ፈልግ

በፖርቱጋል ሊዝበን የሚከበር ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በፖርቱጋል ሊዝበን የሚከበር ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን   (AFP or licensors)

የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ለብዙ አውስትራሊያውያን ወጣቶች ዓይን እንደሚከፍት ተገለጸ

በአውስትራሊያ ጳጳሳት ጉባኤ ብሔራዊ የወንጌል አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ማልኮልም ሃርት፣ በፖርቱጋል ሊዝበን ከተማ የሚከበረው ዓለም አለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በአገራቸው ለብዙ ካቶሊካዊ ወጣቶች “ዓይን የሚከፍት” እንደሚሆን ገለጹ። አቶ ማልኮልም ይህን የገለጹት ከሐምሌ 26-30/2015 ዓ. ም. ድረስ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በማስመልከት ለወጣቶቻቸው ገለጻ በሰጡበት ወቅት ነው። አቶ ማልኮልም በገለጻቸው፥ “አጋጣሚው ወጣቶች የእምነት ልምድ የሚፈልጉበት እና በሕይወታቸው ውስጥ እድገትን የሚያሳዩበት ጊዜ ይሆናል” በማለት ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሊዝበን ከተማ ወደሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል በመሄድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ካቶሊካዊ ወጣቶችን የማግኘት ዕድል በአውስትራሊያ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት እና በተለይም ለወጣቶች ወሳኝ ወቅት ነው" በማለት በአውስትራሊያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ብሔራዊ የወንጌል አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ማልኮም ሃርት መንፈሳዊ ንግደታቸው ወደ ፖርቱጋል ለማድረግ ለተዘጋጁ ከ 3,000 በላይ የአውስትራሊያ ካቶሊክ ወጣቶች ተናግረዋል።

የጳጳሳቱ ቁርጠኝነት እና ያሉ ዕድሎች

ወደ ፖርቱጋል ከሚጓዙ መንፈሳዊ ነጋዲያን ወጣቶች ጋር ፌስቲቫሉን ከሚሳተፍ በርካታ ቁጥር ካላቸው ሌሎች የጳጳሳት ልኡካን ቡድን መካከል አንዱ የሆነው የአውስትራሊያ ጳጳሳት ቡድን እንደሆነ ታውቋል። “ብጹዓን ጳጳሳቱ ያሳዩት ቁርጠኝነት በጣም አስደሳች ነው" ያሉት አቶ ማልኮም ሃርት፥ በፈስቲቫሉ ወቅት በወጣቶች እና በጳጳሳት መካከል ከፍተኛ የመማማር ዕድል ይኖራል" ብለዋል። በየሀገረ ስብከታቸው የተከፋፈሉ በቁጥርም ወደ ሰማንያ የሚደርሱ የአውስትራሊያ ወጣት ቡድኖች ወደ ሊዝበን ከተማ እንደሚሄዱ የገለጹት አቶ ማልኮም ሃርት፥ ከፌስቲቫሉ በኋላ ወጣቶቻቸው ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም፣ ወደ ሮም ጣሊያን፣ በፈረንሳይ ወደ ሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ፣ ወde ስፔን እና በፖርቱጋል ወደ ፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ንግደት እንደሚያደርጉ ገልጽዋል።

የአውታረ መረብ ላይ ግንኙነቶች

ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫሉን በሊዝበን ከሚያከብሩት ወጣቶች በተጨማሪ በሥፍራው መገኘት ለማይችሉ ወጣቶችም ጭምር አስደሳች ዕድሎች መመቻቸታቸውን የገለጹት አቶ ማልኮም ሃርት፥ እያንዳንዱ የወጣት ቡድን የሚገለገልበት የማኅበራዊ ሚዲያ ድረ-ገጽ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። የዓለም ወጣቶች ፈስቲቫሉን በተመሳሳይ ሰዓት እንዳይከታተሉት የሰዓት ልዩነት ቢያግዳቸውም በቀጣዩ ቀን ከፖርቱጋል በቀጥታ የሚተላለፈውን ዝግጅት ወጣቶች ሊመለከቱት እንደሚችሉ አስታውቀዋል። የአውስትራሊያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ “ስብከተ ወንጌል ፕላስ” የተባለውን አዲስ ድረ-ገጽ በቅርቡ ይፋ ማድረጉን አቶ ማልኮልም ገልጸው፥ በድረ-ገጽ አማካይነት ወጣቶች የፌስቲቫሉን ክስተቶች መመልከት እንደሚችሉ አስታውቀው አክለውም፥ “ወጣቶች ስልኮቻቸን በሚገባ በመጠቀም የፌስቲቫሉን መልዕክቶች ለቤተሰቦቻቸው እና ለጓደኞቻቸው እንዲያካፍሉ እንፈልጋለን" ብለዋል።

