ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ በሮንዲኔ ከተማ በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ የሰላም ፌስቲቫል ላይ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ በሮንዲኔ ከተማ በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ የሰላም ፌስቲቫል ላይ 

ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ “ለዩክሬን ሰላም ብቸኛው መንገድ ውይይት ነው” አሉ

“በዩክሬን እና በሩስያ መካከል በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጦርነት አብቅቶ ሰላም እና እርቅ እንዲወርድ ቅድስት መንበር የምታደርገውን ጥረት ለማጠናከር ወደ ዩክሬን የተላኩት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዩ ዙፒ፥ በሁለቱ አገራት መካከል ሰላምን ለማውረድ ብቸኛው መንገድ ውይይት እንደሆነ ተናግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ሚጌል አንጀል ሞራቲኖስ ብጹዕነታቸው የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን የሰላም ጥረት ለማሳካት በዩክሬን ለሚያከናውኑት ተልዕኮ ፍሬያማ እንዲሆን መልካሙን ተመኝተውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዩክሬንን ከግንቦት 28 – 29/2015 ዓ. ም. ድረስ ጎብኝተው የተመለሱት የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የቦሎኛ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ “ሮንዲኔ” በተባለች የጣሊያን ከተማ በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ የሰላም ፌስቲቫል ላይ ተገኝተው ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። “ሮንዲኔ ቺታ ዴላ ፓቼ” በመባል የምትታወቅ የሰሜን ጣሊያን ከተማ በዓለማችን ውስጥ የሚካሄዱ የትጥቅ ትግሎችን ለመቀነስ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ ድርጅት የሚገኝባት ከተማ እንደሆነች ይታወቃል።

ስለ ሰላም በማስመልከት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ፌስቲቫሉ የታደሙ ወጣቶች በመጥቀስ በሰጡት ምላሽ፥ "ወጣቶች የዛሬ ብቻ ሳይሆን የወደፊት ተስፋዎች፣ ፌስቲቫሉን ያዘጋጀችው የሮንዲኔ ከተማ ጦርነትን በማውገዝ ብዙ ታሪክ ያላት፣ በርካታ ስብሰባዎች እና ውይይቶች የሚካሄዱባት ከተማ ናት” ብለው፥ “ግጭት የሚታየው በሚፈነዳበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን መግባባት እና መደማመጥ በማይኖርበት፣ መራራቅ እና ግድ የለሽነት ሲኖር ነው” በማለት አስረድተው፥ “በዚህች ከተማ ውስጥ በተጨባጭ የሚታይ ሰላም ወደ ሁሉም ሥፍራ እንደሚደርስ ተስፋ አለኝ” ብለዋል።

አንድነት የመጪው ጊዜ ተስፋችን ነው

በሮንዲኔ ከተማ ውስጥ አብረው በኅብረት ስለሚኖሩ የሩሲያ እና የዩክሬን ልጆች ተጠይቀው ምላሽ የሰጡት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ “ይህ የሚያሳየው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ‘ሁላችንም ወንድማማቾች ነን’” ብለው በጻፉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው “መጭው ጊዜ አብሮ መሆንን የምንማርበት ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል። አንዳንድ ጊዜ የማይቻል እስኪመስል ድረስ አድካሚ ቢሆንም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “በጥበብ ከተጓዝን ሁሉን ማዳን ይቻላል" ማለታቸውን አስታውሰው፣ “እርስ በርስ መተሳሰብ መሠረታዊ እንደሆነ እና ችግሮችን መወጣት የሚቻለው በኅብረት ሲሆኑ ብቻ ነው” በማለት ተናግረዋል።

ጦርነት ወንድምን እንዲክዱ ያደርጋል

"ሁላችንም እርስ በርስ መነጋገር እና መወያየትን መማር አለብን" ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፥ "ጦርነት ሁል ጊዜ ሕዝቦችን እንደሚከፋፍል፣ እንደሚለያይ፣ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሣሪያ በመሆን ለብዝበዛ እንደሚዳርግ፣ ወንድምን እና እህትን እንዲክዱ ያደርጋል” ብለው፥ ከዚህ ይልቅ በሁሉም ሥፍራ ወደ አንድነት ጎዳና ለመመለስ በጋራ መሥራት እና አብሮ መኖርን መማር እንደሚያስፈልግ ተናግረው፥ ራስን ማወቅ የሚቻለው ወንድም እና እህት ከሆኑት ሕዝቦች ጋር በአንድነት መኖር ሲችሉ ነው” በማለት አስረድተዋል።  

ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተልዕኮ መልካምን ተመኝተዋል

የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የቦሎኛ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ በፌስቲቫሉ ላይ ንግግር ካደረጉት እንግዶች መካከል አንዱ ከሆኑት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ ከአቶ ሚጌል አንጀል ሞራቲኖስ ጋር አጭር ውይይት ያደረጉት ሲሆን፥ የተባበሩት መንግሥታቱ ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአውሮፓ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ለሚያበረክቱት አስተዋፅዖ እና ለብጹዕነታቸው የሰላም ተልዕኮ ፍሬያማነት መልካሙን ሁሉ ተመኝተውላቸዋል።

10 June 2023, 11:11