ፈልግ

ከባህር ላይ አደጋ ለተረፉ ስደተኞች አስቸኳይ እርዳታ እየተደረገ ከባህር ላይ አደጋ ለተረፉ ስደተኞች አስቸኳይ እርዳታ እየተደረገ  (Antonello Nusca)

የካቶሊክ የስደተኞች ኮ. ስደተኞችን ለመታደግ እና ህጋዊ መንገዶችን ለማዘጋጀት ጥረትን ይጠይቃል አለ

ዓለም አቀፉ የካቶሊክ የስደተኞች ኮሚሽን (ICMC) ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በኢጣሊያ ደሴት ላምፔዱዛ ያደረጉትን ሃዋሪያዊ ጉብኝት አሥረኛ ዓመትን በማስመልከት ፥ የሰዎችን ህይወት መጥፋት ለመከላከል እና ጦርነትን እና ድህነትን ሸሽተው ለሚሰደዱ ስደተኞች አስተማማኝ መንገዶችን ለማዘጋጀት የተቻለው ሁሉ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

አሁን ያለንበት ሃምሌ ወር ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የዛሬ አስር ዓመት ለላምፔዱዛ የመጀመሪያው የሆነውን ጳጳሳዊ ሃዋሪያዊ ጉብኝት አሥረኛ ዓመቱን ይዟል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ባለፈው ሃምሌ 1, 2015 ዓ.ም. ለአግሪጀንቶ ሊቀ ጳጳስ አሌሳንድሮ ዳሚያኖ በላኩት ደብዳቤ ፥ ከሲሲሊ በስተደቡብ በምትገኘው ትንሿ የኢጣሊያ ደሴት ላምፔዱዛ ያደረጉትን ጉብኝት አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በደብዳቤው ላይ “በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ለቁጥር የሚታክቱ ንጹሐን ዜጎች በተለይም ሕጻናት ከጦርነት እና ከአመጽ ሸሽተው አስተማማኝ ሕልውና ፍለጋ ሲሰደዱ በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ከባድ አደጋዎች የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው ፥ እነዚህ “ድምፅ አልባ ሞቶች” አሳዛኝ እና ሰሚ ያጡ ጩኸቶች ማንንም በግድየለሽነት መተው እንደሌለበት ገልጸዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱን መልእክት በማስተጋባት የዓለም ዓቀፉ የካቶሊክ የስደተኞች ኮሚሽን የጳጳሱን ጉብኝት አስረኛ ዓመት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል። የስደተኞች ሞት የጀልባ አደጋም ቢሆን ያው ሞት መሆኑን ገልጾ ፥ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ድህነትን ወይም ሃገራቸው ላይ የሚደረጉትን ጦርነትን ሸሽተው የሚሰደዱትን ሁሉ ለመርዳት እና ለማዳን እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል።
የዓለም አቀፉ የካቶሊክ የስደተኞች ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሮበርት ቪቲሎ ከቫቲካን ዜና የሬድዮ ዝግጅት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የላምፔዱዛን ጉብኝት እና አስረኛ ዓመት በማስታወስ ፥ ወደፊት ያለው ረጅም መንገድ በባህር ላይ አንድም ህይወት እንደይጠፋ መስራት እና ከጦርነት እና ከድህነት ለሚሸሹ ስደተኞች አስተማማኝ መንገዶች ማዘጋጀት ዋስትና ሊሆን ይችላል ብለዋል።

  ከኮሚሽኑ ዋና ጸሃፊ ሮበርት ቪቴሎ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

 ሃምሌ 2005 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወደ ላምፔዱሳ ስላደረጉት ጉዞ ምን ያስታውሳሉ?

ወደ ላምፔዱዛ ስለተደረገው የመጀመሪያ ጉዞ በአእምሮዬ ላይ ጎልቶ የሚወጣው ነገር በመጀመሪያ ደረጃ ቅዱስ አባታችን ብቻቸውን ወደዚያ መሄዳቸው እና ለጉብኝቱ ብዙ ትኩረት እንዲሰጠው አለመፈለጋቸው ፡ ይልቁንም በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ የበርካታ ሰዎች ህይወት ስለጠፋ በመጀመሪያ ይቅርታ ለመጠየቅ መፈለጋቸው ነበር። እናም ይህ ሁኔታ ሊቀጥል ስለማይችል እና ሊቀጥል ለማይገባው እውነታ ትኩረት እንዲሰጠው ፈልገዋል። ስለዚህ እኔ የተሰማኝ እርሳቸው በእውነት ብዙ ስደተኞችን በባህር ላይ እንዲሁም በሌላ መንገድ ፣ በበረሃ እና በተራራ ላይ ስለጠፋው አሰቃቂ አደጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለንን ግንዛቤ እያሻሻሉ እንደነበር ነው ።

 ከአሥር ዓመታት በኋላ አሁን ላይ ፥ በመልካምም ሆነ በመጥፎ ውጤቶቹ ምን ላይ ደርሰናል?

