ፈልግ

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ ዩሴፍ አብሲ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ ዩሴፍ አብሲ  

የመልቃይት ቤተ ክርስቲያን ከሮም ቤተ ክርስቲያን ጋር የተዋሃደችበትን 300ኛ ዓመት ልታከብር ነው

ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ የሆነች የመልቃይት ቤተ ክርስቲያን ከሮም ቤተ ክርስቲያን ጋር ሙሉ አንድነት የመሠረተችበትን ሦስት መቶኛ ዓመት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2024 ዓ. ም. እንደምታከብር የቤተ ክርስቲያኗ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዩሴፍ አብሲ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የግሪክ-መልቃይት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1724 ዓ. ም. ከሮም ቤተ ክርስቲያን ጋር በሙላት የተዋሃደችበትን ሦስት መቶኛ ዓመት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2024 የኢዮቤልዩ ዓመት ለማክበር ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ተገልጿል። አንድ ዓመት የሚቆየውን በዓል ለማክበር ቤተ ክርስቲያኒቱ ዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ዩሴፍ አብሲ በሊባኖስ በሚገኝ የፓትሪያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ፓትሪያርኩ በመግለጫቸው የኢዮቤልዩ ዓመት ቤተ ክርስቲያናቸው ባለፈው፣ በአሁኑና በወደፊት ተልዕኮዋ ላይ የምታሰላስልበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶሱ እንደሚያምን አክለው አስታውቀዋል።

የኢዮቤልዩ ዓመት ኅዳር 1/2016 ዓ. ም. ይጀምራል

“የግሪክ-መልቃይት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የ300 ዓመት የአንድነት ጉዞ” በሚል አርዕስት ኅዳር 1/2016 ዓ. ም. የሚጀምረውን የኢዮቤልዩ ዓመት ደማስቆ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል  ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚከፍቱት የግሪክ-መልቃይት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዩሴፍ አብሲ እንደሚሆኑ ታውቋል። የግሪክ-መልቃይት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከሮም ቤተ ክርስቲያን ጋር ሙሉ አንድነትን ከመሠረቱ ትላልቅ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ ስትሆን፣ ዛሬ ከ 1.5 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን እዳሏት እና የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ክርስቲያኖች ተብለው የሚጠሩባት ጥንታዊ የአንጾኪያ መንበር መሠረት እንዳላት ይታወቃል።

የመልቃይት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከ1ኛው ክፍለ ዘመን ይጀምራል

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ ዩሴፍ ታሪክን በመጥቀስ በሰጡት መግለጫቸው፥ በክርስቲያን ማኅበረሰብ መካከል መከፋፈልን የፈጠረው ከመጀመሪያው የሐዋርያት ትምህርት ጀምሮ የነበሩ የነገረ-መለኮት ውዝግቦች መሆናቸውን አስታውሰው፣ በ 451 ዓ. ም. የተካሄደውን የኬልቄዶኒያ ጉባኤ ውሳኔን የተከተሉ ክርስቲያኖች መልቃይት ወይም “የነገሥታት ሰዎች” ተብለው ሲጠሩ፥ የስሙ ምንጭ በጥንታዊት ሶርያ ለንጉሥ የሚሰጥ ስም ወይም “ማልኮ” የሚል መጠሪያ ሲሆን፥ ምዕመናኑ ይህን መጠሪያ የተቀበሉበት ምክንያት፥ ንጉሠ ነገሥታቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላቸው ግንዛቤ ተመርኩዘው የተናገሩትን በመቀበላቸው እንደሆነ ይታወቃል።

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ዩሴፍ በማከልም፥ በመካከለኛው ምሥራቅ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የምዕራብ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሚስዮናውያን የተፈጠረን መከፋፈል ለመጠገን እና በአንጾኪያ ፓትሪያርካዊ አስተዳደር እና በሮም ቤተ ክርስቲያን መካከል አንድነትን ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት ማደርጋቸውን አስታውሰዋል።

