ፈልግ

ከሪኤቲ ከተማ ባለው ተራራ ላይ የሚገኘው የመላእክት አለቃ የሆነው የቅዱስ ሚካኤል  ገዳም ከሪኤቲ ከተማ ባለው ተራራ ላይ የሚገኘው የመላእክት አለቃ የሆነው የቅዱስ ሚካኤል ገዳም 

በሪኤቲ ከተማ ‘ካፑቺኖ’ እየጠጣን ከሲስተር ሜሪ ራምቦ ጋር የነበረኝ ቆይታ

የቫቲካን መገናኛ ብዙሀን በፍሎሪዳ ውስጥ ለታሰሩ እስረኞች ካህን በመሆን ከባለቤታቸው ሱዛን ጋር እያገለገሉ የሚገኙትን የቀድሞ የዎል ስትሪት ፋይናንስ ጠበቃ የነበሩት ዴሌ ሬሲኔላ ታሪክ አቅርቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

(ሪኤቲ 47,700 የሕዝብ ብዛት ያላት በላዚዮ ግዛት በመካከለኛው ኢጣሊያን የምትገኝ ከተማ ናት)
እ.አ.አ. በ1988 በመጥፎ ህመም ምክንያት ለሞት ተቃርቤ ከዳንኩበት ልምድ በኋላ እኔ እና ሱዛን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለን የፍራንሲስካውያን መንፈሳዊ አማካሪዬ ወደ ነበሩት ካህኖቻችን አባ ፎሊ እና አባ ሙሬይ ጋር ለምክር አገልግሎት በተደጋጋሚ እንሄድ ነበር። የእኛ ጥያቄ ሁሌም አንድ ነው፡ “ኢየሱስ የተናገረላቸው እነዚህን መከራ የሚቀበሉ ሰዎች የት እናገኛቸዋለን? ምንስ እናድርግላቸው?” የሚል ነበር።
መልሱን ለማግኘት ስንጥር ፥ መንፈሳዊ አማካሪዎቻችን ከአንድ ሺህ ዓመት ገደማ በፊት በኖሩት ሁለት ሰዎች ላይ በሚያተኩር ጥናታዊ ንግደት ታሪክ ላይ ተመርኩዘን መልሱን ለማግኘት እንደምንችል ተስማምተዋል። ይህ ለሁለታችንም ታላቅ ተሞክሮ ይሆነናል ፥ ግን አንድ ላይ ሳይሆን ለየብቻችን። እኛ ባለትዳሮች ከአርባ ስምንት መነኮሳት እና ቀሳውስት ጋር ለጥናታዊ ንግደት ዕድሜያቸው ከአንድ እስከ አስራ አራት ዓመት የሆናቸውን አምስት ልጆችን ይዘው መሄድ አይችሉም። ስለዚህ እኔ ልጆቹን ስንከባከብ ሱዛን መጀመሪያ ትሄዳለች።
ሱዛን በነሐሴ 1988 ወደ ጣሊያን ከተማ ወደ ሆኑት አሲሲ እና ሮም ሄዳ አሥራ ስድስት ቀናትን በጸሎት እና የቅዱስ ፍራንቺስኮስን እና የአሲሲዋን ቅድስት ክላሬ ሕይወትን በማጥናት አሳልፋለች። እነዚህ ሁለቱ ቅዱሳን በአከባቢያቸው ፣ በነበሩበት ሁኔታ እና በጊዜያቸው ፥ በአስራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ እውነተኛውን ወንጌል ለመኖር የፈለጉ ሁለት ምእመናን ነበሩ። ፍራንቺስኮስ ካህን ሆኖ መሾም አልፈለገም። ክላራ ደግሞ ከሁሉም ነገር በተዘጋ ገዳም ውስጥ መገለል አልፈለገችም። በልባቸውም ሆነ በመንፈስ ሁለቱም ‘ወንጌል የሚናገረው እውነት ካልሆነ በስተቀር’ ምንም ትርጉም የሌለው ሕይወት ለመኖር የሚፈልጉ ምእመናን ነበሩ። ሆኖም፥ በታዛዥነት በጊዜው ወደነበረችው ቤተ ክርስቲያን ለመግባት ሃይማኖታዊ ጥሪዎችን መቀበል ጀመሩ።