ከአሥር ዓመታት በኋላም ችግሩ ተባብሶ ስላለ ይህ እንዴት የዓለምን ህሊና ይነሣል ብዬ የነበረኝ ተስፋ ሁሉ እውን ሊሆን አልቻለም። በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በሆነው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ የተሰሩ እና ሪፖርት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት እ.አ.አ. ከ 2014 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ 56,849 የጠፉ ስደተኞች አሉን ፥ ምናልባት ብዙ ጊዜ የጠፉትን የህዝቡ ቁጥር በትክክል ስለማናውቅ ይህ ዝቅተኛው ግምት ነው። ከእነዚህም ውስጥ 27,629ቱ ፥ ግማሽ ያህሉ ፥ በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ነው የጠፉት ወይም የሞቱት። ስለዚህ አሁንም እነዚህን ሁሉ ሰዎች እያጣን ባለንበት ሰዓት የመገናኛ ብዙሃን ብቻ ሳይሆን የብዙዎቹ የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ትኩረት በዚህ ታላቅ ሰቆቃ ላይ ባለመሆኑ እጅግ ያሳዝናል።

ከእነዚያ ከሰጡት ቁጥሮች አንጻር አሁን ላይ ምን መሆን አለበት ብለው ያስባሉ?

እኔ እንደማስበው አንድ ትልቅ ነገር መሆን ያለበት እኛ የየሃገራቱ ዜጎች የሆንን እና ተወካዮቻችንን እና ውሳኔ ሰጪዎችን የምንመርጥ ሰዎች ለዚህ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጥ አጥብቀን መግለጽ እና መስራት አለብን። እ.አ.አ. በ 2022 የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ሰብአዊ መብቶች ልዩ ሪፖርት ላይ የወጣውን ጥቅስ ላካፍላችሁ እወዳለሁ ፤ ይህ ዘገባ እንደሚለው ፥ “የግፊት አካሄዶች በብዙ ግዛቶች ውስጥ እንደ አጠቃላይ ፖሊሲ ሆነው ቀጥለዋል ፥ እናም ዓለም አቀፍ ድንበሮችን የሚያቋርጡ ስደተኞችን የሰብአዊ መብት ተጠቃሚነት በእጅጉ ማደናቀፉን ቀጥለዋል። በመንግስት የሚመራው ጥፋት ክሶችን ውድቅ ለማድረግ ወይም ለመደበቅ በሚደረገው ሙከራ ምክንያት የዚህ አይነት ጥሰቶች ሙሉ በሙሉ ተደብቀዋል። ይህ ማለት ለምሳሌ የጄኔቫ የስደተኞች ስምምነትን በፈረሙ በብዙ አገሮች ውስጥ እንኳን፣ ቃል ኪዳኑን የፈረሙ አገሮች ሰዎች ሕይወታቸው አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ በዚያች አገር ጥገኝነት እንዲጠይቁ መፍቀድ አለባቸው ፥ አሁን ግን ስደተኞቹን ከድንበሮቻቸው እያሸሹ እና ተመልሰው ወደመጡበት እንዲመለሱ እያስገደዱ ነው። በመሆኑም የጥገኝነት ጥያቄ ለማቅረብ መግባት አይችሉም። ስለዚህም ሌላ ቦታ ማድረግ አለባቸው ማለት ነው። እኔ እንደማስበው ሰዎች ስለ ዓለምአቀፍ ሁኔታ እንዲያውቁ እና ለምን እንደዚህ አይነት ፖሊሲዎችን እንደሚያወጡ ውሳኔ ሰጪዎቻቸውን እንዲጠይቁ ማድረግ ያለብን ነገር ይመስለኛል።

ይህ ደግሞ ሎቢ ማድረግ እና የአደጋ ጊዜ እርዳታ ለተቸገሩ ሰዎች መሰጠቱን ለማረጋገጥ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ማለት ነው ይላሉ?

