ፈልግ

የሩስያ እና የዩክሬይን ጦርነት ያስከተለው ቀውስ የሩስያ እና የዩክሬይን ጦርነት ያስከተለው ቀውስ  (AFP or licensors)

ቅድስት መንበር የዩክሬን ጦርነት እንዲያበቃ የተባበሩት መንግሥታትን አሳሰበች

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ የመንግሥታቱ ድርጅት በኒውዮርክ ከተማ ያዘጋጀውን ጠቅላላ ጉባኤ ተካፍለዋል። አቡነ ገብርኤል በጉባኤው ወቅት ለተካፋዮቹ ባደረጉት ንግግር፥ ዩክሬይን ውስጥ በጊዜያዊነት በተያዙ ግዛቶች ውስጥ ያለውን ሁኔታ ገልጸው፣ ቅድስት መንበር በዩክሬይን በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጦርነት እንዲያበቃ ማሳሰቧንም ተናግረዋል። ከዚህም ጋር በተጨማሪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አገራቱ ጦርነትን በዝምታ ከመመልከት ይልቅ የሰላም ጥረቶችን እንዲያደርጉ ያቀረቡትን ጥሪ በድጋሚ አሰምተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ ዩክሬይን ውስጥ በጊዜያዊነት በተያዙ ግዛቶች ውስጥ ባለው ሁኔታ ላይ ለመምከር ለተቀመጠው 88ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ማክሰኞ ሐምሌ 11/2015 ዓ. ም. ንግግር አድርገዋል።

'ጦርነት ይቁም!'

አቡነ አቡነ ገብርኤል ለጠቅላላ ጉባኤው ባደረጉት ንግግር፥ የሰው ልጅ ደም በከንቱ የሚፈስበት አመጽ ቅድስት መንበርን እንዳሳሰባት እና “የጦር መሣሪያ ድምጽ መሰማት የለበትም” በማለት ያቀረበችውን አቤቱታ እና እንዲሁም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ዓለም አቀፍ ተዋናዮች እና የአገራት የፖለቲካ መሪዎች ጦርነትን ለማስቆም የቻሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ” በማለት ያቀረቡትን ጥሪ አስታውሰዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፥ በዩክሬን ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጦርነት እንደ ሌሎች ጦርነቶች ሁሉ፥ በኖቫ ካኮቭካ ግድብ ላይ ያደረሰውን ውድመት በማስታወስ በሕዝብ እና በቤተሰብ ፣ በህፃናት እና በአረጋውያን ፣ አገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ በተገደዱ ሰዎች ፣ በከተሞች፣ በመንደሮች እና በፍጥረት ላይ የሚያደርስውን አሳዛኝ አደጋ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

ሰብዓዊ ድጋፍን ማድረግ

ቅድስት መንበር ስደተኞችን ተቀብለው ድጋፋቸውን ላደረጉት እና በማድረግ ላይ ለሚገኙ መንግሥታት በሙሉ ምስጋናዋን ማቅረቧን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፥ በጦርነት እና በአመጽ ምክንያት ለተፈናቀሉት ሰዎች አስተማማኝ ሥፍራን ማዘጋጀርት፣ በፈቃደኝነት ወደ ቤታቸው በሰላም እስኪመለሱ ድረስ ሰብዓዊ ድጋፍ ማግኘት እንዳለባቸው አስገንዝበው፥ በግጭቱ ምክንያት ተለያይተው የነበሩ ቤተሰቦችን በፍጥነት ማገናኘት ወሳኝ እንደሆነ እና የሕፃናትን ምኞት ማክበር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሰላም ጎዳና መጓዝ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን የመሰለ መከራ ሲደርስ ጦርነትን በዝምታ ከመመልከት ይልቅ ሰላምን ለማምጣት ተባብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ጠቅሰዋል። አክለውም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰላም ተልዕኮዎችን የመምራት ኃላፊነት እና ወደ ሰላም መንገድ ሊመሩ የሚችሉ ሰብዓዊ ምልክቶችን የመለየት አደራን ለብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ መስጠታቸውን ለጉባኤው ተናግረዋል።

"ጦርነት ስህተት እና አስፈሪ ነው"

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ጥሪ የደገሙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፥ “ጦርነት በራሱ ስህተት እና አስፈሪ” መሆኑ በመገንዘብ ከዚህ በፊት ያልተሞከሩ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን በመጠቀም የጦርነት አስከፊ አደጋን ማስወገድ ይገባል ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በመጨረሻም፥ ቅድስት መንበር ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ጥሪ፥ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ቅድስት መንበር ድርድር መጀመሯን በማረጋገጥ ለጉባኤው ያደረጉትን ንግግር አጠናቀዋል።

20 July 2023, 16:00