ፈልግ

ወደ ሊዝበን የተጓዙት የኢስቶኒያ መንፈሳዊ ወጣት ነጋዲያን ወደ ሊዝበን የተጓዙት የኢስቶኒያ መንፈሳዊ ወጣት ነጋዲያን 

የኢስቶኒያ መንፈሳዊ ነጋዲያን ወደ ዓለም የወጣቶች ቀን ደስታን እና ምስክርነትን እንደሚያመጡ ገለጹ

በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ከሐምሌ 26-30/2015 ዓ. ም. ድረስ በሚከበረው የዓለም ወጣቶች ቀን ለመገኘት ከኢስቶኒያ መንፈሳዊ ንግደት የጀመሩት ወጣቶች ወደ ፌስቲቫሉ ደስታን እና ምስክርነትን ይዘው መምጣት እንደሚፈልጉ ገልጸው የጉዞአቸውን አደራ ለእግዚአብሔር እና የአገራቸው የእግዚአብሔር አገልጋይ ለነበሩ ለሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤድዋርድ ፕሮፊትሊች መጠታቸውን ገለጹ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ጥቂት የኢስቶኒያ ወጣት ነጋዲያን በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን በሚከበረው የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት ሰኞ ሐምሌ 17/2015 ዓ. ም. ጉዞ መጀመራቸውን በኢስቶኒያ ሐዋርያዊ አስተዳደር የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ወ/ሮ ማርጅ-ማሪ ፓያስ ገልጸዋል።

ወ/ሮ ማርጅ-ማሪ በገለጻቸው 15 ወጣቶችን እና ሁለት ካኅናትን ያካተተ የልኡካን ቡድን በዚህ ዓመት በዝግጅቱ ላይ ለመሳተፍ ከአውሮፓ አገራት ከሚመጡ የልኡካን ቡድን መካከል በጣም ትንሹ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው፥ የኢስቶኒያ ወጣት ነጋዲያን ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም ስለ እምነታቸው ለመመሥከር እና ደስታቸውን ለሌሎች ለመካፈል እንደጓጉ አስረድተዋል።

“ዓለማችን ደስታና ሰላም ትፈልጋለች” ያሉት ወ/ሮ ማርጅ-ማሪ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ “በድምሩ 17 ልኡካን ያሉበት የወጣቶች ቡድን ይህን ደስታ እና ሰላም በሊዝበን ከሚያገኟቸው ሌሎች ወጣት ነጋዲያን ጋር ለመካፈል ይፈልጋሉ" ብለዋል።

የእግዚአብሔር በረከት

ኢስቶኒያ ወደ 6,000 የሚጠጉ ካቶሊካዊ ምዕመናን እንዳሏት የገለጹት ወ/ሮ ማርጅ-ማሪ፥ እምነታቸውን አጥብቀው የያዙት ምዕመናኑ በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል። “ኢስቶኒያ እምነታቸውን በሚገባ የሚለማመዱ ብዙ ምዕመናን እንደሌሏት ቢያወቅም ነገር ግን ወጣቶቻቸው የካቶሊክ እምነት አስፈላጊነት እና በልባቸው ውስጥ ሥር የሰደደ መሆኑን ማሳየት ይፈልጋሉ” ብለዋል ወ/ሮ ማርጅ-ማሪ።

እንደ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን አካል የኢስቶኒያ ወጣት ነጋዲያን በሳምንቱ ውስጥ በሚከናወኑ የተለያዩ ዝግጅቶች፥ በመስዋዕተ ቅዳሴ፣ በሌሎች የጸሎት ሥነ-ሥርዓቶች እና የትምህርተ ክርስቶስ ስብሰባዎችን እንደሚሳተፉ አስረድተዋል።

የወጣት ነጋዲያኑ መሪ እና በታሊን የቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ካቴድራል ቁምስና መሪ ካኅን አባ ቶማስ ማቴርና የተሳትፎአቸው ዋናው ክፍል ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በመሆን እሑድ ሐምሌ 30/2015 ዓ. ም. የሚያሳርጉት የዓለም ወጣቶች ቀን የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

አባ ቶማስ ንግደታቸውን ከመጀመራቸው በፊት እንደተናገሩት የኢስቶኒያ ወጣቶች መንፈሳዊ ጉዞን  እግዚአብሔር እንደሚመራ ያላቸውን እምነት ገለጸው፥ ወ/ሮ ማርጅ-ማሪም በበኩላቸው፥ “አባ ቶማስ እግዚአብሔር ትንሹን የኢስቶኒያ ቡድንን ይባርካል የሚል እምነት አላቸው” ብለዋል።

ቅዱስ ባልደረባ

እንደ መንፈሳዊ ነጋዲያን ወጣቶቹ የእግዚአብሔር አገልጋይ ለነበሩት ለብጹዕ ኤድዋርድ ፕሮፊትሊች የቀረበ ጸሎት የሚገኝበት ካርድ ተሰጥቷቸዋል። የብጹዕ ኤድዋርድ የቅድስና ሂደት በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት በኩል እየተካሄደ እንደሚገኝ ታውቋል።

ጀርመናዊው ተወላጅ እና የኢየሱሳውያን ማኅበር አባል የነበሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤድዋርድ ፕሮፊትሊች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1931 ዓ. ም. ጀምሮ የኢስቶኒያ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ በመሆን ያገለግሉ ሲሆን፥ ወደ ሳይቤሪያ በመሰደድ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 22/1942 ዓ. ም. በኪሮቭ በሚገኘው የሶቪየት እስር ቤት ውስጥ ሰማዕትነትን ተቀብለዋል።

ነጋዲያን ወጣቶቻቸው እምነታቸውን ለመመስከር፣ ደስተኛ ለመሆን እና በጉዞአቸው ሁሉ እርስ በርስ ለመደጋገፍ ድፍረት እንዲኖራቸው ወደ ብጹዕ ኤድዋርድ በየቀኑ እንደሚጸልዩ፥ በኢስቶኒያ ሐዋርያዊ አስተዳደር የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ወ/ሮ ማርጅ-ማሪ ፓያስ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

 

 

27 July 2023, 16:46