ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለዓለም ወጣቶች ቀን ፓናማ ሲጎበኙ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለዓለም ወጣቶች ቀን ፓናማ ሲጎበኙ 

‘WorldYouthDay.com’ የተባለው ድህረ ገጽ የህብረት እና የአንድነት መድረክ ነው ተባለ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከዓለም ወጣቶች ጋር በህብረት ሲገናኙ ያለውን ክስተት ትክክለኛ የካቶሊክ ሚዲያ ሽፋን ለመስጠት እንዲሁም የዓለም ወጣቶች ቀንን አስመልክቶ መረጃን ለማሰራጨት የተዘጋጀ የዓለም አቀፉን የወጣቶች ስብስብን መንፈስ ለማቆየት ተልእኮ ያለው ድህረ ገጽ ተከፍቷል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ይህ ልዩ አላማ ያለው እና WorldYouthday.com ተብሎ የተከፈተው ድህረ ገጽ የዓለም ወጣቶች ቀንን የአንድነት መንፈስን ለመጠበቅ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በወጣቶች መካከል ያለውን ህብረት ለማበረታታት ተብሎ የተዘጋጀ የግንኙነት መድረክ ነው።
የድረ-ገጹ አዘጋጅ ዳሪዮ ሞቢኒ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከድረ-ገጹ በስተጀርባ ስላሉት ግቦች እና ለዓለም ወጣቶች ቀን ትክክለኛ የካቶሊክ ሚዲያ ሽፋን በመስጠት ላይ ስላለው ወሳኝ ሚና ተወያይተዋል።

WorldYouthday.com

የዚህ ድህረ ገጽ አጀማመር እ.አ.አ. በ 2008 አቶ ሞቢኒ እና ጓደኞቹ ለብዙ የተለያየ ዓላማ የሚውሉ ድህረ ገጾች መኖራቸውን ሲመለከቱ እነሱም ስለ ዓለም ወጣቶች ቀን ከተለያየ ምንጭ ያገኙትን መረጃን ለማሰራጨት በማሰብ የራሳቸውን ለመፍጠር አሰቡ።
አቶ ሞቢኒ እንዳብራሩት “ስለ ዓለም አቀፍ ወጣቶች ቀን ፣ ለዓለም ወጣቶች ቀን እንዴት መዘጋጀት እንዳለብን እና ከዚያም በዓለም ወጣቶች ቀን እንዴት መሳተፍ እንዳለብን በድህረ ገጹ መረጃ ሰጥተናል ፥ በዚያን ጊዜ የድረ-ገፁ ዓላማም ያ ብቻ ነበር” ብለዋል።

ራዕይን ማስፋፋት

ነገር ግን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጵጵስና ሲከሰት ፥ የድረ-ገጹ ዓላማ ከቀላል የመረጃ ድረ-ገጽነት ባሻገር በመስፋፋቱ በአዲስ ተልዕኮ በ2013 ዓ.ም. እንደገና ተሻሽሎ ቀረበ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለወጣቶች ባስተላለፉት መልእክት በመነሳሳት ዘመናዊ መንገዶችን በመጠቀም ወንጌልን በመስበክ ረገድ የድረ-ገጹ እይታ እየሰፋ ሄደ።
“የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን ታሪክ በመፃፍ እና ስላሰቡት ነገር ፣ ወጣቶች ምን ማድረግ እንዳለባቸው፣ እንዴት እንደሚሰበሰቡ ያስቀመጡትን ራዕይ በመውሰድ አጋጣሚውን በመጠቀም ጀመርን” ሲሉ አቶ ሞቢኒ ተናግረዋል።
እ.አ.አ. በ1983 ‘ዲሌቲ አሚቺ’ ተብሎ በሚታወቀው ደብዳቤያቸው ላይ የተገለጸው የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ዋና መልእክት ፥ ከአቶ ሞቢኒ እና ከቡድናቸው ጋር የሚስማማ ነበር። ደብዳቤው ወጣቶች የቤተክርስቲያኑ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ብቻ ሳይሆኑ የአሁኑዋን ቤተ ክርስቲያን እንደሚወክሉ አጽንኦት ሰጥቶ ይናገራል።
በዚህ ረገድ አቶ ሞቢኒ እንደሚገልፁት ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በደብዳቤያቸው ላይ "ወጣቶችን አንድ ላይ ማምጣት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ነገር ግን ወጣቶችን አንድ ላይ የሚያሰባስበው ደብዳቤያቸው ብቻ አይደለም ፥ የምታሰባስበው ቤተ ክርስቲያን ናት ፥ ስለዚህ ቤተክርስቲያኒቷን ‘አንቺ የወደፊቷ ቤተክርስቲያን ነሽ’ ማለት ይችላሉ” “ደብዳቤው ወጣቶቹን ወደ ለውጥ ጎዳና እንዲመጡ ለማስታወስ የተጻፈ ደብዳቤ ነበር ፥ ነገር ግን ከሁሉም በላይ አሁን በህብረተሰብ ውስጥ ትልቅ ምልክት ያመጣ መልዕክት ነው ፥ ምክንያቱም እርስዎ የወደፊቱ ቤተክርስቲያን አይደሉም ፥ እርስዎ የአህኗ ቤተክርስቲያን ኖት” በማለት አበክሮ ይናገራል።