የኔ ተራ ደርሶ ሰኔ 1989 በአሲሲ እና በሮም የ30 ቀን የጥናታዊ ንግደት ላይ ስገኝ ፥ ሱዛን እና ልጆቻችን ዲትሮይት በሚገኘው የአባቴ ቤት ከቤተሰባቸው ጋር ይቆያሉ። የእኔ መንፈሳዊ ንግደት ወይም ጉዞ በሮም እና በአሲሲ ይጀምራል። ከአሲሲ በኋላ በመሬት መልክአ ምድር አቀማመጥ የኢጣሊያ ባሕረ ገብ መሬት ማዕከል ውስጥ ወደምትገኘው እና የከተማዋ የመሬት የኢጣሊያ ‘የሆድ ጠርዝ’ ተብላ ወደ ምትጠራው ወደ ሪኤቲ ከተማ እንሄዳለን። በይበልጥ ጉልህ በሆነ መልኩ ፥ በቅዱስ ፍራንቺስኮስ እና ቅድስት ክላሬ ሕይወት ውስጥ የበርካታ አስፈላጊ ክስተቶች የተከሰቱበት ቦታ ነው። ለሶስት ሳምንታት የሚጠጋ ጥናት፣ጸሎት እንዲሁም የቅዱሳን እና ታሪካዊ ቦታዎችን በሮም እና አሲሲ ከጎበኘን በኋላ ፥ ሪኤቲ ቡድናችን ቆም ብለን ለመጸለይ እና መንፈሳዊ ንግደቱ ህይወታችንን እንዴት እየተፈታተነው እንደሆነ እናሰላስልበታለን።
ከሪኤቲ በሰሜን በኩል በሚገኘው ተራራ ጫፍ ላይ በሚገኘው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ገዳም የሶስት ቀናት የጸጥታ እና የማሰላሰል ጊዜያትን ከመጀመራችን በፊት በነበረው ምሽት ፥ ከቡድናችን አባላት ከሆኑት ፍራንቺስካውያን መነኮሳት ከአንዷ ጋር በአንድ የውጪ ካፌ ውስጥ ካፑቺኖ እየጠጣሁ ነው። እሷ ዝምተኛ እና ጨዋ ሴት ነች። በእሷ ቅድስና እና በሁሉም ሁኔታ ከእሷ ጋር በሚመጣው መገኘት ተደንቄያለሁ። ግልፅ በነበረው በውይይታችን ወቅት የቅዱስ አጎስጢኖስ ንግግሮችን የሆኑትን “አስፈላጊ የሚባሉ ነገሮችን የሌሏቸው ሰዎች እስካሉ ድረስ ፥ ከሚያስፈልገው በላይ ያለው ሰው የሌላውን ዕቃ እንደያዘ ነው” የሚለውን አባባሉን ጥርት አድርጋ ስትነግረኝ እኔ በምላሹ ጸጥታ ውጦኝ ነበር። ዛሬ ማታ በመጨረሻ በደንብ ለመተዋወቅ የምንችልበት እድል ነው።
ውይይታችን ወደ ቬትናም ጦርነት ዘመን ዞሯል። በጦርነት ቀጣና ውስጥ ወላጅ አልባ ሕፃናትን የምትንከባከብ ሚስዮናዊ ሆና ያጋጠማትን የቬትናም ልምዷን ስትገልጽ በጣም በመገረም እሰማት ነበር። በጦርነቱ አሜሪካ ቬትናምን ለቃ ለመውጣት ስትል በነበሩ የመጨረሻ ቀናት ሞርታር እና መትረየስ እየተተኮሰባቸው ህጻናት ልጆችን ከጦርነት ቀጠናው በአውሮፕላኖች እና በሄሊኮፕተሮች ለማስወጣት ሲሉ የነበረውን ድባብ እና ያሳለፈችውን ተሞክሮ ስትናገር በውስጤ ብዙ ነገሮች ሲፈርሱ ይሰማኝ ነበር።
የተዳከመ ጉሮሮዬን እያፀዳዳው “እሺ… ከዛስ” በማለት በመጨረሻ የታሪኳን ፍጻሜ የሚገልጸውን ዝምታ ሰበርኩ
“በብሩክሊን ሆስፒታል ውስጥ ከኤድስ ህመምተኞች ጋር እሰራለሁ” ድምፅዋ እና የምትመልስበት ፍጥነት አስገራሚ ነበር።
በደመ ነፍስ ምላሽ የምሰጠው በእውነት የሚያስፈራ ፥ ከሥነ ምግባራዊ ራስን የማመጻደቅ ስሜቴ ላይ የተመሠረተ እና በፍርሃት የተሞላ ጥያቄ ነው። ይህች ትንሿ እህት ሜሪ ራምቦ ዓይኖቿን ቀና አድርጋ ተመለከተችኝ እናም በለሆሳስ “ከመካከላችን ትንሹ ስህተታችን ሊያስከትሉ የሚችሉትን አስከፊ መዘዞች መጋፈጥ የሚፈልግ ማን ነው?” ትለኛለች።
ትንሹ ስህተታቸው የሚያስከትለውን መጥፎ ውጤት መጋፈጥ የሚፈልግ ማነው?
