ፈልግ

 ኡጋንዳ ፥ ምፖንድዌ ከተማ ውስጥ በሉቢርሃ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በደረሰ ጥቃት ምክንያት ት/ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ኡጋንዳ ፥ ምፖንድዌ ከተማ ውስጥ በሉቢርሃ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በደረሰ ጥቃት ምክንያት ት/ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች  (AFP or licensors)

የኡጋንዳው ካህን በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን እልቂት ለማስቆም የሠላም ንግግር እንዲደረግ ተማጸኑ

በኡጋንዳ የምእራብ ካሴስ ሀገረ ስብከት ካህን የሆኑት አባ ሰንዴይ አውጉስቲን ማሴሬካ ለሃገረስብከታቸው በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ፥ ምፖንድዌ በሚገኘው ትምህርት ቤታቸው ዉስጥ ከ40 በላይ ተማሪዎች የተገደሉበትን አሳዛኝ ድርጊት አውግዘው ፥ በዚህ የዓለም ማህበረሰብ ትኩረት ባልሰጠው ጦርነት ንፁሀን ዜጎች መሞታቸውን ቀጥለዋል ብለዋል።

 አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ - አዲስ አበባ

በምዕራብ ዩጋንዳ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አማፂያን ባደረሱት ጥቃት አብዛኞቹ ተማሪዎች የሆኑበት 42 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል።
አማፂያኑ ትምህርት ቤቱን ካቃጠሉ በኋላ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ተማሪዎች ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን ከስምንት ያላነሱ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎችም እስከ አሁን ሆስፒታል ውስጥ ይገኛሉ።
የኡጋንዳ ፖሊስ ባለስልጣናት ለኢስላሚክ ስቴት ታማኝ በመሆን በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የትጥቅ ትግል እያደረገ የሚገኘውን ‘የዲሞክራሲ ሃይሎች ህብረት’ (Allied Democratic Forces) ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።
የሃገሪቷ የመከላከያ ሰራዊት እና የፖሊስ ሃይሎች ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ድንበር አቋርጠው ወደ ቫይሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ አቅጣጫ የሸሹትን አጥቂዎችን በማሳደድ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አባ ሰንበት አውጉስቲን ማሴሬካ ጥቃቱ ከተፈፀመበት በምዕራብ ዩጋንዳ የሚገኘው የካሴሴ ሀገረ ስብከት የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሲሆኑ ፥ ስለ ጥቃቱ ለቫቲካን ረዲዮ ተናግረው ከጀርባው ያለውንም ሤራ አብራርተዋል።
አባ አውጉስቲን እንዳሉት የሉቢሪራ ትምህርት ቤት ከሌሊቱ 11 ሰዓት አካባቢ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ድንበር አቋርጠው በመጡ አማፂያን ከፍተኛ ጥቃት ደርሶባቸዋል።
“ትምህርት ቤቱ ወደ 62 የሚጠጉ ሴት እና ወንድ ተማሪ ልጆች የነበሩበት ሲሆን ፥ ከእነዚህም ውስጥ አማፂዎቹ 41ን ገድለዋል ፥ አንዱ ተማሪ ደግሞ ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ የሞተ ሲሆን ይህም የሟቾቹን ቁጥር ወደ 42 አድርሶታል” ብለዋል ካህኑ።
ካህኑ የአማፂያኑ ጥቃት አሰቃቂ እና እጅግ ከባድ ሲሆን ፥ ቦንቦችን በማፈንዳት ፣ ህንፃውን እና ነዋሪዎቹን በማቃጠል ፣ ህጻናትን እና ሰራተኞችን በመሳሪያ እና በቢላ ማጥቃትን ያጠቃልላል።
የባለሥልጣኖቹ መግለጫ በኮንጎ ውስጥ የሚገኙትን የዲሞክራቲክ ሃይሎች ህብረት ታጣቂዎችን የሚያመላክት መሆኑን እና ከተረፉት መካከል አንዷ ነፍሰ ጡር ሴት አማፂያኑ ‘ሙስሊሞች ልጅ የተሸከመ ሰው እንደማይገድሉ’ ተናግረው በመትረፏ ምክንያት ቡድኑ ታጣቂ እስላማዊ ቡድን መሆኑን ካህኑ አረጋግጠዋል። እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት የተፈፀመበት ምክንያት አጸፋዊ እርምጃ መሆኑንም ነው አባ ማሴሬካ ያስረዱት።
የሀገሪቱ የኡጋንዳ ህዝቦች መከላከያ ሃይል (UPDF) አጎራባች ሃገር በሆነችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንዚህን ታጣቂዎች ማለትም ራሳቸውን የዲሞክራሲ ሃይሎች ህብረት ብለው ያሚጠሩትን አማፂያን ለማጥፋት እየተደረገ ባለው ዘመቻ ላይ የተሰማሩ ሲሆን አማፂያኑ ራሳቸው ‘ኡጋንዳን ለመዋጋት በኮንጎ እየሰለጠኑ ነው’ ሲሉ አብራርተዋል።
                “እርስ በርሳቸው ይዋጋሉ”
አማፂያኑ ባለፉት ዓመታት በኡጋንዳ እና በምስራቅ ኮንጎ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጥቃቶችን እና ግድያዎችን ፈጽሟል። አባ ማሴሬካም እንዳሉት በሁለቱም ሃገራት ድንበር አከባቢ ያሉ ህዝቦች በጣም አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል።
“በቅርቡ ኡጋንዳ ውስጥ ህዝቡን ለመግደል ከመጡ ሁለት ሳምንት እንኳ አልሆነም” ሲሉ አክለው ፥ “በዚህን ጊዜም በአዳሪ ትምህርት ቤት እና በተማሪዎቹ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ ፥ በኮንጎም እስከ አሁን ብዙ ግድያዎች ተፈጽመዋል” ብለዋል ካህኑ።
የኡጋንዳው ሊቀ ጳጳስ አብያተ ክርስቲያናትን እና ቀሳውስትን ኢላማ ያደረገ ጥቃት እንደደረሰባቸው አረጋግጠው እ.አ.አ. በ1996 አማፂ ቡድኑ ከተቋቋመ በኋላ በኡጋንዳ የሚገኝ ትምህርታዊ ጉባኤ ማዕከል ላይ የተፈፀመውን አስከፊ ጥቃት አስታውሰዋል።