የእምነት ‘ባንክ’

ከዚህ ሰፊ ራዕይ በተጨማሪ ይህ ድህረ ገጽ በሦስት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዘመን ውስጥ የተሰራጩትን ከዓለም ወጣቶች ቀናት ጋር የተያያዙ ታሪካዊ ይዘቶችን ፣ ምስክርነቶችን ፣ ምስሎችን ፣ ድርሳናትን እና መልዕክቶችን ወደ ሚያከማች ማህደር ባንክነት ተለወጠ።
ይህ ስብስብ ቤተክርስቲያን ለወጣቶች የምታስተላልፈውን ውብ መልእክት እና የዓለም ወጣቶች ቀናት እንዴት በህብረተሰቡ ላይ ጠቃሚ ተጽእኖ እንደሚተዉ ለማስታወስ ያገለግላል።
አቶ ሞቢኒ ይህንን ቅርስ የመጠበቅን አስፈላጊነትን በመግለፅ ፥ ይህም ትውልዱ ትክክለኛ እና ጠቃሚ ሆኖ እንዲቆይ ያደርጋል ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው ይናገራሉ።
“ይህ ሆኖ እንዲቀጥልና በዚያ መንገድ እንዲቆይ እንዲሁም ታሪኮቹ እና ጭብጦቹ እንዲጠበቁ ከዚህም ባለፈ የዓለም ወጣቶች ቀን እራሱ ከአንዱ የጳጳስ ዘመን ወደ ሌላኛው እንዲተላለፍ ማድረግ እንፈልጋለን” ብሏል።

የካቶሊክ ሚዲያ በዓለም አቀፉ የወጣቶች ቀን

አቶ ሞቢኒ በመቀጠልም የካቶሊክ ሚዲያዎች የዓለም ወጣቶችን ቀንን በመዘገብ ረገድ ያላቸውን ሚና ተወያይተዋል። ከእነዚህ ክስተቶች የሚመነጩትን ጥሬ ስሜቶች፣ የመለወጥ ታሪኮች እና ጥሪዎችን መያዝ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።
የእሳቸው ቡድን እነዚህን ሀይለኛ ታሪኮች በማካፈል እና መሳተፍ ያልቻሉትን በሚዲያ በማገናኘት ልምዱን ለሁሉም ሰው ተደራሽ በማድረግ ወጣቶችን እና ሌሎች ትውልዶችን ማበረታታት ነው።
“ለሁሉም ሰው ምስላዊ እይታን በመስጠት ስለ ክስተቱ ስሜት እንዲኖረው እንፈልጋለን ፥ ይህ ደግሞ የምናባዊ እውነታ ስሜት ብቻ ሳይሆን ፥ ከዚህ ክስተት የምናሰራጫቸው ታሪኮች ላይ የልምድ ስሜት እንዲሰማው እንፈልጋለን” ብለዋል።