በትክክል! ለእነዚያ ድንገተኛ ሁኔታዎች ምላሽ እንዲሰጡ የሰዎችን ንቃተ ህሊና ለመቀስቀስ እየሞከሩ ነው። የጣሊያን ጳጳሳት ጉባኤ የስደተኞች ኤጀንሲ በሆነው በሚግራንትስ የተዘጋጀው ዘገባ በጣም አስደንቆኛል ፥ ይህ በ2015 ዓ.ም. ሚያዝያ ወር ላይ በካላብሪያ የባህር ዳርቻ ወደ 70 የሚጠጉ ሰዎች በጠፉበት ወቅት የተደረገ ዘገባ ነው። የዚያ መጣጥፍ ርዕስ ደግሞ “የጀልባ አደጋ የሰው ልጅ አሻራዎች” ነበር። እኛ ደግሞ ግድ የለሽነታችንን ትተን መሄዳችንን ልንገነዘበው የሚገባን ይመስለኛል እና ቅዱስ አባታችን በዚህ የላምፔዱዛ 10ኛ ዓመት የማስታወሻ በዓል ላይ ባስተላለፉት መልእክትም ይህንኑ ተመሳሳይ ነጥብ ሰጥተዋል። እሱም “መላው ቤተ ክርስቲያን ለታደሰ እና ጥልቅ የሆነ የኃላፊነት ስሜት ፣ አብሮነት እና መጋራት ተጠርታለች” ብለዋል። ስለዚህ በእነዚያ ድንገተኛ ሁኔታዎች ውስጥ ሁለቱንም ተካፋይ መሆን አለብን ፥ ለባህር ጉዞ በማይገቡ ጀልባዎች ላይ ሆነው ለአደጋ የተጋለጡትን ሰዎች ህይወት ለማዳን እየሞከሩ ነው ወይም በባህር ውስጥ ሊያድኗቸው የሚሞክሩትን እንዳይገድቡ ወይም እንዳይከለክሉ ማድረግ አለብን ወይም ወንጀለኛ እንደሆኑ እንዳያስቡ ማድረግ አለብን። አፋጣኝ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንድንሰጣቸው በሚያርፉበት ቦታ መገኘታችንንም ያካትታል ማለት ነው። ድንበራችንን አቋርጠው የሚመጡትን እና ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ለመሰደድ የሚገደዱትን ሰዎች እውነተኛ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ለማዳበር መሞከር ፥ የእንኳን ደህና መጣችሁ እና ጥበቃ ለማድረግ መሞከር ማለት ነው። በዓለም ላይ ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጉ ተገደው የተሰደዱ ስደተኞች እንዳሉ በመረዳት ለችግሮቻቸው ምላሽ መስጠት አለብን።

ይህ ብዙ ቁጥር ነው ፥ ‘ብዙ ሰዎችን ማስተናገድ ደግሞ አይቻልም’ ለሚሉ ሰዎች ምን ምላሽ ይሰጣሉ?

ደህና ፣ በመጀመሪያ ሰዎችን ማሳወቅ አለብን ፥ ምክንያቱም ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ይህንን ወደ አገራችን የሚመጡ ብዙ ሰዎች አድርገው ስለሚመለከቱት እና በአንዳንድ መንገዶች ምቾት ላይሰጣቸው እና ልዩ መብቶች ላይም ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ ፥ እኛም በነዚህ ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ እንገኛለን። እውነታው ግን አብዛኞቹ ተገደው የሚሰደዱ ስደተኞች በደቡብ በሚገኙ ድሃ ሃገራት ውስጥ ጥገኝነት ጠያቂ ሲሆኑ ፥ በእነዚያ ድሃ ሃገራት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ግን ወደ እነርሱ እየሄዱ አስቸኳይ ዕርዳታ ሊሰጣቸውና ከማኅበረሰባቸው ጋርም እንዲዋሃዱ እየሞከሩ ነው። ስለዚህ አብዛኛው ሸክሙ የሚደርሰው ከፍተኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ውጪ ነው ፥ እናም እኛ ከፍተኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ውስጥ ያለነው በዓለም ላይ ተገደው የሚሰደዱ ስደተኞችን ለመቀበል በጣም ከባድ ሸክም የተሸከሙትን ድሃ ሃገራት መርዳት አለብን። ግን ደግሞ የምናገኛቸው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ልማት ፋይዳዎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሀገራትም ሊደርሱ እንደሚችሉ የማረጋገጥ ኃላፊነት አለብን። ይህ ደግሞ በዓለም ላይ እየተከሰተ ያለውን ስደትን ለመከላከል ይረዳል።

ስደተኞችን በሚመለከት ሁኔታውን ለማሻሻል እየተሳተፉ ያሉ እና እየተሰሩ ያሉ አንዳንድ ስራዎችን ጥቂት ምሳሌዎችን ማቅረብ ይችላሉ?

