ፈልግ

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ ፍቅር በቤተስብ ውስጥ  

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በቃለ እግዚአብሔር ብርሃን እይታ

መጽሐፍ ቅዱስ በቤተሰቦች፣ በልደቶች፣ በፍቅር ታሪኮችና በቤተሰብ ቀውሶች የተሞላ ነው፡፡ ይህም ሁከትም ብርታትም ካለው (ንጽ. ዘፍ. 4) በአዳምና በሔዋን ቤተሰብ ምሥረታ ከሚጀምረው ከመጀመሪያው ገጽ አንሥቶ የሙሽራይቱንና የበጉን ሠርግ እስከምናይበት (ራእይ 21፡ 2፣ 9) የመጨረሻው ገጽ ድረስ ያለውን ሁኔታ ይመለከታል፡፡ ኢየሱስ በዓለትና በአሸዋ ላይ ስለ ተሠሩ ሁለት ቤቶች የሰጠው ማብራሪያ  (ንጽ. ማቴ. 7፡ 24-27)፣ በአባሎቻቸው ነጻ ድርጊት ላይ ተመሥርተው የተቀረጹ የበርካታ ቤተሰቦችን ሁኔታ ያሳያል፡፡ ምክንያቱም፣ ባለ ቅኔው እንዳለው፣ ‹‹ እያንዳንዱ ቤት የብርሃን መቅረዝ ነውና››፡፡ ስለዚህ፣ እኛም ከመዝሙረኛው ጋር ሆነን፣ ዛሬም ቢሆን በአይሁድም ሆነ በክርስትና የሰርግ ሥርዓተ አምልኮዎች ላይ የሚያስተጋባውን መዝሙር እየዘመርን ወደ እነዚህ ቤቶች እንግባ፡- እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ፤ በመንገዱም የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው፡፡ የድካምህን ፍሬ ትበላለህ፤ ትባረካለህ፤ ይሳካልሃልም፡፡ ሚስትህ በቤትህ፣ እንደሚያፈራ ወይን ናት፤ ወንዶች ልጆችህ በማዕድህ ዙሪያ፣ እንደ ወይራ ተክል ናቸው፡፡ እነሆ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው፣ እንዲህ ይባረካል፡፡እግዚአብሔር ከጽዮን ይባርክህ፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፣ የኢየሩሳሌምን ብልጽግና ያሳይህ፤ የልጅ ልጅም ለማየት ያብቃህ፡፡ በእስራኤል ላይ ሰላም ይውረድ” (መዝ 128)፡፡

አንተና ሚስትህ

በማእድ ላይ የተቀመጠውን የዚህን ጸጥ ያለ ቤትና ቤተሰብ  ድባብ እስቲ እንመልከት፡፡ መሃል ላይ የየግል የሕይወት ታሪክ ያላቸው አባትና እናት ተቀምጠው እናያቸዋለን፡፡ እነርሱም ክርስቶስ ራሱ ‹‹ ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን?›› (ማቴ. 19፡ 4)  ሲል የተናገረው የጥንቱ መለኮታዊ ዕቅድ ተምሳሌት ናቸው፡፡ በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ፣- ‹‹ስለዚህ ሰው፣ አባቱንና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ››(ዘፍ. 2፡ 24) የሚለውን ትእዛዝ ሲያስተጋባ እንሰማለን፡፡

የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፎች የባልና ሚስትን ጥልቅ እውነታ ያሳያሉ፡፡ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ገጾች በርካታ ግልጽ የሆኑ ሐሳቦችን ያቀርባሉ፡፡ የመጀመሪያውና ኢየሱስ አሳጥሮ ያቀረበው ሐሳብ፣ ‹‹ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው››( ዘፍ. 1፡ 27) የሚል ነው፡፡ እዚህ ላይ ‹‹የእግዚአብሔር መልክ›› የሚለው ቃል ባልና ሚስትን፣ ‹‹ወንድና ሴትን›› የሚገልጽ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህ ታዲያ ጾታ የራሱ የእግዚአብሔር ሀብት ወይም ፣ አንዳንድ የጥንት ሃይማኖቶች እንደሚናገሩት፣ እግዚአብሔር መለኮታዊት ሴት ጓደኛ አለው ያስብላልን? በእርግጥ መልሱ አይደለም ነው፡፡ በቅድስት አገር በከነዓናውያን ዘንድ የነበረውን ጣኦት አምልኮ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት በግልጽ እንደሚቃወም እናውቃለን፡፡ የእግዚአብሔር ልዕልና እንደ ተጠበቀ ነው፤ እርሱ ፈጣሪም እንደ መሆኑ፣ የባልና ሚስት ፍሬያማነት የእርሱ ሕያውና ውጤታማ ‹‹መልክ››፣ የእርሱ የፈጠራ ሥራ ጉልህ ምልክት ነው፡፡

የሚዋደዱና ልጆችን የሚወልዱ ባልና ሚስት ፣ በአሥርቱ ትእዛዛት እንደ ተከለከለ የድንጋይ ወይም የወርቅ ጣኦት አምልኮ ሳይሆኑ፣ ፈጣሪና አዳኝ እግዚአብሔርን የሚገልጹ ሕያው ምሥሎች ናቸው፡፡ በመሆኑም፣ ፍሬያማ ፍቅር የእግዚአብሔር ውስጣዊ ሕይወት ተምሳሌት ይሆናል (ንጽ. ዘፍ. 1፡ 28፤ 9፡ 7፤ 17፡ 2-5፣ 16፤ 28፡ 3፤ 35፡ 11፤ 48፡ 3-4)፡፡ የዘፍጥረት ታሪክ  ‹‹ከካህናዊ ባህል›› ቀጥሎ ከተለያዩ የሥነ ተዋልዶ ታሪኮች ጋር ሊተሳሰር የቻለውም ለዚህ ነው ( ንጽ. 4፡ 17-22፣ 25-26፤ 5፤ 10፤ 11፡ 10-32፤ 25፡1-4፣ 12-17፣ 19-26፤ 36)፡፡   የባልና ሚስት ልጆችን የመውለድ ችሎታ የድኅነት ታሪክ የሚጓዝበት መንገድ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ፣ የባልና ሚስት ፍሬያማ ግንኙነት የራሱን የእግዚአብሔርን ምሥጢር ለመረዳትና ለማብራራት ጥሩ ተምሳሌት ይሆናል፤ ምክንያቱም ስለ ቅድስት ሥላሴ ባለው ክርስቲያናዊ አመለካከት፣ እግዚአብሔር አብ፣ ወልድና የፍቅር መንፈስ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ሥላሴ መለኮት የፍቅር ሱታፌ ሲሆን፣ ቤተሰብ ደግሞ የእርሱ ሕያው ነጸብራቅ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ይህን ጉዳይ ሲያብራሩ፣- ‹‹ የአምላካችን ጥልቁ ምሥጢር የብቸኝነት ሳይሆን፣ የቤተሰባዊነት ነው፤ ምክንያቱም እርሱ በውስጡ አባትነት፣ ወልድነትና የቤተሰብ ባሕርይ የሆነው ፍቅር አለውና፡፡ በመለኮታዊ ቤተሰብ ውስጥ፣ ያ ፍቅር መንፈስ ቅዱስ ነው››፡፡ (6)  ስለዚህ፣ ቤተሰብ ከእግዚአብሔር ሕልውና ጋር የተገናኘ ነው፡፡ (7) ይህ ሥላሴያዊ ገጽታ ይበልጥ ግልጽ የሚሆነው ባልና ሚስትን ከክርስቶስና ከቤተክርስቲያን ጋር በሚያገናኘው በቅዱስ ጳውሎስ ነገረ መለኮት ትምህርት ውስጥ ነው (ንጽ. ኤፌ. 5፡ 21-33)፡፡