እንዴት ያለ ጥያቄ ነው! በጥያቄው ፊት ለትዕቢት ወይም ለራስ ጽድቅ ቦታ የለም። የአስተሳሰቧን ጥልቅ ትርጉም አውቃለሁ። ነገር ግን ለእግዚአብሔር ፀጋ ፥ ወደ ራሴ ተመለስኩኝ። ያ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰው የአሲሲው ቅዱስ ፍራንቺስኮ ስህተት ለሰሩ ሰዎች ስላለው ስጋዊ አስተያየት ሲጠየቅ የተናገረው ነው። በእግዚአብሔር ቸርነት ብቻ ነው ፥ እሱ እንደሚያመለክተው እኛ እራሳችን ከትንሽ ስህተታችን ሊመጣ የሚችለውን የከፋ መዘዝ እንዳንጋፈጥ ሌላው ቀርቶ የከፋው ጉዳያችን ነው።
ምን ለማለት እንደፈለገች አውቃለሁ ፥ ምን እንደፈለገች እንደማውቅም ታውቃለች። በቀሪው ምሽት ዓይኖቿን ማየት አልቻልኩም ፥ ለረጅም ደቂቃዎች ወደ ትንሹ የጣሊያን ቡና ስኒ አፈጠጥኩ።
እ.አ.አ. በ1990 መጀመሪያ ላይ እኔና ሱዛን ሁለታችንም በኤድስ ለተያዙ ሰዎች አገልግሎት የሚሰጠውና በታላሃሴ ከተማ ከሚገኘው ለትርፍ ያልተቋቋመ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት የበጎ ፈቃደኝነት ስልጠና አጠናቅቀናል። ሱዛን ለተንከባካቢዎች ድጋፍ ለመስጠት የሰለጠነች ናት። በኤች አይ ቪኤድስ ለሚታመሙትና ለሚሞቱት ጓደኛ ለመሆን እስከ መስዋዕትነት ድረስ የሚያደርስ ስልጠና ሰልጥኛለሁ።
ስልጠናውን እንዳጠናቀኩ ከግማሽ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው የመጀመሪያ የስልክ ጥሪዬን የተቀበልኩት ፥ ከዛም በኋላ በታላሃሴ ክልል በሚገኘው የኤች አይ ቪ ኤድስ የበሽትኞች አገልግሎት አቅራቢው በረጅሙ በተዘረጋው የቢሮው ግድግዳ መተላለፊያ አልፌ ቢሮው ውስጥ ተገኘሁኝ። ምንጣፉ፣ ወንበሮቹ እና ጠረጴዛዎቹ ሁሉም የ1970ዎቹ ስሪቶች ናቸው።
“በፍጥነት እዚህ ስለደረስክ እናመሰግናለን” አለችኝ ዳይሬክተሯ ፥ በሃያዎቹ መጨረሻ ላይ የምትገኝ ወጣት ነች ፥ በሁሉም የማዕከሉ አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ የሰለጠነ ችሎታ ያላት ሴት ነች። “ይህ አዲስ ደንበኛ የአንተን መንፈሳዊ ዕርዳታ እንደሚፈልግ ይሰማኛል” አለችኝ ወደ አንድ ህመምተኛ እያሳየችኝ።
“በምን መንገድ?” አልኳት... ድምፄ እየሞተ ላለ ሰው ምንም አይነት ምክር ለመስጠት ብቁ እንዳልሆንኩ መሆኑን ያሳያል።
“ትናንት ነበር ወደዚህ የመጣው ፥ ትንሽ ተረብሾ ነበር ፥ ከዚያም ‘እኔ አርበኛ ነኝ ፥ የኤች አይ ቪ ኤድስ ታማሚ ነኝ ፥ ሽጉጥም አለኝ ፥ ስለዚህ ጓደኛ ካልሰጠሽኝ ራሴን አጠፋለሁ’ አለኝ ፥ ወዲያው እሱን ለመንከባከብ ከሁሉ የተሻለው ሰው አንተ እንደሆንክ በሃሳቤ መጣብኝ”