አዎን ፥ በዓለም አቀፉ የካቶሊክ የስደተኞች ኮሚሽን ውስጥ እየሰራን ያለነው ሥራ ፥ ለጳጳሳት ጉባኤዎች እና ተገደው ለሚሰደዱ ስደተኞች እና ለተቸገሩ ሰዎች ምላሽ ለሚሰጡ የካቶሊክ ድርጅቶች ትንሽ እርዳታ ለመስጠት የተወሰነ ገንዘብ ማግኘት ችለናል ። ለዚህም አንድ ምሳሌ እሰጣችኋለሁ ፤ በኮትዲቯር ከኮትዲቯር የጳጳሳት ጉባኤ እና እዚያ ካሉት ካሪታስ ጋር ከአውሮፓ የተባረሩ ስደተኞችን እንደገና ለማሰልጠን እየሰራን ነው። ወደ አውሮፓ የሄዱት ወደ አገራቸው ተባርረዋል ነገር ግን በገዛ አገራቸው ራሳቸውን መቻል የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው። እናም የሙያ ክህሎት እየሰጠናቸው እና አንዳንድ አነስተኛ ንግዶችን እንዲያሳድጉ እየረዳቸው በሃገራቸው እንዲቆዩ እና ነገር ግን ተገደው ከመሰደዳቸው በፊት ክብር ባለው መንገድ መኖር እንዲችሉ እየረዳቸው ነው። ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች ለመግባት ሞክሯል ፥ በህንድ ውስጥም በተመሳሳይ መልኩ ብዙ ሥራዎችን ለመስራት ተችሏል። እንደ አንድ አይነት የታክሲ ትራንስፖርት ስርዓት መዘርጋት ፣ ወይም መጠነኛ መጠነ ሰፊ መደብር መክፈት፣ መደበኛ ያልሆነ ስራ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ግን ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ እና ጨዋ ኑሮ እንዲኖሩ የሚያስችል በቂ ድጋፍ በሚሰጣቸው መንገድ እየተሰረ ነው። እነዚህ የመሰደጃ መንገዶችን ከመቀየር ፥ የስደትን ፍሰቶች እና ሰዎች በመኖሪያ አካባቢያቸው የበለጠ ተረጋግተው እንዲኖሩ እና ከመኖሪያ አካባቢያቸው እንዳይወጡ ከማገዝ አንፃር የምናያቸው ናቸው።

የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ችግር ለመቋቋም የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ እንዲሁም የእንኳን ደህና መጣችሁ ፣ ይፋዊ ስምምነት ፣ ከረጅም ጊዜ ዕርዳታ በተጨማሪ የስደት እውነታ አጠቃላይ ውስብስብነት ላይ ለመሞከር እና ለመሥራት የታሰቡ የተቀናጁ ጥረቶች አሉ ወይ?

አዎ ፥ በየዓመቱ የዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ልማት ፎረም ተብሎ የሚጠራ ስብሰባ አለ ፥ እናም ይህ የሁለቱም የመንግስት ተወካዮች እና የሲቪል ማህበራት ስብሰባ ነው። የእኛ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ኮምሽን ተቋም በዚያ ስብሰባ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ተሳታፊዎችን ወደ ጉባኤው ይጠራል። ስለዚህ ለዚያ ስብሰባ ለመዘጋጀት አብረን የምንሰራቸው ወደ 2000 የሚጠጉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አሉን። የሃገራት ፣ የመንግሥታት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ትይዩ ስብሰባዎች አሏቸው ፥ ከዚያም የሁለቱም ወገኖች ተገናኝተው የጋራ ስብሰባዎችን ያደርጋሉ ። እናም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጠቃሚ መልእክት መላላኪያ ፣ የድጋፍ መስጫ መልዕክቶችን እንዲያዳብሩ ፣ ይበልጥ ህጋዊ እና ፍትሃዊ የስደት መንገዶችን እንዲያስተዋውቁ እየረዳን ነው ፥ ስለዚህም ሰዎች በስደት የተሻለ ሕይወት ለመፈለግ ለባህር መንገድ ምቹ ያልሆኑ ህገወጥ ጀልባዎችን እንዳይጠቀሙ እና በበረሃ ወይም በተራራ እንዳይንከራተቱ ለማገዝ እየጣርን ነው። በዚህ ዓመት መስከረም 16 ቀን በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የተከበረው 109ኛው የዓለም የስደተኞች እና የፍልሰተኞች ቀን ላይ ብፁዓን ጳጳሳት ከመረጡት መሪ ቃል ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው። የዚህ ዓመት መሪ ቃልም “ለመሰደድም ሆነ በሃገር ለመቆየት የመወሰን ነፃነት አለን” ይል ነበር ፥ እና እኔ እንደማስበው ከሆነ በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባርም ሰዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚረዱ ትክክለኛ እና በትውልድ ሃገራቸው ውስጥ አጠቃላይ የሰው ልጅ እድገት የሚረዱ ፖሊሲዎች ላይ የበለጠ ልናስተዋውቅ የሚገባን ጭብጥ ነው።
 

14 July 2023, 13:59