ፈልግ

ፕሮፌሰር ማርኮ ካርሎ ፓሳሮቲ በሚላን በተካሄደውትምህርታዊ ሴሚናር ላይ ንግግር ሲያደርጉ ፕሮፌሰር ማርኮ ካርሎ ፓሳሮቲ በሚላን በተካሄደውትምህርታዊ ሴሚናር ላይ ንግግር ሲያደርጉ 

የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ‘ሰውሰራሽ አስተዉሎትን’በሥነ ምግባር የተደገፈ እንዲሆን ግፊት ያደርጋሉ ተባለ

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ስምንት የካቶሊክ ዩኒቨርስቲዎች በሚላን ከተማ በተደረገ የሁለት ቀን ኮንፈረንስ ስለ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም በአማሪኛው አቻ ትርጉም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስላለው ማህበራዊ ተፅእኖ ወጣቶችን ለማስተማር እና ምርምር ለማድረግ የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አዘጋጅተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሳክሩ (SACRU) የተባለው ዓለም አቀፉ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ጥምረት በጣሊያንዋ ሚላን ከተማ በሚገኘው ‘ልበ ቅዱስ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ’ የሁለት ቀን ሳይንሳዊ የትምህርት ኮንፈረንስ አዘጋጅቷል።
በቺሊ፣ ስፔን ፣ አውስትራሊያ ፣ አሜሪካ ፣ ጃፓን ፣ ፖርቱጋል ፣ ብራዚል እና ስፔን ከሚገኙ ስምንት የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከ80 በላይ ፕሮፌሰሮች እና ተመራማሪዎች ሰው ሰራሽ አስተውልሆት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ስላሉት ደካማ ጎኖች ወይም ተግዳሮቶች እና እድሎች ተወያይተዋል።
“የወደፊት የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች በሰው ሰራሽ አስተውልሆ ዘመን” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ጉባኤው ላይ የተሳተፉት ባለሙያዎች ከተለያዩ የሰብአዊነት እና የሳይንስ ዘርፎች የተውጣጡ ናቸው።

የሳይንስ እና የሰብአዊነት ድንበር መጨረሻ

ተመራማሪዎቹ ከሃምሌ 6-7 2015 ዓ.ም. ባደረጉት የተለያዩ ውይይቶች ሰው ሰራሽ አስተውሎ በተፈጥሮ ሳይንስ እና በማህበራዊ ሳይንስ መካከል ሁለገብ መደራረብን ወይም መጠላለፍን ያመጣል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።
የልበ ቅዱስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ፕሮፌሰር ማርኮ ካርሎ ፓሳሮቲ በሰብአዊነት እና በሳይንስ ትምህርቶች መካከል ያለው መለያየት በሰው ሰራሽ አስተውልሆት በመተግበሩ ምክንያት ወደ ቀድሞው ደረጃ ሊወርድ ይችላል ብለዋል ።
ፕሮፌሰር ፓሳሮቲ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ጥምረት ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “የሰው ልጆች ምንጊዜም ቢሆን መረጃን ይጠቀማሉ ፤ ነገር ግን በጣታቸው ጫፍ ላይ ያን ያህል መጠን ያለው መረጃ እና ይህን የመሰለ ከፍተኛ ጥራት ያለው አቀነባበር አግኝተው አያውቁም” ብለዋል።
የሰው ሠራሽ አስተውልሆ እድገቶች ለተመራማሪዎች አዳዲስ ተግዳሮቶችን ወይም ፈተናዎችን ይፈጥራሉ ተብሎም ይታሰባል።
“ይህ ጠቃሚ ግኝት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ መረጃን እና ግንኙነቶችን በእጃቸው ውስጥ ያስቀምጣል ፥ ይህም የምርምር ሥራዎቻቸውን ማንም ሰው እንዲያባዛ ያደርግባቸዋል” ብለዋል ፕሮፌሰሩ።