“በእውነት?” አልኳት ፥ የእኔ አጠር ያለች የማስመሰል ጥያቄዬ በፍርሃት መጨናነቄን እንደሚሸፍነው ተስፋ እያደረኩ ነበር።
“በፍፁም” እሷ በእኔ ላይ በጣም እርግጠኛ የሆነች ትመስላለች። “ከምንም ነገር በላይ መንፈሳዊነት ያስፈልገዋል። መድሃኒት እና ማህበራዊ አገልግሎት እንዳለው ማረጋገጥ እንችላለን ፥ እሱ ግን መንፈሳዊ አገልግሎት ያስፈልገዋል”
“ምክንያቱም…” ብዬ ቅደም ተከተሉን እንድትጨርስ ጋበዝኳት “ምክንያቱም መንፈሱ በብቸኝነት እየሞተ ነው። በዓለም ላይ ከእናቱ በስተቀር አንድ ጓደኛ ያለው አይመስለኝም”
“እና የእሱ ጓደኛ እንድሆን ትፈልገያለሽ?” አልኳት
“ለዚህ ነው እዚህ የፈለኩህ” እርግጠኛ እንደሆነች ያስታውቃል።
“ነገር ግን እሱ ትንሽ ሊያስቸግርህ ይችላል ፥ ይሄን ለመቆጣጠር በጣም ትክክለኛ ሰው አንተ ነህ ብዬ አስባለሁ”
የእሱ አፓርታማ በዝቅተኛ ደረጃ ከተሰሩት የመኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት ውስጥ የመጀመሪያ ፎቅ ላይ ነው።
“ማን ልበል?” አለ የመኖሪያ ቤቱን በር እየከፈተ
“ከማዕከሉ ነው የመጣሁት ፥ ጓደኛ ትፈልጋለህ አሉ” አልኩት።
“ስለዚህ አሁኑኑ ግባ ትችላለህ!” አለኝ
ያልተቆለፈው በሩ የተመሰቃቀሉ እቃዎቹን ለማሳየት ተከፍቷል ፥ በስተግራ ያለው የኩሽና ክፍል በቆሻሻ ምግቦች የተከመረ ሲሆን ከረጅም ጊዜ በፊት አገልግሎቱን ካቆመ የፕላስቲክ ጣሳ ላይ በተዝረከረከ የቆሻሻ መጣያ የተከመረ ነው። መታጠቢያ ቤቱ በቀጥታ ፊት ለፊት ይታያል። በስተቀኝ በኩል በተለምዶ ሶፋዎች የሚቀመጡበት ቦታ ላይ የሆስፒታል አይነት አልጋ ነው ተዘርግቷል። አዲሱ ጓደኛዬ ወደ ቴሌቪዥኑ አፍጥጦ ተቀምጧል።
“ታዲያ ጓደኛዬ ለመሆን ምን ያህል እየከፈሉህ ነው?” አለኝ
“እኔ በጎ ፈቃደኛ ነኝ ፥ ክፍያ የለውም”
"እሺ... ልዩ ሰው አይደለህም?"
"አይ ፥ በጎ ፈቃደኛ ብቻ"
“ደህና ፥ እንዴት ማድረግ እንዳለብህ ምን ታውቃለህ አቶ በጎ ፍቃደኛ?” አለኝ
"ምን ትፈልጋለህ?"
በሆስፒታሉ አልጋ ላይ ያለው እንግዳ ወጣት የቴለቪዥኑን የርቀት መቆጣጠሪያውን ወደ ጭኑ ጣል አድርጎ ወደ ሰማይ ተመለከተ።
“ምን እንደምፈልግ አላውቅም” አለኝ ወደ እኔ ሳያይ ፥ "የምፈልገውን አላውቅም"
"ስለዚህ አንተን ለተወሰነ ጊዜ ከዚህ ቦታ በማውጣት እንጀምር ፥ መራመድ ትችላለህ?” አልኩት
“አዎ ፥ እስካሁን አልሞትኩም"
"ይህ ጥሩ ምልክት ነው ፥ ወደ ኤላ ሀይቅ እንሂድና ዳክዬዎችን እንመግብ ፥ ከመሀል ከተማ ታላሃሴ በስተሰሜን በእግረኛ መንገድ የተከበበ የውሃ ምንጭ ያለው ውብ ሀይቅ እንዳለ ታውቃለህ መቼም ፥ እዚያ ብዙ ዳክዬዎች አሉ” አልኩት።
"ለምንድን ነው ዳክዬዎችን መመገብ የምፈልገው?"
