ፈልግ

እ.አ.አ በ2023 ዓ.ም በፖርቹጋል ሊዝቦን የሚከበረው የዓለም የወጣቶች ቀን አርማ እ.አ.አ በ2023 ዓ.ም በፖርቹጋል ሊዝቦን የሚከበረው የዓለም የወጣቶች ቀን አርማ   (AFP or licensors)

የዓለም የወጣቶች ቀን ከአጀማመሩ ጀምሮ የተከበረባቸው አገራት እና መሪ ቃላት

ከ1987 እስከ 1993 (እ.ኤ.አ.) የመጀመሪያው የዓለም የወጣቶች ቀን የተከበረው እ.አ.አ 1987 ዓ.ም በአርጀንቲና በቦነስ አይረስ ሲሆን ይህ የዓለም የወጣቶች ቀን የተከበረው “እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ” (1 ጴጥሮስ 3፡15) በሚል መሪ ቃል መካሄዱ ይታወሳል።

የእዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

እ.አ.አ በ 1989 ዓ.ም የዓለም የወጣቶች ቀን “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” (ዩሐንስ 2፡5) በሚል መሪ ቃል በስፔን በሳንቲያጎ ዴ ኮምፖስትላ ውስጥ ተካሂዷል። እ.ኤ.አ. በ 1991 ዓ.ም “እኔ የወይን ተክል ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ” (ዮሐንስ 15፡5) በሚል መሪ ቃል የዓለም የወጣቶች ቀን በፖላንድ በቼስቶቾኮቫ ተካሂዷል። እ.አ.አ 1993 ዓ.ም “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” (ማርቆስ 16፡15) በሚል መሪ ቃል የዓለም የወጣቶች ቀን  በዴንቨር፣ ኮሎራዶ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ተካሂዶ ነበር።

ከ1995 እስከ 2005 (እ.ኤ.አ.)

እ.አ.አ 1995 ዓ.ም “አብ እኔን እንደ ላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” (ዮሐንስ 20፡21) በሚል መሪ ቃል ከ5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የተሳተፉበት የዓለም የወጣቶች ቀን  በማኒላ፣ ፊሊፒንስ በሉኔታ ፓርክ መከበሩ የሚታወስ ሲሆን ይህ ክስተት በዓለም የድንቃድቅ መዝገብ በጊነስ ወርልድ ሪከርድስ መጽሐፍ ውስጥ እስካሁን ከተደረጉት እንዲህ ያለ ሕዝባዊ ቀናት ውስጥ ሕዝብ እንዲህ ተሰብስቦ ስለማያውቅ በዓለም ድንቃድንቅ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል።

እ.አ.አ 1997 የዓለም የወጣቶች ቀን “ጌታ ሆይ፤ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ (ዮሐንስ 6፡68) በሚል መሪ ቃል በፈረንሳይ በፓሪስ ተካሂዶ ነበር። እ.አ.አ 2000 የዓለም የወጣቶች ቀን “አብ ራሱ ይወድዳችኋል” (ዮሐንስ 16፡27) በሚል መሪ ቃል በጣሊያን በሮም ከተማ ተካሂዷል። እ.አ.አ 2002 ዓ.ም የዓለም የወጣቶች ቀን “በኋላዬ ሊመጣ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም በየዕለቱ ተሸክሞ ይከተለኝ” (ሉቃስ 9፡23) በሚል መሪ ቃል  በካናዳ በቶሮንቶ ተካሂዶ ነበር። እ.አ.አ 2005 የዓለም የወጣቶች ቀን “ኢየሱስን ለማየት እንፈልጋለን” (ዮሐንስ 12፡21) በሚል መሪ ቃል በኮሎን ጀርመን ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል።

እ.አ.አ 2008 ዓ.ም የዓለም የወጣቶች ቀን “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” (ዮሐንስ 13፡34) በሚል መሪ ቃል በአውስትራሊያ ሲድኒ ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት በኔድክቶስ 16ኛ እንደ ነበሩም ይታወሳል። በወቅቱ በመላው አውስትራሊያ እና ኒውዝላንድ በሚገኙ የካቶሊክ አህጉረ ስብከት በተዘጋጀው የሀገረ ስብከት መርሐ ግብር ላይ ከሁሉም አህጉራት የተውጣጡ ምዕመናን የተሳተፉበት ሳምንት ነበር።