የተባበሩት መንግስታት ሠላም አስከባሪዎች በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ

በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ ምን አይነት ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንደሚደረግ ተጠይቀው አባ አውገስቲን ሲመልሱ “የተባበሩት መንግስታት ሠላም አስከባሪ ጦር በስፍራው ቢገኝም ይሄ ነው የሚባል ተጨባጭ ሥራ እየሠራ አይደለም ፥ እንደ ኮንጎዎች ብዙ እየሰሩ ስላልሆነ በሃግሪቷ ውስጥ አሁንም ድረስ እጅግ በርካታ ሰዎች እየተፈናቀሉ ነው” ብለዋል.
“በእርግጥ ኮንጎ ውስጥ ሰዎች እየተሰቃዩ ነው ፥ ካህናት እንኳን ሳይቀር እየተገደሉ ነው ፥ በጣም አስፈሪ ነው ፥ እዚያ አከባቢ ብዙ ፍላጎቶች አሉ ፥ ነገር ግን እዚያ ያሉት ሠላም አስከባሪዎች ህዝቡን ብዙም እየረዱት አይደለም። ለዚህም ነው ኮንጎ ዉስጥ የሚኖሩ ሰዎች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ብዙም ምቾት ያልተሰማቸው” ብለዋል ካህኑ።
ባለፈው የካቲት ወር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለነበራቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ምስጋና ይግባውና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዚያ አከባቢ ስላለው ውጥረት ብዙም የሚያውቀው ነገር አልነበረም ፥ ከብጹዕነታቸው ጉብኝት በኋላ ግን ትንሽ ትኩረት ሊያገኝ ችሏል። የእሳቸው መልዕክት የእምነት እና የጸሎት ሰዎች ለሆኑት የተስፋና የድጋፍ መልእክት ማድረሱን አባ ማሴረካ ተናግረዋል።

ስለ ሠላም ውይይቶች ጥሪ

“ትግሉ ምንም መፍትሄ ስላላመጣ አሁን የሚያስፈልገው ነገር በድርድር ወደ መፍትሄ ሃሳብ መምጣት ነው” ያሉት ካህኑ ፥ “ምክንያቱም ደግሞ አሁንም ድረስ ሰዎች መሞታቸውን ቀጥለዋል” ብለዋል።
“የሠላም ንግግሮች የተለያዩ ቡድኖች ወደ አንድነት እንዲመጡ ፣ እንዲነጋገሩ እና ሃሳብ እንዲካፈሉ እንዲሁም እንዲስማሙ ያደርጋል ፥ ይህ ካልሆነ የሰዎች ሞት አሁንም ይቀጥላል ፥ መሳሪያ ምንም ነገር አይፈታም ፥ ጦርነቱ ምንም መፍትሄ ባለማግኘቱ የአካባቢው ሰዎች በየቀኑ እየሞቱ ነው” ብለው ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል።
“አንድ ላይ ተሰብስበው ከተስማሙ እና የሠላም ውይይቶችን ቢያደርጉ ምናልባት የሆነ ነገር ማምጣት ይችሉ ይሆናል” ያሉት አባ ማሰረካ በዚህ ጉዳይ ቤተክርስቲያኒቱም መሳተፍ አለባት ብለዋል።
በዚህ ትግል ውስጥ ያሉት ተዋናዮች እነማን እንደሆኑ ሲጠየቁ “የዲሞክራሲ ሃይሎች ህብረት አማፂያን ፣ የኮንጎ እና የኡጋንዳ መንግስታትን ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን እና አሜሪካውያን” መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የተረሳ ጦርነት

“በዚ ጉዳይ ሰዎች እንዲሳተፉ እና ሚዲያዎች ዜናውን የበለጠ እንዲያሰራጩ እጸልያለሁ ፥ ምክንያቱም በአንድ ወቅት በኮንጎ ውስጥ ያለው ጦርነት ‘የተረሳ ጦርነት’ ተብሎ ይጠራ ነበር” ብለዋል።
“በኮንጎ ሰዎች መሞታቸውን ቀጥለዋል ነገር ግን ይህ የሚዘገበው ጥቃት በሚፈጸምበት ጊዜ ብቻ ስለሆነ ጉዳዩ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት እንዲያገኝ ጥሪዬን አቀርባለው” በማለት አባ አውገስቲን ሃሳባቸዉን ደምድመዋል።
                      “የሚያወሩት ጥቃቱን ሲፈፅሙ ነው”
             ይህ በእንዲህ እንዳለ “እዚያ ሰዎች በዝምታ እየሞቱ ነው”
 

20 June 2023, 13:51