ፈልግ

ሲስተር ኔቨስ ክሬስፖ ዓለም አቀፉን የበላይ አለቆች ውይይት ለመታደም በዝግጅት ላይ ፥ ሮም ሲስተር ኔቨስ ክሬስፖ ዓለም አቀፉን የበላይ አለቆች ውይይት ለመታደም በዝግጅት ላይ ፥ ሮም 

‘የስደትን ውስብስብ ችግሮች መፍታት’ በሚል በገዳማዊያን የሚመራ ውይይት ተካሄደ

ዓለም አቀፉ የበላይ አመራሮች ህብረት ስለስደት ለመወያየት በገዳማዊያን እህቶች መሪነት ሁለተኛውን ውይይት አካሂዷል። በውይይቱም የተሳተፉት ሲስተር ኒቭስ ክሬስፖ ስደተኞችን ለማብቃት የትምህርትን አስፈላጊነት አጉልተው አንስተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት የሳሌዥያ ማህበር አባል የሆኑት ሲስተር ኒቭስ ክሬስፖ ሰኞ ዕለት በተካሄደው የዓለም አቀፉ የበላይ አለቆች ማህበር ስብሰባን አስመልክተው ባደረጉት ቃለ ምልልስ በስብሰባው ላይ መሳተፋቸው በጣም ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ለቫቲካን ዜና ተናግረዋል።

ለስደተኞቹ ጠቃሚ የሆነ ሃይማኖታዊ ድጋፍ ማድረግ

“መሳተፍ ከብዙ ሰው ጋር የመገናኘትን እድል ይፈጥራል ፥ ይህ ደግሞ የበለጸገ ልምድ እንድናገኝ ይረዳል። ምክንያቱም ከተለያዩ ጉባኤዎች ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የተለያዩ ግን በአንድ ነጥብ ላይ እሱም በስደት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሰዎች ጋር አብረን ነበርን” ሲሉ ተናግረዋል። የስደተኞችን ችግር የበለጠ በማሰላሰል ፥ ገዳማዊያን ሲስተሮች እንደ ተሟጋች ሆነው እንደሚያገለግሉ እና በሚሠሩት ሥራ ስደተኞችን እንደሚደግፉ ሲስተር ክሬስፖ ተናግረዋል። ቤተክርስቲያኗ እና ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በአስቸጋሪ ጊዜያት ተስፋን እና የባለቤትነት ስሜትን በመስጠት የስደተኞችን ፍላጎት እና መብት ላይ በማተኮር ጉልህ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል ።
ሲስተር ክሬስፖ በኢትዮጵያ እየሠሩት ስላለው ሥራ ሲናገሩ ፥ “እንደ ገዳማዊያን እህቶች ትኩረታችን በትምህርት ላይ ነው ፥ ከግሎባል ሶሊዳሪቲ ፈንድ ጋር በጣም ጥሩ ፕሮጀክት አብረን እየሰራን እንገኛለን ፥ ካሉት አጠቃላይ አምስት የሰበካ ጉባኤዎች እያንዳንዱን ጉባኤ ይበልጥ ለማጠናከር ጥሩ ነገር ለማድረግ እየጣርን ነው ያለነው” ብለዋል።
ይህ ሲስተሯ የተናገሩለት ፕሮጄክት ፥ ስደተኞች እና የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ለሚገጥሟቸው አንዳንድ ችግሮች መፍትሄ የሚፈልግ የሙከራ ፕሮጀክት ነው።
ሲስተር ክሬስፖ አክለውም እንደ ሃይማኖት ጉባኤዎች “እነዚህ ልጃገረዶች ቴክኒካል ክህሎት እና የህይወት ክህሎት ባገኙበት ወቅት (እናበረታታቸዋለን) በሥራው ደስተኛ እንደሚሆኑ እና ክብር እንደሚሰማቸው ተረድተናል ምክንያቱም በብፊቱ ህይወታቸው ብዙ ሲሰቃዩ እና ሲታገሉ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

ለስደተኞች በርህራሄ የተሞላ ድጋፍ ማድረግ

በስደት ላይ ያተኮረው በገዳማዊያን መሪነት በተካሄደው ውይይት ላይ አንዱ ቁልፍ ነጥብ ተብሎ የተነሳው ትምህርት መሆኑን ሲስተር ክሬስፖ ገልፀዋል። “ትምህርት የአንድን ሰው አስተሳሰብ እና አመለካከት ስለሚቀይር ፥ በዓለም ዙሪያ ትምህርት አስፈላጊ ነገር ነው” ይላሉ።
ሲስተር ክሬስፖ ሁሉም ግለሰቦች በአስተዳደጋቸው ፣ በሃይማኖታቸው ፣ በባህላቸው እና በአኗኗራቸው ምክንያት የተለያየ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ላይ ያላቸውን አመለካከት እንዲቀይሩ አሳስበዋል። በተጨማሪም ስደተኞቹን የዓለማችንን እውነታ በጋራ ለመገንባት እንደተጠሩ ዜጎች እንዲያይዋቸው ይገባል” ሲሉ ሲስተር ክሬስፖ ተናግረዋል።

ፖለቲካዊ አካሄድን እንደ ቁልፍ ነጥብ

በመጨረሻም ሲስተር ክሬስፖ የስደት ጉዳዮች ወጥ የሆነ የፖለቲካ አካሄድ እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበዋል። መልእክቱም ሰዎች እንደ ዓለም አቀፍ ዜጎች በአንድነት እንዲያስቡ ማስተማር እና ማበረታታት መሆን አለበት ብለዋል።
በገዳማዊያን እህቶች የተመራው እና ትኩረቱን ስደተኞች ላይ ያደረገው ዓለም አቀፍ የበላይ አለቆች ህብረት ውይይት ፖሊሲ አውጪዎችን ፣ የፍልሰት ባለሙያዎችን ፣ የማህበራዊ ተመራማሪዎችን ፣ ማህበራዊ ሠራተኞችን ፣ ገዳማዊያንን ፣ የሚዲያ ባለሙያዎችን እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በአንድ ላይ አሰባስቧል።
የአንድ ቀኑ ኮንፈረንስ ዓለም አቀፍ ውይይቶችን ፣ የእውቀት ልውውጥን እና ለተወሳሰቡ የስደት እውነታዎች ወሳኝ መፍትሄዎችን ለማዘጋጀት ይረዳል ተብሏል።
 

05 July 2023, 14:50