እ.አ.አ በ2011ዓ.ም የዓለም የወጣቶች ቀን “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል?” (ማርቆስ 10፡17) በሚል መሪ ቃል በስፔን ማድሪድ ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። በወቅቱ 2,000,000 በላይ የሚገመቱ ወጣቶች በስፍራው መገኘታቸው ይታወሳል።

እ.አ.አ 2013 ዓ.ም

እ.አ.አ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የዓለም ወጣቶች ቀን በየሦስት ዓመቱ እንዲከበር ተወሰነ። እ.ኤ.አ. ከ2011 ዓ.ም ዝግጅት በኋላ የሚቀጥለው የአለም ወጣቶች ቀን ከወትሮው አንድ አመት ቀደም ብሎ ማለትም በ2013 በሪዮ ዴጄኔሮ ፣ ብራዚል “ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ” (ፊሊጵስዮስ 4፡4) በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን  እ.አ.አ. በ2014 የፊፋ የአለም ዋንጫ በብራዚል እና በ2016 በተለያዩ 12 የተለያዩ አስተናጋጅ ከተሞች ከሚካሄደው ጋር ምንም አይነት ግጭት እንዳይፈጠር ታቅዶ የተደረገ ለውጥ ነበር። የበጋ ኦሎምፒክ በሪዮ ዴ ጄኔሮ በወቅቱ ታካሂዶ ነበር። በዝግጅቱ ላይ ከ3 ሚሊዮን በላይ የካቶሊክ ወጣቶች ከአለም ዙሪያ ተገኝተው ነበር።

እ.አ.አ በ2016 ዓ.ም  “ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና” (ማቴዎስ 5፡8) በሚል መሪ ቃል የአለም ወጣቶች ቀን በፖላንድ ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ.ኤ.አ. በ2013 በብራዚል በተካሄደው የዓለም ወጣቶች ቀን መዝጊያ ላይ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ እንዳስታወቁት፣ በክራኮቫ፣ ፖላንድ፣ የዓለም ወጣቶች ቀን እ.አ.አ 2016 እንደ ሚካሄድ ማሳወቃቸው ይታወሳል። በወቅቱ በግምት ከሦስት ሚሊዮን ሰዎች በላይ መገኘታቸው ይታወሳል። በወቅቱ እ.አ.አ በሐምሌ 25/2016 በተጀመረው እና በነሐሴ 31/2016 ዓ.ም በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መሪነት በተካሄደው የመዝጊያ ስነ ስርዓት በተጠናቀቀው የአንድ ሳምንት ዝግጅት ላይ ከተለያዩ የአለም ሀገራት የተውጣጡ ወጣቶች ተሳትፈው እንደ ነበረ ይታወሳል። በወቅቱ ቀጣዩ የዓለም የወጣቶች ቀን በፓናማ በመካከለኛው አሜሪካ እ.አ.አ በ2019 ዓ.ም እንደ ሚካሄድ መገለጹም ይታወሳል። ይህ እ.አ.አ በ1919 ዓ.ም “ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ” (ሉቃስ 1፡ 30) በሚል መሪ ቃል በፓና ተካሂዶ ነበር።

በፓናማ ተካሂዶ የነበረው የዓለም የወጣቶች ቀን ማብቂያ ላይ ብፁዕ ካርዲናል ኬቨን ፋሬል ቀጣዩ የዓለም ወጣቶች ቀን በሊዝበን ፖርቱጋል እንደሚሆን መግለጻቸው ይታወሳል። እ.ኤ.አ. በነሐሴ ወር 2022 ዓ.ም እንዲካሄድ ታቅዶ የነበረው የዓለም የወጣቶች ቀን ቅድስት መንበር በየካቲት 20/2020 በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እስከ ነሐሴ ወር 2023 እንዲራዘም በጠየቀችው መሰረት እነሆ አሁን 34ኛው የዓለም የወጣቶች ቀን “ማርያም በፍጥነት ተነስታ ሄደች” (ሉቃስ 1፡39) በሚል መሪ ቃል እ.አ.አ ከነሐሴ 1-6/2023 ዓ.ም በፖርቹጋል ሌዝቦን እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

 

 

26 July 2023, 13:47