ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሞንጎሊያ ለሚያደርጉት  ሐዋርያዊ ጉብኝት አርማ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሞንጎሊያ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አርማ 

በሞንጎሊያ የሚኖሩት የካቶሊክ ሲስተር የጳጳሱ ጉብኝት እዛ ያሉ ሚስዮናውያንን እንደሚያበረታታ ገለጹ

በኡላንባታር ከተማ ሃገረስብከት እያገለገሉ የሚገኙት ህንዳዊ ሚስዮናዊ ሲስተር አግኔስ እንደገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በመጪው ነሓሴ 25 እስከ 29 2015 ዓ.ም. በሞንጎልያ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝትን በጉጉት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሲስተር አግነስ ጋንግሜይ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በሞንጎሊያ ‘የማርያም ሴት ልጆች’ ማህበር አባል ሆነው እያገለገሉ የሚገኙ ሚስዮናዊ ናቸው። ሲስተሯ ከሞንጎሊያ ዋና ከተማ ኡላንባታር ወጣ ብሎ በሚገኘው ኦቢት ውስጥ 100 የሚጠጉ ህጻናት ተማሪዎች ከመዋዕለ ህጻናት እስከ አንደኛ ደረጃ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ውስጥም አስተማሪም ናቸው።
ሲስተር አግነስ ለሁለት ዓመት ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ህንድ ተልከው ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ሞንጎሊያ ይመለሳሉ። ነገር ግን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ሰፊና ብዙ ህዝብ ወደሌላት የምስራቅ እስያ ሀገር ሞንጎሊያ የሚያደርጉትን ሃዋሪያዊ ጉብኝት እንደሰሙ በጣም ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ሲስተር አግኔስ ከኤሲያ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “በዚህ ሰዓት ያለኝ ስሜት ቅድስት ኤልሳቤጥ የማርያምን ጉብኝት በተቀበለችበት ወቅት በደስታ ብዛት ‘የጌታዬ እናት ወደ እኔ መጥታ እንዴት ይሆንልኛል?’ ብላ ካለችው ስሜት ጋር ሊመሳሰል ይችላል” ብለዋል።
በሞንጎሊያ የሚገኘውን የካቶሊክ ማህበረሰብ “በጣም ወጣት እና በጣም ትንሽ” ሲሉም ገልጸው ፥ “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወደ ማህበረሰባችን መጥተው ስለሚጎበኙን ልዩ የሆነ መብት ፣ ክብር እና በረከት ይሰማኛል” ብለዋል።
“እኛ 1500 የሚጠጉ የተጠመቁ ካቶሊኮች ብቻ ነው ያሉን” ሲሉ ፥ ተልእኮዋቸውም ከተመሰረተች 30 ዓመታት ብቻ በሆናት ቤተክርስቲያን ውስጥ ከሚያገለግሉ ደናግላን ውስጥ አንዷ መሆናቸውንም ገልፀዋው “በቫቲካን እና በሞንጎሊያ ምድር መካከል የበለጠ ግንኙነት እንዲኖር ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉም ተናግረዋል።
ሲስተር አግነስ ደናግላን እህቶች ብዙ ጊዜ ተስፋ አድርገው ለዚህ አጋጣሚ እንደጸለዩ ተናግረው ፥ “በመጨረሻ እግዚአብሔር ጸሎታችንን ሰማ!” ብለዋል።
“የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት መገኘት ብቻውን ብዙ ይናገራል ፥ ለማመስገንም በቂ ቃላት የሉንም” በማለት ንግግራቸውን ሲቀጥሉ ፥ “ይህ ጉብኝት የካቶሊክ ማህበረሰብን እምነት እንደሚያጎለብት እና እሳቸውንም መንጋውን እንደሚንከባከብ ጥሩ እረኛ እንደሚያያቸው” ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በማከልም “ወደዚህ ለሚላኩ ሚስዮናውያን የቪዛ ጉዳይ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ እንደሚረዳን ተስፋ እናደርጋለን። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ካጋጠሙን ችግሮች አንዱ ይህ ነው” ሲሉም ስለነበረው ችግር ተናግረዋል።
በቫቲካን እና በሞንጎሊያ መካከል መቀራረብ እንደሚፈጠር ያላቸውን ተስፋ ደጋግመው የገለጹት ሲስተር አግነስ ፥ ይህም ሚስዮናውያን በተለያዩ የትምህርት ፣ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ፣ በጤና እና በማህበራዊ ልማት ዘርፎች ሐዋርያዊነታቸውን እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል ብለዋል።
እ.አ.አ. ከ2020 ጀምሮ የኡላንባታር ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ጆርጂዮ ማሬንጎ በኩል እንዲጎበኙን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ የቀረበላቸውን ግብዣ ስለተቀበሉ ያላቸውን አድናቆት እና ምስጋናንም ጭምር ገልጸዋል። በመጨረሻም “ለቺንግጊስ ካን ምድር እና ለህዝቡ ፣ ለመላው ካቶሊኮች ፣ እንዲሁም ለቡድሂስቶች እና ለሻማኒዝም ተከታዮች የተትረፈረፈ በረከት እንዲሆን እንጸልያለን” በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
 

13 July 2023, 17:15