ፈልግ

ወጣት ባርቶዝ ፕላካክ ፥ ሊዝበን (ሃምሌ 7 2015 ዓ.ም.) ወጣት ባርቶዝ ፕላካክ ፥ ሊዝበን (ሃምሌ 7 2015 ዓ.ም.) 

የአሜሪካ ወጣት መንፈሳዊ ተጓዦች ሊዝበን ላይ ለሚካሄደው የዓለም ወጣቶች ቀን እየተዘጋጁ ነው።

አሜሪካ ሃምሌ 25/ 2015 ዓ.ም. የሚጀመረውና ለአንድ ሳምንት በሚቆየው “ማርያም በፍጥነት ተነስታ ሄደች” በሚል መሪ ቃል በሚከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን ዝግጅት ላይ ከሚሳተፉት አምስት ታላላቅ ልኡካን መካከል አንዷ ነች። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስም ወደ ሊዝበን በሚያደርጉት ሃዋሪያዊ ጉዞ ወቅት ወጣቶቹን መንፈሳዊ ተጓዦች ከሃምሌ 27 እስከ 30 ባለው ቀን እንደሚያገኟቸው ይጠበቃል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከ1,300 የአሜሪካ ቡድኖች የተውጣጡ ከ28,600 በላይ ወጣቶች ወደ ሊዝበን ለ37ኛው የዓለም ወጣቶች ቀን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ሊጓዙ ነው። ይህ የአሜሪካ ልኡክ በዝግጅቱ ላይ ከሚሳተፉት አምስት ትላልቅ ልኡካን መካከል አንዱ ሲሆኑ የተመዝጋቢ ቁጥሮች አሁንም እየጨመረ መሆኑን የአሜሪካ ጳጳሳት መግለጫ ገልጿል።
አሁን ወደ ሊዝበን ያቀኑት መንፈሳዊ ነጋዲያኑ በ2011 ዓ.ም. በፓናማ በተካሄደው የዓለም ወጣቶች ቀን ከተሳተፉት የአሜሪካ ወጣቶች በእጥፍ ይበልጣል። በ 2008 ዓ.ም. በክራኮው ፖላንድ የተደረገው የዓለም ወጣቶች ቀን አሜሪካ 40,000 ተሳታፊዎችን በማሳተፍ ሪከርዱን ይዛለች።
ከሌሎች 60 የአሜሪካ ጳጳሳት ጋር ወደ ሊዝበን የሚጓዙት እና በምእመናን ፣ በጋብቻ ፣ በቤተሰብ ሕይወት እና በወጣቶች የጳጳሳት ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው የሚያገለግሉት ጳጳስ ሮበርት ባሮን እንደገለጹት “ሀገራችን ይህንን መንፈሳዊ ንግደት በጉጉት ትጠብቃለች” ብለዋል።

ከኢየሱስ ጋር ወሳኝ የሆነ ግንኙነት

እንደ ኤጲስ ቆጶስ ባሮን ገለጻ ፥ ዝግጅቱ ለወጣቶች ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እና ከዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን ጋር ጉልህ የሆነ ግንኙነት የሚፈጠርበት አስደናቂ አጋጣሚ ነው ይላሉ። ብጹእነታቸው በማከል
“እንዲሁም ቅዱስ አባታችን እና የቤተክርስቲያኑ አመራሮች በዝግጅቱ ላይ የተገኙትን ወጣቶች ለማዳመጥ ፣ ለማስተማር እና በወንጌል አስተምርሆ ለማቅናት እና በመጨረሻም በዓለም ላይ በሚመላለሱበት ጊዜ ለአገልግሎት እና ተልእኮ የሚልኩበት እድል የሚያገኙበት ጊዜ ነው” ብለዋል።
የአሜሪካ መንፈሳዊ ነጋዲያን በዓለም የወጣቶች ቀን በሚከበርበት ሳምንት በሊዝበን ዙሪያ ባሉ አጥቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በመኖሪያ ቤቶች እና ሆቴሎች ዉስጥ የሚያርፉ ሲሆን ፥ በቆይታቸውም በጸሎት እና በቅዳሴ ፣ መንፈሳዊ ትምህርቶችን በመከታተል ፣ ኮንሰርቶችን በመሳተፍ ፣ ውይይቶችን በማድረግ ፣ የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት እና ከዓለም ዙሪያ ከመጡ ወጣቶች ካሉ ጋር በመገናኘት ተሳትፎ ያደርጋሉ። ከ35 የሚበልጡ የአሜሪካ ጳጳሳት “ተነስ!” በሚል መሪ ቃል የሚሰጠውን ዕለታዊ የሃይማኖት ትምህርት መርሃ ግብሮችን በማስተባበር መሪ ጳጳሳት ሆነው ያገለግላሉ።
የአሜሪካ ጳጳሳት ጉባኤ ሃምሌ 26/ 2015 ዓ.ም. ለሁሉም የአሜሪካ ነጋዲያን (መንፈሳዊ ተጓዦች) በሊዝበን በሚገኘው ‘ዳ ኩንታ ዳስ ኮንቻስ’ ፓርክ ብሔራዊ የነጋዲያን ስብሰባ ለማድረግም እንዳቀደ ለማወቅ ተችሏል። በዕለተ ቀኑም ከሚቀርበው ሙዚቃ ዝግጅት እና ከወጣቶች ምስክርነት በኋላ ጳጳስ ባሮን የመክፈቻ ንግግር ያደርጉና ከጳጳስ ኤድዋርድ ጋር ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን መነቃቃት ተነሳሽነት አካል በመሆን የተቀደሰ ጊዜውን ይመራሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሃምሌ 27 መንፈሳዊ ነጋዲያኑን ይቀላቀላሉ

