ፈልግ

በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን የሚከበር ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን የሚከበር ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል   (AFP or licensors)

የሆንግ ኮንግ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያ ወጣቶች በዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት መዘጋጀታቸው ተገለጸ

ከ300 የሚበልጡ የሆንግ ኮንግ ካቶሊካዊ ወጣት ነጋዲያን ከሐምሌ 26-30/2015 ዓ. ም. ድረስ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን በሚከበር ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት ዝግጅት ማድረጋቸው ታውቋል። ወጣት ነጋዲያኑ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ለካርዲናልነት ካጯቸው ከብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ቾው ሳኡ-ያን ልዩ የተልዕኮ አገልግሎት ጥሪን ተቀብለው እምነትን ለሌሎች እንዲያካፍሉ ተጋብዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ቾው ሳው-ያን በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ላይ በሚከበር ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ለመገኘት ዝግጅት እያደረጉ ለሚገኙ 300 የሆንግ ኮንግ ወጣቶች ልዩ የተልዕኮ አገልግሎት አደራን ሰጥተዋል። ሐምሌ 25/2015 ዓ. ም. በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ላይ በሚጀምረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ከሁሉም የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ወጣቶች እንደሚገኙ ሲነገር፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ሐምሌ 26/2015 ዓ. ም. በሥፍራው እንደሚገኙ ይጠበቃል።

በ14 ቡድኖች የተመደቡት የሆንግ ኮንግ ወጣቶች በአገሪት ከሚገኙ የተለያዩ ቁምስናዎች፣ ገዳማት፣ ትምህርት ቤቶች እና መንፈሳዊ ማኅበራት የተወጣጡ መሆናቸው ታውቋል። እያንዳንዱ ቡድን በፌስቲቫሉ ወቅት ቡድኑን እንዲያግዝ በተመረጠ ወጣት የሚመራ ሲሆን፥ የ14ቱ ቡድኖች መሪዎች የቅዱስ ወንጌል ንባባት አስተንትኖን፣ የቅዱስ ቁርባን ቡራኬን እና የኅብረት ጸሎት ሥነ-ሥርዓቶችን አስመልክቶ በተዘጋጁ 4 ስብሰባዎች ላይ መሳተፋቸው ታውቋል።

እምነትን በኅብረት መካፈል

ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ቾው ሳው-ያን ለሆንግ ኮንግ ወጣቶች የተልዕኮ አደራን ለመስጠት በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ በሚገኝ የንጽሕት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማቅረባቸው ታውቋል። የሆንግ ኮንግ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ቾው ሳው-ያን፥ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫልን የሚካፈሉ የሆንግ ኮንግ ወጣቶች ልባቸውን እንዲከፍቱ አደራ ብለዋል። ግብዣው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀረበላቸው መሆኑን የተናገሩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፥ ወጣቶቹ ከራሳቸው ወጥተው ከመላው ዓለም ከሚመጡ ወጣቶች ጋር በመገናኘት እና በመበረታታት ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽ እንዲሰጡ መክረዋቸዋል። አቡነ እስጢፋኖስ በተጨማሪም ወጣቶቹ በሊዝበን ከሚያገኟቸው ሌሎች ወጣቶች ጋር በመተባበር እምነታቸውን እንዲያካፍሉ አሳስበዋል።

በመላው አውሮፓ ውስጥ የሚደረግ ንግደት

በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ 14ቱ የቡድን መሪዎች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጉዞአቸው እንድትጠብቃቸው፣ በፍጥነት እና በትህትና እግዚአብሔርን መከተል መማርን ለምነዋል። በሆንግ ኮንግ የተለያዩ ወጣት ማኅራትን በመሪነት ከሚያገለግሉ በርካታ ካህናት ጋር 300 ወጣቶችን  ወደ ፖርቱጋል መዲና ሊዝበን የሚመሩት የጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ሚስዮናውያን ማኅበር አባል እና የሀገረ ስብከቱ የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት አባ ፍሩክቱዎሶ ሎፔዝ ማርቲን መሆናቸው ታውቋል።

የቡድኑ ዓባላት ሊዝበን ከደረሱ በኋላ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በፌስቲቫል ላይ ለመገኘት ከተመዘገቡት 600,000 ሰዎች ጋር ለመገናኘት እና ሱባኤን ጨምሮ እራስን ለበዓሉ ለማዘጋጀት የሚያግዙ ስልጠናዎችን እንደሚሳተፉ ታውቋል። ወጣት ነጋዲያኑ እንደ ጉዞ መርሐ ግብራቸው ስፔን ውስጥ ወደ “ሳንቲያጎ ዴ ኮምፖስቴላ” የሚወስደውን መንገድ በመያዝ በታዋቂው የቅዱስ ያዕቆብ “ካሚኖ ደ ሳንቲያጎ” የ100 ኪሎ ሜትር ጉዞን እንደሚያደርጉ ታውቋል። ወጣቶቹ በተጨማሪም አውሮጳ ውስጥ በሚያደርጉት ቆይታም በፈረንሳይ የሚገኙ ልዩ ልዩ ቤተ መቅደሶችን እና እንዲሁም በጀርመን የሚገኘውን የኤሰን ሀገረ ስብከት እንደሚጎበኙ ታውቋል።

ማርያም ሚስዮናዊት እናት

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ዘንድሮ በሐምሌ ወር 2023 ዓ. ም. የሚከበረው ዓለም አቀፍ ወጣቶች ቀን በሉቃ. 1፡39 ላይ “ማርያም ተነሥታ ፈጥና ሄደች” ከሚለው መሪ ቃል ወጣቶች መመሪያን እንዲቀበሉ የሚጋብዝ መሆኑ ታውቋል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናት እንደምትሆን ከመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል መልዕክት ከተቀበለች በኋላ በፍጥነት ተነስታ ዘመዷ ኤልሳቤጥ ዘንድ በመሄድ “ሚስዮናዊት” እንደሆነች ሁሉ፥ እያንዳንዱ ወጣት በሚያደርገው ንግደት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌን በመከተል ተነሳሽነትን ማግኘት እንደሚችል ተገልጿል።

15 July 2023, 16:40