“እኔን ዬትኛውም አይነት የሚያስጨንቀኝ ነገር ሲኖር ዳክዬዎችን ስመግብ ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ እንደሚያደርግ ብዙ ጊዜ ተገንዝቤያለሁ” አልኩት።
“ያ ደደብ ቢሮ ደውዬ እንዳባረርኩህ ብነግራቸው ሌላ ሰው ይሰጡኛል?” አለኝ
“አይሆንም ፥ እኔ ላንተ የተመደብኩ ብቸኛ ሰው ነኝ”
"አንተ እና እነዛ ዳክዬዎች!" አለኝ በተቃውሞ መልክ ወደ መኪናው እና ወደ ኤላ ሀይቅ እየወሰድኩት ፥ ብዙ የተበላሹ ዳቦ የያዙ ከረጢቶችን ከገንዳው ውስጥ ለዳኪዬዎቹ ብዬ ይዤ ነበር።
"ምንድ ነህ? ዳቦ ጋጋሪ?" አለኝ ፥ ተጠራጣሪነቱ ያልተጠበቀ ነው።
"አይ... ጊዜው ያለፈበት ዳቦ ከሾርባ ኩሽና ወስጄ ነው ፥ ሰዎች እንዳይጠቀሙት ድግሞ በጣም የቆየ ነው” አልኩት
“ታዲያ ጊዜው ያለፈበት ዳቦ ለዳክዬዎች ትሰጣለህ? ምን አይነት ሰው ነህ?” አለኝ
"ከአንተ ጋር እዚህ የተቀመጠው ሰው ነኝ" አልኩት
ወደ ሲኒማ ቤቶች እንሄዳለን ፣ የቤዝቦል ጨዋታዎችን እንከታተላለን እና ዳክዬዎችን እንመግባለን። የመራመድ ችሎታው ሲዳከም ተሽከርካሪ ወንበር እንይዛለን።
በአፓርታማው ውስጥ ማንኛውንም አይነት ጽዳት ከተከናወነ በእናቱ ነው የተከናወነው ማለት ነው። ባለቤቷ ፥ የልጇ የእንጀራ አባት የሚገርም አሳዳጊ ነበር። የባህር ኃይል አርበኛ ነበር ፥ ልጇን በመታጠቢያ ቤት ሲረዳው የነበረው እሱ ነው። ይህ የእንጀራ አባት ለእነሱ ብዙ ነገራቸው ነው ፥ በርህራሄም የተሞላ ሰው ነው። የኢየሱስ ምድራዊ የእንጀራ አባት ከሆነው ቅዱስ ዮሴፍ ጋር ዝምድና ይኖራቸው ይሆን ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል ፥ እንደዚህ በማሰቤ ምንም ማድረግ አልችልም።
እናትን በተመለከተ ፥ ሴቲቱን ለኢየሱስ ፍጹም ዕንቁ አድርጌ እቆጥራለሁ። እሷ ጠንካራ ክርስቲያን ነች ፥ የደቡባዊ ባፕቲስት ትውልዶች ሃይማኖታዊ መሰረት ያሏት ናት። ልጇ ለውትድርና ሄዶ ሄሮይን ሱስ ሆኖበት እና በኤድስ ተይዞ ተመለሰ። ልጇ ከባህር ማዶ ከተመለሰ በኋላ ለአምላክም ሆነ ለእምነት ምንም ፍላጎት አልነበረውም። እሷም እግዚአብሔር የፈቀደውን በጭራሽ አታወግዝም ፥ በጭራሽ አታጉረመርምም ፥ መጽሐፍ ቅዱሷን እና አዳኝዋን አጥብቃ ይዛለች ፥ መጸለይን አዘውትራ ቀጥላለች።