የፌስቲቫሉን ታሪኮች ለሌሎች ማጋራት

“ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ከመላው ዓለም የሚመጡ ወጣቶች አንድ ላይ የሚሰባሰቡበት አጋጣሚ ነው” ያሉት አቶ ማልኮልም፥ ወደ በዓሉ ሥፍራ የመጓዝ ዕድል ማራኪ እንደሆነ እና ነገር ግን መንፈሳዊ ንግደት በማድረግ የእምነት ጉዞ ማድረግ የበለጠ አስደሳች ነው" ብለው፥ እነዚህ ልምዶች በወጣቶች ሕይወት ውስጥ በተለይም በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ሌሎች እኩዮቻቸው ጋር ሲተዋወቁ የእምነት ልምድ ፍለጋ እና የመንፈሳዊ ዕድገት ጊዜ ይሆናሉ” በማለት ገልጸዋል። ይህ ወቅት “በአውስትራሊያ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ወሳኝ ጊዜ" ያሉት አቶ ማልኮልም፥ አገሪቱ ወደ ዓለማዊነት ያዘነበለችበት ጊዜ እንደሆነ ገልጸው፥ ምዕመናን እና የቤተ ክርስቲያን ሰዎች የሚገለሉበት ወቅት መሆኑን አስረድተዋል። “ይህ በሆነበት ጊዜ ወጣቶች አብረው ተሰብስበው በርካታ ቁጥር ያላቸውን ካቶሊካዊ ወጣቶችን ማየት፣

ያለውን ከእነሱ ጋር መካፈል፣ ታሪኮቻቸውን ማድመጥ፣ ጥረታቸውን ደስታቸውን እና ጥበባቸውን መጋራት እና ዛሬ እምነት በሕይወታቸው ውስጥ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ማሳየት አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ለዚህ ነው” ብለው፥ በሊዝበን የሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በአውስትራሊያ ውስጥ ለብዙ ካቶሊክ ወጣቶች ዓይን የሚከፍት ነው” በማለት ያላቸውን ተስፋ ገጸዋል።

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘት

“ወጣት ምዕመናን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ነው” ያሉት በአውስትራሊያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ብሔራዊ የወንጌል አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ማልኮልም ሃርት፣ "ቅዱስነታቸው ለወጣቶች በሚያስተላልፉት መልዕክት ጠንካራ በመሆናቸው ወጣቶችም አድምጠው ምላሽ ይሰጣሉ" ብለው፥ ቅዱስነታቸውን በማየት ከእርሳቸው ጋር ሰላምታ መለዋወጥ የጸጋ ጊዜ ነው” ብለዋል። ወደ ፖርቱጋል የሚደረገው መንፈሳዊ ንግደት እና ከልዩ ልዩ አገራት ከመጡ ወጣቶች ጋር መገናኘት ብርታትን እንደሚጨምር የገለጹት አቶ ማልኮልም፥ የፌስቲቫሉ ቀናት በነጋዲያኑ ልብ እና ሕይወት ውስጥ እንደሚቀሩ፥ እንዲሁም አውስትራሊያ ውስጥ ባለች ቤተ ክርስቲያን ልብ ውስጥም እንደሚኖር፥ አውስትራሊያ ካለፉት ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ከፍተኛ ተጠቃሚ እንደነበረችም አስታውሰዋል።

የአረጋውያን እና የወጣቶች ግንኙነት

ከመጪው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን አስቀድሞ እሑድ ሐምሌ 16/2015 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን እንደሚከበር ያስታወሱት አቶ ማልኮልም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአረጋውያን እና በወጣቶች መካከል ስላለው ግንኙነት አጽንኦት መስጠታቸውን እና ይህ ትስስር ሕጻናት እና ጎልማሶች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ካደረጉት የመጀመሪያ ግንኙነት አንፃር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ መጠቆማቸውን ተናግረዋል። “እነዚያ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስን በተለያዩ መንገዶች፣ በጓደኞቻቸው ወይም በእኩዮቻቸው፣ በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ወይም በቤተሰባቸው በኩል ያወቁት ቢሆንም፥ በተለይም ከአያቶች እና ከአረጋውያን ጋር መገናኘታቸው የዚያን ልምድ ጥልቀት ያጎላል” ብለዋል።

ከአረጋውያን ጋር መወያየት እና ድጋፍ መስጠት

ይህ ዓይነቱ ግንኙነት በርካታ የአውስትራሊያ ወጣቶች ትኩረት የሆነው እና በሉቃ. 1:39 ላይ “ማርያም በፍጥነት ተነስታ ሄደች” የሚለው የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ጭብጥ የተከተለ እንደ ሆነ አቶ ማልኮልም ሃርት ገልጸዋል። “ይህ ጥቅስ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን የሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በተቃረበበት በዚህ ወቅት "ወጣቶችን ከተለያዩ አረጋውያን ጋር በማስተዋወቅ እና ውይይት እንዲያደርጉ በመጠየቅ" በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና በኤልሳቤጥ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲመለከቱ አድርጎአቸዋል” ብለዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አጥብቀው ከተናገሩ በኋላ በወጣቶች እና በአዛውንት መካከል ያለው ግንኙነት በእውነት አድጓል” ያሉት አቶ ማልኮልም፥ “ይህም በአውስትራሊያ ውስጥ በተጨባጭ የሚታይ እና የበለጠ ትኩረት በመስጠት ከአረጋውያን ለሚገኝ ጸጋ እና ጥበብ ራስን ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።

22 July 2023, 15:57