ፈልግ

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ሲያሰለጥናቸው የነበሩ ተማሪዎችን አስመረቀ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ሲያሰለጥናቸው የነበሩ ተማሪዎችን አስመረቀ 

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ሲያሰለጥናቸው የነበሩ ተማሪዎችን አስመረቀ

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሆነው ‘የቅዱስ ቶማስ አኪውነስ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ’ ኢኩስታ ወይም በእንግሊዘኛው Ethiopian Catholic University of St Thomas Aquiuness (ECUSTA) የሚባለው ተቋም ዛሬ ዕለተ ቅዳሜ ሃምሌ 22/ 2015 ዓ.ም. አዲስ አበባ ፥ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ቅጥር ጊቢ ውስጥ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ለአራት ዓመታት ሲያሰለጥናቸው የነበሩ 37 ተማሪዎችን በከፍተኛ ድምቀት አስመርቋል።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ዛሬ ከተመረቁት ተማሪዎች ውስጥ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ 14 ተማሪዎች ፣ በማህበራዊ ሳይንስ 10 ተማሪዎች እና በሜዲካል ላቦራቶሪ ቴክኖሎጂ 13 ተማሪዎች ሲሆኑ ፥ በምረቃው ሥነ ስርዓርት ላይ የዩኒቨርሲቲው ቻንስለር የሆኑት የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን ብጹእ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ፣ ብጹዕ አቡነ አንትዋን ካሚሌሪ በኢትዮጵያ በጂቡቲ እና በሱማሊያ የቅድስት መንበር ተወካይ ፣ ክቡር ዶ/ር አባ ተሾመ ፍቅሬ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ጸሃፊ እና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርስቲ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፣ ወንድም ሃንስ ስቴቨን የዩኒቨርሲቲው ፕረዚዳንት ፣ ክቡር አምባሳደር ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ፣ የተማሪዎች ወላጆች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። የዚህን የ2015 ዓ.ም. የተማሪዎች ምረቃ ሥነ ስርዓት በእጅጉ ካደመቁት መሃል የልደታ ካቴድራል ቤተክርስቲያን መዘምራን ይገኙበታል።

የምርቃት ሥነ ስርዓቱን በጸሎት እና በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ የምረቃውን ሥነ ስርዓት አምላክ እንዲባርከው እና በተለይ ደግሞ በዚህ በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚሰጠውን ትምህርት እና ምርምር እንዲባርክ ፥ በዚህ ተቋም የሚሰሩ የክርስቲያን ወንድሞችን ፣ የኦርሶላይን ማህበር እህቶችን ፣ መምህራንን ፣ ሠራተኞችን እና ተማሪዎችን ቸሩ አምላክ እንዲባርክ ጸሎታቸውን አድርሰዋል። ብጹእ ካርዲናሉ አክለዉም ሁሉም ሰው በየእምነቱ ለምንወዳት ሃገራችን ኢትዮጵያ ሠላምን ፣ ፍቅርን እና አንድነትን እንዲሰጥ አጥብቀው እንዲጸልዩ አበክረው ጠይቀዋል።  

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ጸሃፊ እና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ክቡር ዶ/ር አባ ተሾመ ፍቅሬ ለተማሪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት መማር ማለት አንድ ሲደመር አንድ ሁለት ነው ማለት ሳይሆን ፥ መማር ማለት የባህሪ ለውጥ ማምጣት እንደሆነ ፣ መማር ማለት እግዚያብሄርን መፍራት መጀመር እንደሆነ ፣ ክፉዉን ጥሎ ደጉን ማንሳት እንደሆነ ፣ ውሸትን ጥሎ ደጉን መያዝ እንደሆነ እንዲሁም ጨለማን ጥሎ ብርሃንን መያዝ እንደሆነ ተመራቂ ተማሪዎቹን መክረዋል። አባ ተሾመ አክለውም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በትምህርት ላይ ጉልበቷን ፣ ሃሳቧን ፣ ዕውቀቷን እና ሃብቷን የምታጠፋው የእናንተን ትምህርታዊ ዕውቀት መጨመር ላይ ብቻ ለማተኮር ሳይሆን ፥ የተማረ ሰው ለማህበረሰቡ ችግር ፈቺ እንጂ እራሱ ችግር እንዳይሆን ተስፋ ሰንቀን ነው የምናዘጋጃችሁ ብለዋል። በመጨረሻም ተማሪዎቹ ወደ ማህበረሰባቸው ሲወጡ ዕውቀትን ይዘው በማህበረሰቡ ዉስጥ ያሉ ችግሮችን ከእግዚያብሄር ጋር ሆነው መፍታት እንዲችሉ አሳስበዋል።

ዩኒቨርሲቲውን ከሚያስተዳድሩት የክርስቲያን ወንድሞች ማህበር አባል አንዱ የሆኑት የአካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕረዚዳንት ወንድም ጌታቸው አለማየሁ እንደተናገሩት ይህ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመ 12 ዓመታት የሆነው ሲሆን ፥ ዝዋይ ከተማ ባለው ካምፓሱም ተማሪዎችን በሜዲካል ሳይንስ ፣ ማህበራዊ ሥራዎች ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ሜዲካል ላቦራቶሪ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል። ዩኒቨርሲቲው እስከ ዛሬ ድረስ ለዘጠኝ ጊዜያት ያህል ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች አሰልጥኖ አስመርቋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ሲያሰለጥናቸው የነበሩ ተማሪዎችን አስመረቀ
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ሲያሰለጥናቸው የነበሩ ተማሪዎችን አስመረቀ
30 July 2023, 10:31