የሊዝበኑ የዓለም ወጣቶች ቀን ሃምሌ 25 2015 ዓ.ም. የሚጀመር ሲሆን ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ደግሞ ሃምሌ 27 ከመንፈሳዊ ነጋዲያኑ ጋር ተገናኝተው በከተማው መሃል በሚደረግ የእንኳን ደህና መጣችሁ ሥነ ሥርዓት ላይ ይገኛሉ ትብሎም ይጠበቃል። ሃምሌ 28 የመስቀል ማረፊያ የጽሎት ሥነ ስርዓቱን በመምራት እንዲሁም ‘በጃርዲም ቫስኮ ዳ ጋማ’ የተወሰኑ ወጣቶችን ኑዛዜ ያስገባሉ። በነጋታው ሃምሌ 29 የሚደረገውን የጸሎት መርሐ ግብር በመምራት ከታመሙ ወጣቶች ጋር የመቁጠሪያ ጸሎት ያደርጋሉ። ቅዱስ አባታችን ሃምሌ 30 ላይ አንድ ሚሊዮን ወይም ከዚያ በላይ እንደሚሆን ከሚጠበቀው ሕዝብ ጋር በመዝጊያውን መርሃግብር በሥርዓተ ቅዳሴ ያሳርጋሉ።

ከመላው ዓለም የመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት መንፈሳዊ ነጋዲያን ከሁሉም የዓለም ማዕዘናት በፖርቱጋሏ ሊዝበን ከተማ በሚከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከካናዳ የሚመጡትን 5000 እና ከብራዚል የሚመጡ 10,000 ተሳታፊዎችን ጨምሮ አብዛኛዎቹ መንፈሳዊ ነጋዲያን ከአውሮፓ እና አሜሪካ የሚመጡ ሲሆን ፥ ከእስራኤል ፣ ፍልስጤም እና ዮርዳኖስ l 400 ፣ ከቻይና 50 እና አልፎ ተርፎም በዓመፅ እየተናጠች ካለቺው ሄይቲ 26 ነጋዲያን ይሳተፋሉ።

ከዓለም ወጣቶች ቀን በፊት በየሀገረ ስብከቶች ውስጥ የነበሩ ቀናት

የዓለም የወጣቶች ቀን እስከሚደርስ ማለትም ከሐምሌ 19 እስከ 24 ከ67,600 በላይ የሚሆኑ ከ126 ሀገራት የተውጣጡ ምዕመናን በፖርቹጋል እና በደሴቶቹ ዉስጥ በሚገኙ 17 ሃገረ ስብከቶች ‘ቀናትን በሃገረ ስብከቶች ውስጥ’ (Days In the Dioceses) እንዲለማመዱ አቀባበል የሚደረግላቸው ይሆናል። እንደ አዘጋጅ ኮሚቴው ገለጻ መንፈሳዊ ነጋዲያኑ ከ950 በላይ በሚሆኑ ቡድናት ተከፋፍለው በመኖሪያ ቤት፣ በአድባራት፣ በትምህርት ቤቶች እና በሕዝብ መገልገያ ተቋማት ውስጥ ይቆያሉ።
ወጣቶቹ መንፈሳዊ ነጋዲያን ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን፣ ከሕዝቡና ከአካባቢው ጋር ትውውቅ የሚያደርጉ ሲሆን ፥ እያንዳንዱ ሀገረ ስብከትም አምስት ዋና ዋና ቁም ነገሮችን ያማከለ ማለትም የእንኳን ደህና መጣችሁ ፣ የመገኘት ፣ የተልእኮ ፣ የባህል እና የሽኝት መርሐ ግብሮችን ያዘጋጃሉ።
 

27 July 2023, 10:52