ፈልግ

ከወጣት አርቲስቶች አንዷ የሆነቿ ሊም ሱንግ ዩን 'የመሆን ሪትም' ስራዋን እየገለጸች ከወጣት አርቲስቶች አንዷ የሆነቿ ሊም ሱንግ ዩን 'የመሆን ሪትም' ስራዋን እየገለጸች 

ወጣት የኮሪያ አርቲስቶች ሃይማኖታዊ የጥበብ ስራዎች አማካኝነት ላውዳቶሲን ዓላማ እያስተማሩ ነው ተባለ

የደቡብ ኮርያዋ ሴኦል ከተማ ሃገረ ስብከት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ኤንሳይክሊካል ላውዳቶ ሲ' አስተምርሆ የሆነውን ‘የጋራ ቤታችንን’ እንዴት መጠበቅ እንደምንችል የሚያብራራ በአስራ አንድ ወጣት ኮሪያውያን አርቲስቶች የተዘጋጀ የስዕል አውደ ርእይ በሚዮንግዶንግ የስዕል ማሳያ (ጋላሪ) ልዩ ኤግዝብሺን አዘጋጀ።

   አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በደቡብ ኮሪያው ሲኦል ሃገረ ስብከት የተዘጋጀ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ኢንሳይክሊካል ላውዳቶ ሲ' በሚል መሪ ቃል የ11 ወጣት ኮሪያውያን አርቲስቶችን ሥራ የሚያሳይ 1898 የተባለ የሥዕል አውደ ርዕይ በሚዮንግዶንግ የስእል ማሳያ ከሃምሌ 5-13 2015 ዓ.ም. ድረስ እየታየ ይገኛል።
ወጣቶቹ የደቡብ ኮሪያ አርቲስቶች ስለ ላውዳቶ ሲ' በዚህ ሃይማኖታዊ የሥነ ጥበብ ትርኢት “ስለ የጋራ መኖሪያችን ውይይቶች” በሚል ርዕስ ለመግለፅ ጥረት አድርገዋል።
ሥዕሎችን ፣ ገላጭ የሆኑ ሥዕላዊ ሥራዎችን ፣ የመስታወት ላይ ሥዕሎችን እና ጽሁፋዊ ሥዕሎችን ያካተተው የተለያዩ የጥበብ ሥራዎች ለሕዝብ በነፃ እየታዩ ናቸው። 11ዱ አርቲስቶች ከሁለት ዓመት በፊት በ‘ጋለሪ 1898’ በተካሄደው እና “የወጣት አርቲስቶች ሃይማኖታዊ የጥበብ ሥራ ውድድር” በተባለው የሥዕል ውድድር ላይ ተሳትፈው አሸናፊዎች ሆነው ነበር።
አርቲስቶቹ ምድራችንን ወይም 'የጋራ ቤታችንን' ስለመጠበቅ እና ከሁሉም ፍጥረታት ጋር ተስማምተው ስለ መኖር የሚናገረውን ላውዳቶ ሲ' አስተምህሮ በማንበብ እና በማሰላሰል ነው የተነሳሱት። 'ስለ የጋራ ቤታችን የሚደረጉ ውይይቶች' የሚለው ርዕስም ከላውዳቶ ሲ ሶስተኛ አንቀጽ የተቀነጨበ ነው ፥ ይህም ሶስተኛ አንቀጽ “ይህን ኢንሳይክሊካል የምጽፈው ስለጋራ ቤታችን ከሁሉም ሰው ጋር ለመነጋገር ነው” የሚል ነው።

የምክትል ሊቀ ጳጳሱ መልእክት

የሴኡል ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ምክትል የሆኑት ጳጳስ ቤኔዲክቶስ ሶን ሄ-ሶንግ ለወጣቶቹ አርቲስቶች 'እንኳን ደስ አላችሁ' በማለት ፥ “እናንተ ወጣት አርቲስቶች ፥ በውስጣችሁ ያለውን መልካም ነገር ስላካፈላችሁን እናመሰግናለን” ብለዋል። “በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ኢንሳይክሊካል ተነሳስታችሁ እና ይሄንንም ወደ ጥበብ ሥራ የመቀየራችሁ ዕውነታ ካህናት በቅዳሴ ሥነ ስርዓት ላይ ከሚያደረጉት ስብከት ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህም በጥበብ ሥራዎች በኩል በእግዚአብሔር የተፈጠረውን ‘ውበት’ ለማሰላሰል እና መልእክት ለማስተላለፍ ነው” በማለትም አስረድተዋል።
“በእግዚአብሔር የተፈጠረውን ዓለም አተኩረን ስንመለከት ውበቷን ለይተን ማወቅ እንችላለን። አካባቢን በሚገባ መንከባከብ የተፈጥሮን ውበት መግለጥ ነው” በማለት አቡነ ቤነዲክተስ ሶን ተናግረዋል። በማስከተልም ወጣቶቹን የኪነጥበብ ባለሙያዎችን “የእናንተ ስራ እግዚአብሔር በተፈጥሮ ላይ ያስቀመጠውን ውበት መግለጥ ነው በሚል ስሜት የጥበብ ስራዎችን እንዲሰሩ” አሳስበዋል።

የጎብኝዎች የተሳትፎ ፕሮግራም

ኤግዚቢሽኑ የጎብኚዎች ተሳትፎ ፕሮግራምንም ያካትታል። በ‘የጋራ ቤት’ በተሰኘ ፕሮግራም አማካኝነት ጎብኝዎች ወይም ተመልካቾች በሚሰጣቸው የተሳትፎ ወረቀቶች ላይ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን እንስሣት እንዲስሉ ይጋበዛሉ።
በ ‘ከአርቲስት ጋር ውይይት’ በሚባለው ክፍለ ጊዜም ፥ በአንድ ወጣት አርቲስት የሚመራ በድምጽ የታገዘ መመሪያ ተመልካቾች ስለ አጠቃላይ ስራው ትርጓሜ እንዲሰሙ ያስችላቸዋል። ይሄም ፕሮግራም በሳምንቱ ቀናት ላይ ከቀኑ 8 ሰዓት እንዲሁም በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ደግሞ ከቀኑ 10 ሠዓት ላይ ይካሄዳል።
 

18 July 2023, 20:55