ፈልግ

ሱዳናውያን በዋና ከተማይቱ ካርቱም እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ሸሽተው ንብረታቸውን ይዘው ሲሸሹ ሱዳናውያን በዋና ከተማይቱ ካርቱም እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ሸሽተው ንብረታቸውን ይዘው ሲሸሹ  (AFP or licensors)

በደ.ሱዳን የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ከሱዳን የመጡ ስደተኞችን መልሶ የማቋቋም እቅድ እንዲኖር አሳሰበች

የጁባ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት እስጢፋኖስ አሜዩ ማርቲን ሙላ ሁሉም ሀገረ ስብከቶች በጦርነት ከምታመሰው ሱዳን ሸሽተው ለሚመጡ ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች የድንገተኛ አደጋ ማዕከል እንዲያቋቁሙ አሳሰቡ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

 በሱዳን ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት ሀገሪቱን እያወደመ እና እየተፈናቀሉ ያሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ እና የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦቱ በፀጥታ እጦት እና በገንዘብ እጥረት ሳቢያ በመስተጓጎሉ የተነሳ የጁባ ሊቀ ጳጳስ እስጢፋኖስ አሜዩ ማርቲን ሙላ በደቡብ ሱዳን የሚገኙ የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች የአደጋ ጊዜ ማቆያ እና ማገገሚያ ማዕከል ለስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች እንዲያቋቁሙ ደጋግመው ጠይቀውል።
ሊቀ ጳጳሱ ጥሪያቸውን ያቀረቡት ባለፈው ሳምንት ዓርብ ሰኔ 23 2015 ዓ.ም. በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ በተጠናቀቀው የደቡብ ሱዳን የካቶሊክ ጳጳሳት የክልል ምክር ቤት መድረክ ላይ ነው።

የድንገተኛ አደጋ ጊዜ ዕርዳታ

ሊቀ ጳጳስ አሜዩ እንዳሉት በሱዳን ያለውን ቀውስ ሸሽተው የሚሰደዱ ሰዎች በሀገሪቱ ውስጥ እንዲሰፍሩ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉ የቤተክርስቲያን ድርጅቶች በሰብአዊ አደጋዎች ላይ የሚያደርጉትን እገዛ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አበረታተዋል።
ሊቀ ጳጳሱ በካቶሊክ ሬድዮ ኔትዎርክ እንደተናገሩት “ጉድዩ ቀላል አይደለም ፥ ነገር ግን እየተቆጣጠራችሁት ነው ፥ በደቡብ ሱዳን ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ አልደረሰም ነገር ግን እየተፋጠነ ነው ፥ ያለንበትን የአደጋ ጊዜ ዕርዳታ በማድረግ እንድትቀጥሉ አበረታታለሁ” ብለዋል።
ሱዳን ወደ ትርምሱ የገባችው ባለፈው ሚያዚያ 7 2015 ዓ.ም. ሲሆን ፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሀገሪቱ ለፕሬዝዳንት ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ታማኝ ለሆኑት በሱዳን ጦር ሃይሎች (SAF) እና በምክትል ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራው በፈጣን የድጋፍ ሰጪ ሃይሎች (RSF) መካከል ከባድ የትጥቅ ግጭቶችን እያስተናገደች ነው። ግጭቱም እስከ አሁን ከ3,000 በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል ፥ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ቆስለዋል።
ውጊያው የግጭት ማዕከል ወደ ሆነችው ዳርፉር በተለይም በደቡብ ዳርፉር ዋና ከተማ ኒያላ ድረስ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በደቡብ ኮርዶፋን እና የተከፋፈለው የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ ቡድን በሱዳን ጦር ላይ ማጥቃት የጀመረበት በብሉ ናይል ደቡባዊ ክልሎች ድረስ ዘልቋል።

2.5 ሚሊዮን ህዝብ ተፈናቅለዋል

እንደ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ግምት ከሆነ እስካሁን 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ከሱዳን ውስጥ እና ውጭ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ተፈናቅለዋል ፥ ከ137,000 በላይ ሰዎች ደግሞ እስከ ሰኔ 20 2015 ዓ.ም. ድረስ ደቡብ ሱዳን ደርሰዋል።
ከ16,000 በላይ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን 159,060 ሱዳናውያን ስደተኞችም ቻድ ገብተዋል። እንዲሁም በግምት 15,335 የሚሆኑ ሰዎች ወደ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ መድረሳቸውም ታውቋል።

ለደቡብ ሱዳን ሠላም እና እርቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው

በሱዳን ካለው የጦርነት እውነታ ጎን ለጎን ፥ ሊቀ ጳጳስ አሜዩ የቤተክርስቲያን መሪዎች በ2010 ዓ.ም. የተጀመረውን የሠላም ጥረቶችን የሚያበላሹ በታጣቂዎች መሃል እንዲሁም በአጠቃላይ የሚነሱ ግጭቶች ተባብሰው እንዳይሄዱ በደቡብ ሱዳን የሠላም ግንባታ እና እርቅ ላይ የሚያደርጉትን ጥረቶች አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
“ለሠላም እና እርቅ ቅድሚያ እንስጥ” ያሉት ጳጳሱ ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ፥ የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ እና ሬቨረንድ ኢየን ግሪንሺልድስ በየካቲት 2015 ዓ.ም. በደቡብ ሱዳን ባደረጉት ታሪካዊ እና ሃዋሪያዊ የጋራ ጉብኝት ወቅት ያስተላለፉትን የማኅበረ ቅዱሳን መልእክት ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም የኃይማኖት አባቶች ቀዳሚ ተግባራትን እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።
“እኛ ጎብኚዎቻችን በተለይም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ያስተላለፉልንን ክርስቲያናዊ መልዕክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆመናል” ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ አሜዩ በንግግራቸው በደቡብ ሱዳን የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የአብሮነት ቡድኖች በደቡብ ሱዳን ለመሥራት ያሳዩትን ቁርጠኝነትም አድንቀዋል።
 

03 July 2023, 15:51