ፈልግ

የኢትዮጲያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባሄ አባላት የኢትዮጲያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባሄ አባላት  

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ 55ኛውን መደበኛ ስብሰባ እያደረገ እንደሚገኝ ተገለጸ!

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት 55ኛ መደበኛ ጉባኤያቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በቅዱስ ዶንቦስኮ ገዳም ከሐምሌ 4/2015 ዓ.ም. መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ ከጥዋቱ 1 ሠዓት ላይ በብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን በተመራ መስዋዕተ ቅዳሴ መጀመሩ ተገልጿል። በመስዋዕተ ቅዳሴውም ላይ ለጳጳሳት ፣ ለካህናት ፣ ለደናግላን ፣ ለምዕመናን እንዲሁም በእድሜ መግፋት የተነሳ ጡረታ ወጥተው በተላያየ ገዳማት ላሉ ጳጳሳት ጸሎት ተደርጓል።

የእዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ በዓመት ሁለቴ ማለትም በታህሳስ ወር እና በሐምሌ ወር የሚደረግ ሲሆን ፥ በዚህም ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ የቅድስት መንበር ተወካይ የሆኑት ብጹዕ አቡነ አንቱዋን ካሚሌሪ የተገኙ ሲሆን ፥ የአዲግራቱ ብጹእ አቡነ ተስፋስላሤ መድህን አሁን ሃገራችን ላይ ባለው የፀጥታ ምክንያት በጉባሄው ላይ ሊገኙ አልቻሉም፥  የሶዶው ሃገረ ስብከት ብጹዕ አቡነ ጸጋዬ ቀነኒ በህመም ምክንያት ካለመገኘታቸው በስተቀር የሁሉም ሃገረስብከት ብጹአን አባቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጸሃፊ የሆኑት ክቡር አባ ተሾመ ፍቅሬ እንደገለጹት በዚህ ጉባኤ ላይ ከብጹአን አባቶች የተሰበሰቡ አጀንዳዎች ላይ ውይይት የሚደረግ ሲሆን ፥ አጠቃላይ ቤተክርስቲያኒቷን የሚያጋጥሟትን ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶች ላይም ምክክር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ተናግሯል።

አጀንዳዎቹ በዋናነት ባለፉት ስድስት ወራት የቤተክርስቲያኒቷ ሐዋርያዊ እንቅስቃሴ እንዴት እንደነበር እና በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ምን ይጠብቀናል ፥ ምንስ መሰራት አለበት በሚለው ሃሳብ ዙሪያ ላይ ይወያያል።

በተጨማሪም ክቡር አባ ተሾመ እንዳብራሩት በዚህ ጉባኤ አጠቃላይ የሲኖዶስ ሂደት በዋናነት የሚታይ ሲሆን በየደረጃዎቹ ሲካሄዱ የነበሩ የቤተክርስቲያን የአስር ዓመት ሐዋርያዊ ዕቅድም ወደ ማጠቃለያው ቀርቦ በብጹአን አባቶች ይሁንታ እና ውሳኔ የሚሰጥበት ጉዳይ እንደሆነም ገልፀዋል።

ይህ ጉባኤ ለአራት ተከታታይ ቀናት ተካሂዶ ሃምሌ 7 ፥ ዕለተ አርብ ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል።  

12 July 2023, 10:46