ህብረት

አቶ ሞቢኒ የዓለም ወጣቶች ቀን ዋና ጭብጥ የሆነውን የኅብረት ፅንሰ-ሀሳብ ላይ አፅንዖት ሰጥቶ ተናግረዋል። ከተለያዩ አስተዳደግ፣ ባህሎች እና ቋንቋዎች የተውጣጡ ወጣቶች በአንድነት ተሰባስበው የክርስቶስ ፍቅር ምስክሮች መሆናቸውን አበክሮ ተናግረዋል።
የዓለም ወጣቶች ቀንን እንደ ጠንካራ የኅብረት ምሳሌ ገልፀው ፥ ወጣቶች መሸሸጊያ፣ ብርታት፣ ማጽናኛ እና ተስፋ የሚያገኙት በአንድነት በመጓዝ ነው ብለዋል።
“በክርስቲያናዊ ጉዞአችን ብቻችንን አይደለንም ፥ እያንዳንዳችን ማህበረሰብ አለን ፤ ከተለያየ አስተዳደግ ፣ የተለያየ ባህል ፣የተለያየ ቋንቋ ካለው ማህበረሰብ ነው የምንመጣው። ነገር ግን ለዓለም ወጣቶች ቀን የምንሰበሰበው ለዛ ብቻ አይደለም ፥ አንድ ላይ ተሰባስበን በመምጣት የተለያየ የህይወት ትግል እና ስቃይ ውስጥ ያሉ ወጣቶች የሚመሰክሩትን ታሪኮች እንሰማለን ፥ ከዚህም ርህራሄን እያገኘን ነው። ምክንያቱም ርህራሄ ማለት አብሮ መከራን ማየት ማለት ነው ፥ እናም እኛ ራሳችንን አንድ አድርገን አብረናቸው እንሄዳለን ፥ ይሄንንም አጋርነት ብለን እንጠራዋለን” በማለት አብራርቷል።

ወደ ፊት መመልከት

አቶ ሞቢኒ አክለዉም እያንዳንዱ የዓለም ወጣቶች ቀን ካለቀ በኋላ ወጣቶችን መደገፉን እና ህብረትን የሚያበረታታ መድረክ እንዲሆን እንደሚፈልጉ በመግለጽ ስለ ድህረ ገጹ የወደፊት ራዕይ አካፍለዋል።
በትክክለኛ የሚዲያ ሽፋን ሃይል ድህረ ገጹ ወጣቶችን በዓለም ዙሪያ ለማነሳሳት፣ ለማስተማር እና ለማገናኘት ይፈልጋል ፥ ይህም የአብሮነት እና የተስፋ ስሜትን ያሳድጋል ብለዋል።
“የእኛ ድረ-ገጽ ሁሉም ነገር የተገናኘ መሆኑን ዓለምን ለማስታወስ ይፈልጋል”

የዓለም ወጣቶች ቀን ዘላቂ መንፈስ

በመጨረሻም አቶ ዳሪዮ ሞቢኒ እንዳሉት ይህ ‘WorldYouthDay.com’ የተባለው ድህረ ገጽ የዓለም ወጣቶች ቀን በወጣቶች ህይወት እና በእምነት ጉዞ ላይ የሚያሳድረውን ትርጉም ያለው ተፅእኖ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ድረ-ገጹ የቤተክርስቲያንን መልእክቶች ለመጠበቅ ባለው ቁርጠኝነት እና የኅብረት እሴትን በመቀበል የዓለም ወጣቶች ቀን መንፈስን በማንፀባረቅ እና ወጣቶች በዛሬው ዓለም የክርስቶስ ፍቅር እውነተኛ ምስክሮች እንዲሆኑ በመምራት ዓለም ላይ ላሉ የካቶሊክ ወጣቶች ትልቅዝ መነሳሳት ሆኗል።
 

31 July 2023, 15:26