ፈልግ

ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ ፒዛባላ 

ፓትርያርክ ፒዛባላ በጄኒን የስደተኞች ካምፕ ውስጥ እየተፈጸመ ስላለው ጥቃት ተቃውሞዋቸውን አሰሙ

እስራኤል የጄኒን የስደተኞች ካምፕ ላይ እየወሰደችው ስላለው እርምጃ የተቃውሞ ድምፃቸውን ያሰሙት የኢየሩሳሌም የላቲኑ ሥርዓት ፓትርያርክ የሆኑት ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ፍልስጤማዊያን የገዛ ግዛታቸው ላይ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን የመቻላቸው ጉዳይ ቶሎ እልባት ካላገኘ አሁንም ብዙ ተጠቂዎች እንደሚኖሩ አስጠንቅቀዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“ይሄ ጥቃት የመጀመሪያው አይደለም ፥ በሚያሳዝን ሁኔታ ለመጨረሻ ጊዜም አይሆንም ፥ በሰሜን ሰማርያ በሚገኘው በጄኒን የስደተኞች ካምፕ ውስጥ በፍልስጤማዊያን ወታደሮች ላይ የእስራኤል መንግስት እየወሰደ ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ እያየን ነው” ብለዋል ፓትሪያርኩ።
ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፥ ባለፈው ሰኞ ዕለት ከተጀመረው ድንገተኛ የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ በኋላ በጄኒን የተቀሰቀሰውን ሁከት ገልፀዋል።
የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ “እነዚህ ጊዜያዊ መፍትሄዎች መሆናቸውን እናውቃለን ፥ ካምፖቹ አሁን ቢመቱም ወደፊት ያለማቋረጥ መገንባታቸው አይቀርም ፥ ስለዚህ መዋቅራዊ ችግሮች እስካልተፈቱ ድረስ ፥ በተለይም የፍልስጤም ህዝብን ክብር ፣ ነፃነት እና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጉዳይ እስካልተከበሩ ድረስ ፥ እነዚህ ከባድ ችግር የሚያስከትሉ ሁኔታዎች በሁለቱም ወገን ከብዙ ሰለባዎች ጋር መቀጠላቸው አይቀርም” በማለት አስጠንቅቀዋል።
በእየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ የወጣው ማስታወሻም በተጨማሪ እንደሚገልፀው የእስራኤል ጦር በጀኒን ላይ የፈጸመው ጥቃት ‘ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ’ ጥቃት እንደሆነ የሚያመላክት ሲሆን ‘አረመኔያዊ ድርጊቶችን’ እንዲሁም ቅዱሳን ቦታዎችን የሚያፈርስ እና የተከበረ ሕይወት ሊያገኙ የሚገባቸውንም ሰዎች ያጠፋል” ብለዋል።
ጽሑፉ አብዛኛውን ስለ ‘እስራኤል የጠብ ማጫር ጥቃትን’ በመግለጽ ፥ ይሄ ጥቃት በሚፈፀምበት ጊዜ የአካባቢው ቤተክርስቲያን እና የቤተክርስቲያን ማህበረሰብም አብሮ እንደሚመታ ይገልፃል። መግለጫው በአፋጣኝ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደረግ እና ‘ኢ ፍትሃዊ ወንጀሎች’ እንዲቆሙ በመማጸን ይጠናቀቃል።

በጄኒን የተከናወነው የእስራኤላዊያን ተልዕኮ

በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ ምክንያት ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን በሰሜናዊ ዌስት ባንክ የሚገኘውን ጄኒን የስደተኞች ካምፕ ለቀው ሸሽተዋል። እንደ አንዳንድ የዜና ዘገባዎች መሠረት ቢያንስ ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 23 ዓመት የሆናቸው 12 ታጣቂ ‘አማፂ’ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ፥ አራቱ ምናልባትም ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ናቸው ተብሏል።
የፍልስጤም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም እንደገለፀው ከሁለት ቀናት በላይ በቆየው ኦፕሬሽን ቢያንስ 120 ሰዎች መቁሰላቸውን እና ከነዚህም ውስጥ ቢያንስ 20 ያህሉ በከባድ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ብሏል። አሁንም እንደ እስራኤል ጦር አባባል ከሆነ ሁሉም ከታጣቂዎች ጋር የተገናኙ ናቸው ብሏል።
ከስደተኞች ካምፕ አጠገብ የሚገኘው የከተማዋ ጎዳናዎች በሰው አልባ አውሮፕላኖች በቤቶች ላይ በደረሰው ጥቃት ከደረሰ በኋላ በፍርስራሾች ተሞልተዋል። የቃጠሎ ጭስ ከአድማስ ላይ ታይተዋል ፥ ካምፑ ውሃ እና መብራት የሌለበት ሁኗል ፥ ወታደራዊ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች አሁንም በጎዳናዎች ይታያሉ ፤ የጄኒን ከንቲባ የሆኑት ኒዳል አል-ኦቤዲ እንደተናገሩት ከአከባቢው የሸሹት በዘመዶቻቸው ቤት እና መጠለያ አግኝተዋል።
እንደ እስራኤል ገለጻ ከሆነ በጄኒን የተካሄደው ዘመቻ ጥቃቶች የታቀደው እና ያነጣጠሩት የጦር መሣሪያ ማከማቻ ላይ እና በጥቃቱ ውስጥ የሚሳተፉ ሚሊሻዎች በሚጠቀሙባቸው ‘የአሸባሪ መሰረተ ልማቶች’ ላይ ያነጣጠረ ነው ብሏል።
ሃማስ እና ኢስላሚክ ጂሃድ ፍልስጤማውያን በጄኒን የሚገኙ ሚሊሻዎች በእስራኤል ወታደራዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርጉትን ውጊያ እንዲቀላቀሉ አሳስበዋል።