በ 1724 (እ.አ.አ) ከሮም ጋር እንደገና መዋሃድ

የሚስዮናውያኑ ጥረት ከሌሎች አስፈላጊ ከሆኑ ተጨማሪ ሥራዎች ጋር ተዳምሮ ወደ ዳግም ውህደት እንቅስቃሴ በማደግ በራሱ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን መካከል ሌሎች ክፍፍሎችን አስከትሏል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1724 ዓ. ም. የመልቃይት ቤተ ክርስቲያን ከሮም ቤተ ክርስቲያን ጋር እንደገና የመሠረተችው አንድነት ከመጀመሪያው ሺህ ዓ. ም. ጀምሮ የነበራትን አንድነት ተከትሎ እንደሆነ የአንጾኪያው ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ስድስተኛ አረጋግጠዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአንጾኪያ መልቃይት ቤተ ክርስቲያን ከሮም ቤተ ክርስቲያን ጋር ግንኙነት ከሌላት ግሪክ-ኦርቶዶክስ ተለይታ ከሮም ቤተ ክርስቲያን ጋር ግንኙነት ካላት ግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር በቋሚነት አንድነቷን መጀምሯ ይታወሳል። በአንፆኪያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከፋፈል ቢኖርም፥ የክርስትና እምነትን የመጠበቅ ተልዕኮዋን እየተወጣች አስቸጋሪ ጊዜያትን በሙሉ በአሸናፊነት መዝለቋን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ዩሴፍ አብሲ አስታውሰዋል።

“ዛሬ ለልዑል እግዚአብሔር እና መልካም ፈቃድ ላላቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምስጋና ይግባቸው” ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዩሴፍ አብሲ፥ በቤተ ክርስቲያናቸው እና በእህት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ግንኙነት እርስ በርስ የመከባበር፣ በወንድማማችነት መዋደድ እና በአንድ ወንጌል አገልግሎት ውስጥ ለመተባበር ምእመናኖቻቸው ዕድል እንዳላቸው ገልጸዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች መሆናቸውን በግልጽ ለመመስከር ከተለያዩ ቤተ እምነቶች ጋር በአንድ ጣሪያ ሥር የመሰብሰብ ልምድ እንዳላቸው ገልጸው፥ ከክርስቲያኖች የአንድነት እንቅስቃሴ በተጨማሪ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ይበልጥ አንድ ያደረጋቸው ከእስላማዊ መንግሥት ቡድን የደረሰባቸው ስደት እንደሆነ አስረድተዋል።

በዓለም ዙሪያ የምትገኝ የግሪክ-መልቃይት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን

የግሪክ-መልቃይት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሶርያ፣ በሊባኖስ እና በሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፥ ባለፉት ዓመታት ባጋጠማት ስደት ምክንያት በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እና በኦሽንያ ውስጥ ካሏት ሀገረ ስብከቶች በተጨማሪ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ኒውተን እና ማሳቹሴትስን ጨምሮ በመላው ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ከ50 በላይ ቁምስናዎች እና የተልዕኮ ሥፍራዎች እንዳሏት ታውቋል።

የግሪክ-መልቃይት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከሮም ቤተ ክርስቲያን ጋር የተዋሃደችበትን ሦስት መቶኛ ዓመት በ 2024 የኢዮቤልዩ ዓመት የምታከብረው የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶችን በመፈጸም፣ የጥናት ጉባኤዎችን እና ሕትመቶችን በማዘጋጀት፣ ጥልቅ የሆኑ ታሪካዊ፣ ሥነ-መለኮታዊ እና ሥነ-ምህዳራዊ ጥናቶችን በማዘጋጀት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የመልቃይት ማኅበረሰቦች ተጠብቀው የቆዩ መንፈሳዊ እና ሥነ-ጥበባዊ ቅርሶች ለትርዒት በማቅረብ እንደሚሆን ተገልጿል።

13 July 2023, 13:45