ኢየሱስ ስለ ጋብቻ ሲናገር፣ በሁለተኛው ምዕራፉ ላይ ስለ ባልና ሚስት ድንቅና ዘርዘር ያለ ሥዕል ወደሚያሳየው ወደ ሌላው የኦሪት ዘፍጥረት ገጽ ይመራናል፡፡ አንደኛ፣ ሰው  በእንስሳትና በዙሪያው ባለው ዓለም ውስጥ የብቸኝነት ስሜቱን ሊያቃልልለት የሚችል ‹‹ለእርሱ የሚስማማ ረዳት›› ( ዘፍ. 2፡ 18፣ 20) እንደሚፈልግ እናያለን፡፡  ፍቅርን በተመለከተ፣ ጸጥታ ሁልጊዜ ከቃላት በላይ ነውና፣ የጥንቱ የዕብራውያን አባባል  ጸጥ ባለ ውይይት ውስጥ  ቀጥታ ፣ የፊት ለፊት፣ የዐይን ለዐይን ግንኙነት እንዲኖር ያሳስባል፡፡ ይህ ግንኙነት ፣ የእግዚአብሔርን ፍቅርና  በመጽሐፍ ቅዱስ የጥበብ አነጋገር ‹‹የሰው ትልቁ ሀብት፣ ለእርሱ የሚስማማ ረዳትና ደጋፊ ዓምድ›› የሆነውን ‹‹አንተነትን›› (ሲራክ 36፡24) የሚገልጽ መልክ ያለው  ግንኙነት ነው፡፡ ወይም በመኀልየ መኀልይ ዘሰሎሞን ‹‹ ውዴ የእኔ ነው፣ እኔም የእርሱ ነኝ፤… እኔ የውዴ ነኝ፣ ውዴም የእኔ ነው›› (ማኅ. 2፡16፤ 6፡ 3) በማለት ፍቅርዋንና ራስዋን አሳልፋ መስጠትዋን ድንቅ በሆነ መዝሙር እንደምትገልጽ ሴት ነው፡፡

የሰውን ብቸኝነት የሚያስወግድ ይህ ግንኙነት ለአዲስ ልደትና ለቤተሰብ መሠረት ይሆናል፡፡ የጊዜና የቦታ ባለቤት የሆነው አዳም፣ ከሚስቱ ጋር በመሆን፣ አዲስ ቤተሰብ መሠረተ፡፡ ኢየሱስም ስለዚህ ጉዳይ  ኦሪት ዘፍጥረትን ጠቅሶ ሲናገር፣- ‹‹ሰው ከሚስቱ ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ›› ይላል (ማቴ. 19፡5፤ ዘፍጥ. 2፡24)፡፡ በጥንቱ የዕብራውያን አነጋገር ‹‹ ይጣመራል››፣ ‹‹ይተሳሰራል›› የሚለው ቃል፣ ጥልቅ ኅብርን፣ አካላዊና ውስጣዊ ቅርበትን የሚገልጽ ከመሆኑ የተነሣ፣ ‹‹ነፍሴ አንተን የሙጥኝ ብላለች›› (መዝ. 63፡ 8) የሚለውን በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ኅብረት ለማመልከት ያገለግላል፡፡ ስለዚህ፣ የጋብቻ ትስስር በጾታዊና ሥጋዊ ገጽታው ብቻ ሳይሆን፣ በፍቅር ራስን አሳልፎ በመስጠትም ይገለጣል፡፡ በሁለቱም አካላዊ፣ ልባዊና ሕይወታዊ አንድነት፣ በመጨረሻም በሁለቱም ወላጆች ‹‹ ሥጋ›› አካላዊም መንፈሳዊም ሥነ ባሕርይ በሚካፈለው ልጅ አማካይነት የሁለቱም ‹‹አንድ ሥጋ መሆን›› የዚህ አንድነት ውጤት ነው፡፡

ምንጭ፡ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 8-12 ላይ የተወሰደ።

አቅራቢ ባራና በርግኔ

 

 

 

 

15 July 2023, 16:42