ሃማስ በቴል አቪቭ ስለ ተፈጸመው ጥቃት ሃላፊነት ወስዷል

ይህ እ.አ.አ. በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ ጄኒን የፍልስጤም ወታደራዊ እንቅስቃሴ መናኸሪያ በነበረችበት ወቅት ከነበረው ሁለተኛው አመጽ በኋላ በዌስት ባንክ ውስጥ ከተደረጉት ዘመቻዎች ያሁኑ ትልቁ የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ እንደሆነም ታውቋል። በአሁኑ ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በአካባቢው እየተዘዋወሩ የጦር መሳሪያዎችን እየቀሙ እና ታጣቂዎች የሚጠቀሙባቸውን ዋሻዎች በማፈንዳት ላይ ሲሆኑ ፥ በቴል አቪቭ ደግሞ መኪና እግረኞችን ገጭቶ ሰባት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት አድርሷል። በድርጊቱም ሃማስ ሃላፊነቱን የወሰደ ሲሆን ፥ በጄኒን ውስጥ በነበሩት ሰዎች ላይ ለተፈጸመው ‘የወረራው ወንጀል የመጀመሪያ ምላሽ’ እንደሆነ እንዲሁም ድርጊቱንም ‘የጀግንነት ጥቃት’ ሲል አወድሶታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዌስት ባንክ ፍልስጤማውያን ኦፕሬሽኑን በመቃወም አጠቃላይ የሥራ ማቆም አድማ አድርገዋል።

የጄኒን ሃገረስብከት ካህን ጉዳዩን 'በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ' ማለታቸው

የጄኒን ሃገረስብከት ቁምስና ካህን የሆኑት አባ ላቢብ ዴይበስ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት “በእነዚህ ቀናት በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረገው ድርድር የለም ማለት ይቻላል” ብለዋል።
“እኛ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከጦርነት ጋር በሚመሳሰል መልኩ ፍንዳታ ፣ አውሮፕላኖች ፣ ታንኮች አንድ ላይ ሆነው በፍልስጤም ህዝብ ላይ ፥ ማለትም መሬታቸውን የመከላከል መብት ባላቸው አንዳንድ ወጣቶች ላይ መጥፎ ጊዜያት አምጥተዋል። ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ነበር” በማለት አክለውም “የፍልስጤም ህዝቦች መብቶቻቸው በሙሉ መልሰው በምድራቸው ላይ በሠላም እንዲኖሩ እንፈልጋለን” በማለት ምኞታቸውን ገልጸዋል።
“የጄኒን ነዋሪዎችን መርዳት እንፈልጋለን ፥ በመጀመሪያ የደረሰውን ውድመት ለመጠገን በገንዘብ መርዳት ፥ ከዚያም የፍልስጤም ህዝብ መብቶቹን በሙሉ እንዲያገኝ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ፥ መብቶቻቸውን መልሰው ካገኙ በኋላ የውጭ እርዳታ አያስፈልገንም ፥ ከዛም በሠላም እና በነፃነት መኖር እንችላለን” ብለዋል አባ ዴይቤስ። የፍልስጤም ህዝብ ለሚደረገው እርዳታው ምስጋና ይግባውና እንዴት ሲኖር እንደነበር ያስታወሱት አባ ዴይቤስ “አሁን መመሪያ መፅሃፍ አንፈልግም ፥ መብታችንን ነው የምንፈልገው ፥ እናም መብታችንን ከወሰድን እኛ ለራሳችን ማድረግ እንችላለን ፥ መኖሪያችንን እና መተዳደሪያችንን በራሳችን እናዘጋጃለን” ብለዋል።
“ለ75 ዓመታት የዘለቀውን ግጭት ለመፍታት እንዲቻል የመፍትሄ ሃሳቦችን እንዲያመጣ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እጠይቃለሁ” በማለትም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግስታት እና ድንበር የለሽ ዶክተሮች ውግዘት

የፍልስጤም ብሄራዊ ባለስልጣን ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “እስራኤል ፍልስጤማዊያን ነዋሪዎችን ማፈናቀሏን እንድታቆም በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገባ” ጥሪ አቅርበዋል ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት ቫኔሳ ሁጉኒን በበኩላቸው “በአየር እና በየብስ የሚደረጉ የጦር እንቅስቃሴዎች መጠን” እና “ብዙ ህዝብ በሚኖርበት የስደተኞች ካምፕ ላይ የተደረገው የተኩስ ልውውጥ” እንዳስደነገጣቸው ተናግረዋል።
መንግስታዊ ተቋም ያልሆነው የድንበር የለሽ ዶክተሮች ማህበርም በጤና አጠባበቅ ላይ ያሉ እንቅፋቶች እንዲሁም መንገዶች ተዘግተው እና አምቡላንሶች በብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች አደጋ እየደረሰባቸው በመሆኑ እንደሚያሳስበው ገልጿል። የእስራኤል መከላከያ ሃይል ቃል አቀባይ በበኩላቸው “ኦፕሬሽኑ አብዛኛዎቹን ኢላማዎቹን በአነስተኛ የመልስ ምት እና ጥቃቅን መሰናክሎች ውጭ ግቡን አሳክቷል ፥ ስለዚህ ከተያዘለት ቀነ ቀጠሮ ቀደም ብሎ በቀናት ውስጥ ተልዕኮው ሊጠናቀቅ ይችላል” ብለዋል።
 

06 July 2023, 17:13