በሽታው እየገፋ ሲሄድ ጓደኛዬ የአልጋ ቁራኛ እየሆነ ነው። የእኔ እርዳታ አሁን መንፈሳዊውን ያህል ተግባራዊም ነው። ዳይፐር መቀየር እና መድሃኒቶችን መከታተል ስላለበት ወንድ ነርስ ሁሊም በስራ ላይ ነው። ወቅቱ ክረምት ከሰዓት በኋላ ነው። በአፓርታማው ውስጥ ካለው የኩሽና ዕቃ ማጠቢያ ገንዳ አጠገብ ቆሜ እቃ እያጠብኩ ነው። የነተበው የእጅ መጥረጊያ እና የእጅ ጓንቶች ጠረን በጣም ይሰነፍጣል። ከአሁን በኋላ እነዚህን ነገሮች አናስተውላቸውም። ብዙ መናገር አይችልም ፥ በጣም እየተዳከመ ነው። ስለዚህ ሳሎን ውስጥ ካለው የሆስፒታል አልጋ ላይ ሆኖ ሃይሉን ሰብስቦ ወደ እኔ ጮሆ ሲጠራ በጣም ደነገጥኩ።
"ቤተ ክርስቲያን መሄድ እፈልጋለሁ" አለኝ
"እኔ አላምንም ፥ ይህ ከእኔ የሆነ ነገር ለማግኘት የተደረገ ዘዴ ነውን?
"ፈንዳ ከፈለክ" አለ ፥ ይህ የሁል ጊዜ ስድቡ ፥ "የምሬን ነው ፥ ቤተ ክርስቲያን መሄድ እፈልጋለሁ” አለኝ ደግሞ
"በጣም ጥሩ ፥ ወደ እናትህ እደውላለሁ ፥ አንተን ወደ ቤተክርስቲያን ለመውሰድ በጣም ትደሰታለች” አልኩት።
"እሷ የምትሄድበትን ቤተክርስቲያን አልፈልግም" እንደገና እንደመሳደብ አለ ፥ "ወደ ቤተ ክርስቲያንህ መሄድ እፈልጋለሁ"
“ቤተ ክርስቲያኔ? እኔ ምን እምነት እንደሆንኩ እንኳ አታውቅም። ለምን ወደ ቤተ ክርስቲያኔ መሄድ ትፈልጋለህ?
"ምክንያቱም ለምን ወደዚህ እንደምትመጣ መረዳት እፈልጋለሁ" አለኝ
“ደህና…” እጆቼን ከመታጠቢያ ገንዳው ላይ ከማውጣቴ በፊት ውሃውን ለመዝጋት ብዬ ቆም አልኩ። "ለገንዘብ እንዳልሆነ እናውቃለን"
ያለ እናቱ ፈቃድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ልወስደው አልፈልግም። ለአምላክ ያለኝን አዲስ ቅንዓት በማስመሰል በእሷ ላይ እንደ መሣሪያ አድርጎኝ እንዲጠቀምብኝ አልፈቅድም። ወደ ቤተክርስቲያን የመሄዱን ዜና በስልክ ስነግራት እያለቀሰች ስታወራኝ ነበር።
“እባክህን ወደ ፈለገበት ቤተክርስቲያን ይሂድ ፥ ይሄ እንዲሆን ለዓመታት ስጸልይ ነበር። ወደ ቤተ ክርስቲያንህ ውሰደው። ጊዜው ሳይረፍድ ወደ ጌታ ውሰዱት” አለችኝ።
ጓደኛዬን ወደ ቤተ ክርስቲያን መውሰድ ቀላል ስራ አይሆንም ምክንያቱም እሱ የዳይፐር እና ከዊልቸር ጋር የታሰረ የግሉኮስ ተጠቃሚ ሆኗል። ይህ ከማለቁ በፊት ወደ አንድ በብዙ ምዕመን ወደታጨቀ የእሁድ አገልግሎት የሚሰጥበት ቤተክርስቲያን ልወስደው አልችልም ፥ ስለዚህ የነርሷን እርዳታ እፈልጋለሁ።
ለሳምንት ቀናት ጧት ጧት አጠገባችን ወደ ነበረው ጸሎት ቤት ስንመላለስ ነበር ፥ አገልግሎቱ እስኪጀመር ቆመው መዝሙር ሲዘምሩ የነበሩ ወደ ሃምሳ የሚጠጉ ታዳሚዎች አሉ። ካህኑ ወዲያውኑ ሁኔታውን ገምግሞ አንድ ሰው ሊገምተው ከሚችለው በላይ በሆነ ጸጋ ተሞልቶ ምላሽ ይሰጣል።