የሰው ሠራሽ አስተውልሆ ዕድገትን በሥነ ምግባር መምራት

የዓለም አቀፉ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ትሥሥር ፕሮፌሰሮች ሰው ሠራሽ አስተውልሆትን በትክክል እና በስነ ምግባር ከተጠቀምንበት ፥ ሰዎች ስለ ዓለም እና ስለ ራሳቸው የበለጠ ግንዛቤ እንዲያገኙ ማስቻል እንደሚችል ተስማምተዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች የሰው ሠራሽ አስተውልሆ ቴክኖሎጂዎችን ዝግመተ ለውጥ ለመቀበል እና የሰው ልጅን ማዕከል በሚያደርግ መንገድ ለመገልገል አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
“የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ስለ ሰው ሠራሽ አስተውልሆ ተጽእኖ የማሳወቅ ጠንካራ ግዴታ አለባቸው” ብለዋል ፕሮፌሰር ፓሳሮቲ ፥ በማከልም “ይህን ተፅእኖ ማወቅ እና ጥቅም ላይ ማዋል የሰውን ልጅ ክብር ለማስጠበቅ ፈቃደኛ ወደ ሆነ አቀራረብ እና የሰው ልጅን ሥነ ምግባራዊ ሃላፊነት በማሽን እንዳይወከል ለማድረግ ይጠቅማል” ብለዋል።

የማስተማር ተልዕኮ በሰው ሠራሽ አስተውልሆ ዘመን

በሰው ሠራሽ አስተውልሆ ላይ ለቀረቡት ተግዳሮቶች ምላሽ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ህብረት ወጣቶችን ለማስተማር እና በስምንቱ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ትብብርን ለመፍጠር የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ቀርጿል።
የቅዱስ ልብ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ዳይሬክተር እና የካቶሊክ ዩኒቨርስቲዎች ህብረት ዋና ጸሃፊ ፕሮፌሰር ፒየር ሳንድሮ ኮኮንሴሊ እንደተናገሩት ጉባኤው በትምህርት ዘርፍ ውስጥ ያለውን ተለዋዋጭ የቴክኖሎጂ ገጽታ እንዴት መቀበል እንደሚቻል ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።
“ስምንቱ ዩኒቨርሲቲዎች አንድ የጋራ ተልዕኮ እና ራዕይ አላቸው ወጣቱን ትውልድ ለማስተማር እና በህብረተሰቡ ላይ እውነተኛ ተጽእኖ ያላቸውን ጥናቶች ለማበልፀግ ነው” ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲዎች የማስተማር እና የምርምር ተልእኮዎቻቸውን ከሰው ሠራሽ አስተውልሆ ዘመን ጋር እንዴት ማስማማት እንደሚችሉ ለሕዝብ ለማቅረብ ከኮንፈረንሱ የተገኙ ውጤቶች ተዘጋጅተው በዓመቱ ውስጥ ይታተማሉ።

ስለ ሳክሩ (SACRU)

SACRU (Strategic Alliance of Catholic Research Universities) ( የካቶሊክ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ስትራቴጂካዊ ጥምረት) በሚላን በሚገኘው የልበ ቅዱስ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት የሚንቀሳቀስ በአራት አህጉራት የሚገኙ የስምንት የካቶሊክ ዩኒቨርስቲዎች ጥምረት ሲሆን ፥ በካቶሊክ ማህበራዊ ትምህርት አነሳሽነት ወይ አርዓያነት ለጋራ ጥቅም እና የሁለገብ ጥናት ሲባል ዓለም አቀፋዊ ትምህርትን ለማበረታታት እንዲሁም ማስተዋወቅን ዓላማ ያደረገ ትብብር ነው።
ጥምረቱ የተመሰረተው በ2012 ዓ.ም. ሲሆን ፥ የአውስትራሊያ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ (አውስትራሊያ) ፣ ቦስተን ኮሌጅ (አሜሪካ) ፣ ፖንቲፊሺያ ዩኒቨርሲቲ ካቶሊካ ዴ ቺሊ (ቺሊ) ፣ ፖንቲፊሺያ ዩኒቨርስቲ ካቶሊካ ዶ ሪዮ ዴ ጄኔሮ (ብራዚል) ፣ ሶፊያ ዩኒቨርሲቲ (ጃፓን) ፣ ካቶሊካ ፖርቱጋል (ፖርቱጋል) እና ዩኒቨርስቲ ራሞን ሉል (ስፔን) ዩኒቨርስቲዎችን ያጠቃልላል።
 

19 July 2023, 13:51