ፈልግ

በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን የሚገኝ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕንጻ በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን የሚገኝ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕንጻ  

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ለአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እርምጃ ምላሽ ሰጡ

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊክ ብፁዓን ጳጳሳት በዘር ልዩነት ምክንያት ለተገለሉ ቡድኖች ትምህርትን ተደራሽ የማድረግ አስፈላጊነት በማረጋገጥ፥ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “የዘር ልዩነት ካሁን በኋላ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ መስፈርት ሊሆን አይችልም” በማለት ላሳለፈው ውሳኔ ምላሽ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሰሜን አሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ በወሰደው እርምጃ በርካታ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች እና የሰሜን አሜሪካ ካቶሊክ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ በዘር ልዩነት ምክንያት ከማኅበረሰቡ ለተገለሉት ቡድኖች የትምህርት ተደራሽነትን አስፈላጊነት በማረጋገጥ የፍርድ ቤቱን ውሳኔው ተቀላቅለዋል።

አሜሪካ ውስጥ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ የተወሰደ አዎንታዊ እርምጃ

የሰሜን አሜሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአገሪቱ በሚገኙ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም ሃርቫርድ እና ሰሜን ካሮላይና ዩኒቨርሲቲዎችን መግባት አስመልክቶ በሁለት የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሰኔ 22/2015 ዓ. በሰጠው ብይን የዘር ልዩነት ከአሁን በኋላ በዩኒቨርሲቲ መግቢያ መስፈርቶች መካከል እንደ አንድ ምክንያት ሊቆጠር እንደማይችል ገልጾ፣ ለአሥርተ ዓመታት የቆዩ የመድልዎ ፖሊሲዎችን በአወንታዊ እርምጃ መሻሩን አስታውቋል።

“ለሁሉም እኩል መብት ይሰጥ!” የሚለው አዎንታዊ እርምጃው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1960ዎቹ በሲቪል መብቶች ንቅናቄ ወቅት በአሜሪካ ፖሊሲዎች ውስጥ የተካተተ እና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተለያየ የዘር ሐረግ ያላቸውን ማኅበረሰብ ለማካተት እና የአፍሮ-አሜሪካውያንን ማኅበራዊ አቋም ለማሻሻል ዋና መለኪያ አድርገው የተሟገቱበት እንደሆነ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የእነዚህ ፖሊሲዎች ተቃዋሚዎች በምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አዎንታዊ እርምጃው የተወሰኑ አናሳ ብሔረሰቦችን በሌሎች ኪሳራ መቀበልን እንደሚያበረታታ፣ ብዙውን ጊዜ የእስያ ተማሪዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እና ፖሊሲው በራሱ አድሎአዊ እንደሆነ ተከራክረዋል። የመጨረሻ ውሳኔው ቀደም ባሉት ጊዜያት በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሁለት አጋጣሚዎች፥ የቅርብ ጊዜው በ 2016 ዓ. ም. አዎንታዊ እርምጃ ፕሮግራሞችን የሚደግፉ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች እነዚህን ክርክሮች አምነዋል።

የበርካታ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ተስፋ መቁረጥ

ውሳኔው በሁሉም የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር ሲሆን፥ የካቶሊክ ተቋማትን ጨምሮ በርካቶቹ በውሳኔው ቅር እንዳሰኛቸው በመግለጽ የዘር መድልኦ ችግርን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት እንደሚጎዳ እና በተማሪዎቻቸው መካከል ያለውን ልዩነት እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል። የካቶሊክ ኮሌጆች እና ዩኒቨርሲቲዎች ማኅበር እንደገለጸው፥ “የዳኞቹ ውሳኔ በማኅበረሰባችን ውስጥ ቀጣይነት ያለው የዘር ልዩነት ወይም ዘረኝነት የሚያስከትለውን ውጤት ችላ ያለ ነው” በማለት ገልጸዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለተቸገሩ ሰዎች ተደራሽ ማድረግ

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊክ ብፁዓን ጳጳሳት በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርትን በኅብረተሰቡ ውስጥ በጣም ለተቸገሩት ሰዎች ተደራሽ የማድረግ አስፈላጊነት አረጋግጠዋል። "ትምህርት ሁሉም ሊደርስበት የማይችል የዴሞክራሲ ስጦታ፣ ዕድል እና ጠቃሚ ገጽታ ነው” ያለው የጳጳሳቱ መግለጫ፥ በተለይም የዘር እና የጎሳ ቡድኖች እራሳቸውን ወደ ጎን እንደተገፉ ይመለከቱታል” ሲሉ በጳጳሳቱ ጉባኤ የፀረ ዘረኝነት ኮሚቴ ጊዜያዊ ሰብሳቢ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጆሴፍ ፔሪ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል። አቡነ ጆሴፍ ፔሪ በማከልም “የካቶሊክ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አስተዳደግ ምንም ይሁን ምን ትምህርት ለሁሉም ሰው የሚሆንበትን እና ተመጣጣኝ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥል ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።

የካቶሊክ ትምህርት ፈር ቀዳጅ የሆነች የቅድስት ካትሪን ድሬክሰልን ቃላት በመጥቀስ የሰሜን አሜሪካ ብፁዓን ጳጳሳት በሐዋርያዊ መልዕክታቸው ላይ፥ “በዘላቂው የፍቅር ጥሪ ልባችንን በስፋት እንክፈት” በማለት የጻፉትን ብፁዕ አቡነ ፔሪ በመግለጫው አስታውሰው፥ “እግዚአብሔርን ማገልገል እና ባልንጀራችንንም መውደድ ከፈለግን ለእነርሱ በምንሰጠው አገልግሎት የምናገኘውን ደስታችንን መግለጽ አለብን” ብለው፣ ልባችንን በሰፊው እንድንከፍት እና ያለ ምንም ፍርሃት ወደ ፊት እንድንጓዝ የሚጋብዘን ይህ ደስታ ነው” ብለዋል።

13 July 2023, 16:11