሰዎች ፊት ቆንጆ ምስል ማስቀመጥ ምንም ፋይዳ የለውም። አይናቸውን የጨፈኑ ማየት አይችሉምና! የሚሰጣቸው ምልክት የዮናስ ምልክት ብቻ ነው።

“እነሆ፤ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ” (ማቴዎስ 12፣41)።  ኢየሱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሲያመለክት “ዮናስ በዓሣ ዐንበሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ቈየ፣ እንዲሁ የሰው ልጅ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በምድር ሆድ ውስጥ ይቈያል” በማለት ይናገራል። ይህ ማለት ደግሞ ብቸኛው ምልክት በተከታዮቹ እስከ ትንሣኤ ድረስ የሚዘልቅ የኢየሱስ ትንሣኤ ነው። ይህ የሕግ መምህራን እና ለፈሪሳውያን ወደፊት የሚሰጠው ምልክት ነው። ሥቃይ እና የመስቀል ሞት የፈረዱበት ኢየሱስ እግዚአብሔር እንደሚያስነሳው እና በእርሱ የሚያምኑትንም በብዙ መንገድ እንደሚያስነሳ የሚናገሩት ነገር ይገጥማቸዋል። ለምሳሌ የኢየሱስን ትንሣኤ በማወጅ ከባለሥልጣናት ጋር ለመጋፈጥ ድፍረት የሚያገኙ “ያልተማሩ ሰዎችን” በሐዋርያት ምስክርነት ያስነሣል (የሐዋርያት ሥራ 4፡13)። ሕይወትን የሚለውጠው ምስክርነቱ ነው! ተአምራቱ አይደለም፡- “የነነዌ ሰዎች በፍርድ ዕለት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው  ይፈርዱበታል፤ እነርሱ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና” ። የነነዌ ሰዎች በዮናስ ስብከት ምስክርነት ምክንያት ተለውጠው የሕግ መምህራንንና የፈሪሳውያንን ክህደት አውግዘዋል። "እነሆ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ”።

“እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ” (ማቴዎስ 12፣42)። የነነዌ ሰዎች መለወጥ የሚያመለክተው ማጣቀሻ እና የንግሥት ሳባ ታሪክን ያስታውሳል። "በፍርድ ዕለት የደቡብ ንግሥት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና። እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ”። የሰሎሞንን ጥበብ የተገነዘበችው የንግሥት ሳባ  ታሪክ ይህ ስሜት መጽሐፍ ቅዱስ በዚያን ጊዜ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ ያሳያል። እርስ በእርሱ የተገናኘ ነገር እንዳለ ያሳያል። ዋናው የትርጓሜ ህግ ይህ ነበር፡ "መጽሐፍ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ በራሱ ተብራርቷል"። እስካሁን ድረስ ይህ ለመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ደንቦች አንዱ ነው፣ በተለይም የእግዚአብሔርን ቃል በጸሎት መንፈስ ለማንበብ።

የተከበራችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች እኛ የሚያስፈልገን እንደ ፈሪሳውያን ተአምር ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ መታመን ነው፡፡ ይህ ከሌለን ከእግዚአብሔር ለመራቅ ቅርብ ነን በእኛ ላይ የእምቢተኝነት መንፈስ ይነግሳል፡፡ እምቢተኝነት ደግሞ ከእግዚአብሔር ያርቀናል፣ ከእግዚአብሔር መራቅ ደግሞ የእግዚአብሔርን ጸጋና በረከት የእርሱን ቸርነትና ምህረት በማጣት ሕይወታችን አሰቃቂና በመከራ የተሞላ ነው የሚሆነው፡፡ ሕይወታችን የተድላና የደስታ የጸጋና የበረከት የሰላምና የምህረት ሕይወት ሊሆን የሚችለው በእግዚአብሔር ላይ እምነት ሲኖረንና የእርሱን ፈቃድ ስንፈጽም ብቻ ነው፣ በዚህም የእግዚአብሔር ልጆች አባትና እናት ወንድምና እህት የምንሆንበትን ጸጋ ሰጥቶናል በዛሬውም ወንጌል የተላለፈልን መልዕክት ይህንኑ ነው፡፡

በእግዚአብሔር ላይ እምነት የሌለው ሰው እና የእርሱንም ፈቃድ የማይፈጽም አማኝ በቤቱ ሰላምና ፍቅር ጸጋና በረከት አይኖረውም፥፥ ቤታችን ቤተሰባችን ሀብታችን ንብረታችን ልጆቻችን የሚባረኩት በእግዚአብሔር ላይ እምነት ሲኖረንና የእርሱንም ፈቃድ ስንፈጽም ብቻ ነው፥

በተጨማሪም ልክ ሐዋርያው ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ (26፡ 6) ላይ አሁንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ስለ ተስፋ ቃል በጽናት መመስከር የምንችልበትን ጸጋ የምናገኘውም በዚሁ የእምነት ጽናት ነው፥፥ ስለዚህ ሁላችንም ለዚህ ተጠርተናል በዚህ መንፈስ ተጉዘን የአባታችን የልዑል እግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ለመመስከር ተነስና በእግርህ ቁም ስለዚህ እኔን ባየህበት ነገር ለአንተም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር ትሆን ዘንድ ልሾምህ ታይቼልሃለሁና ብሎ ጳውሎስን እንዳነሳሳው እኛንም በዚሁ መንገድ  ግብዣውን ያቀርብልናል፥፥

ለዚሁ ማረጋገጫ ይሆነን ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኃለሁ ያለው ለደቀ መዛሙርቱ ብቻ ሳይሆን በእምነት ለሚለምኑት ሁሉ የተሰጠ ተስፋ ነው፡፡ ይሁንና ከፈጣሪያችን የምንለምነውን ሁሉ ለማግኘት በእኛ በሰዎች ዘንድ የሚፈለግ አንድ ቅድመ ሁኔታ አለ ይህም በእግዚአብሔር ላይ ሙሉ እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል፥፥ ጌታም አምነን የምንለምነውን ሁሉ ይፈጽምልናል፡፡ በዚህ መንፈስ ኖረን ለመንግስቱ እንድንበቃ በጸጋው ይርዳን። አሜን!

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን ቫቲካ

 

12 August 2023, 15:32