ዛሬ ጠዋት ልዩ እንግዳ አለን ። ወደ ኋላ እንዲጠጉ እና በመንገዱ ላይ ያሉትን ሁለት ተጣጣፊ መቀመጫዎች እንዲያነሱት ከፊት ረድፍ ያሉትን ሰዎች በትህትና ይጠይቃል። "እባክህ እዚህ ፊት ለፊት ና" አለው ጓደኛዬን ፥ ከዚያም ፊት ለፊት ተሰልፈን ስንቀመጥ ካህኑ ወደ ጓደኛዬ መጥቶ ወንበሩ ላይ ጎንበስ ብሎ ሞቅ አድርጎ አቀፈው።
"እንኳን ደህና መጣህ" ሃምሳዎቹ ሁሉ እንዲሰሙ ጮክ ብሎ ይናገራል። "ኢየሱስ ወደዚህ እንድትመጣ ሲጠብቅህ ነበር"
ከቁርባን በፊት ፥ ለሰላምታ እጅ የመጨባበጫ ጊዜ ላይ በቤተመቅደስ ውስጥ የነበረ እያንዳንዱ ሰው በፈገግታ ተሞልቶ ወደ ጓደኛዬ መጥቶ አቅፎ ሰላምታ ሰጥቶታል።
ከአገልግሎቱ በኋላ እኔና ነርሷ ጓደኛዬን ወደ መኪና ማቆሚያ ቦታ እየወሰድነው ሳለ ሶስት ትልልቅ ሴቶች ወደ እሱ ሲመጡ አየን።
በቆንጆ የቀለም ህትመቶች የታተሙ መጽሄቶች እየሰጡት ፥ “እነዚህ የወንጌል ታሪኮችን የሚገልጹ ሥዕሎች ናቸው። በምትጸልይበት ጊዜ እነርሱን ማየት ትችላለህ” አሉት።
"አመሰግናለሁ" አልኩኝ እሱን ወክዬ አንገቴን እየነቀነኩ።
እነዚያ ሥዕሎች የጓደኛዬ አልጋ ላይ ከዚያ ቀን ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ተንጠልጥለዋል። እነዚህን ወንጌላት ብቻ ነው ያነበበው። ከአሁን በኋላ በህትመት ላይ ማተኮር ለማይችል ዓይኑ የሚመች እና የሚነበብ ነበር። ያለ ከባድ ችግር መናገር በማይችልበት ጊዜ ዓይኖቹ እነዚያ ምስሎች ላይ ለብዙ ሰዓታት ያፈጣሉ። ብዙውን ጊዜ በሥዕሎቹ ላይ ኢየሱስን በመጠቆም ፈገግ ይላል።
ከመሞቱ በፊት በእርግጥም ወደ ጌታ መጥቷል ፥ የመጨረሻውን እስትንፋሱን ሲተነፍስ ጭንቅላቱ እና ትከሻዎቹ በእጆቼ ውስጥ ነበሩ ፥ እናቱ እና የእንጀራ አባቱ ከአልጋው አጠገብ ሆነው እጆቻቸውን እሱ ላይ ጭነው ነበር። ነርሷ በአልጋው ግርጌ በኩል ቆማለች ፥ ሁላችንም ‘አባታችንን’ ጮክ ብለን ስንጸልይ ነበር።
ነፍሱ ስጋውን ትታ ስትሄድ ፥ ጓደኛዬ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያን የመጣበትን ቀን በዙሪያው የነበሩት ሰዎች በፍቅር እና በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዴት ሲሆኑ እንደነበር ፥ የእግዚአብሔርን ፍቅር እና የማዳን ሃይሉን እንዲገነዘብ የሚያግዙትን የቅዱስ ወንጌልን የሚያንፀባሪቁ ሥዕሎችን ይዘው የተቀበሉትን ሴቶች እያሰብኩ ሳሰላስል ነበር። እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ምን ያህል ሩቅ መንገድ ይሄዳል! በጥልቅ የምስጋና ጊዜ ውስጥ ያለሁ ይመስለኛል። ጌታ ሆይ ለማዳን ሥራህ እኔን ተጠቀምብኝ።
 

28 July 2023, 22:10