ፈልግ

የሰኔ 11/2015 ዓ.ም እለተ ሰንበት ቃል እግዚአብሔር እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የሰኔ 11/2015 ዓ.ም እለተ ሰንበት ቃል እግዚአብሔር እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ   (ANSA)

የሰኔ 11/2015 ዓ.ም እለተ ሰንበት ቃል እግዚአብሔር እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ምንባባት

1.    1ቆሮ 14፡1-25

2.    1ኛ ዮሐ 4፡1-8

3.    ሐዋ ሥ 14፡44-11፡10

4.    ዩሐንስ  15፡17-27

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ፣ ትእዛዜ ይህቺ ናት። ዓለም ደቀ መዛሙርትን መጥላቱ

“ዓለም ቢጠላችሁ፣ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ ዕወቁ።ከዓለም ብትሆኑ ኖሮ፣ ዓለም የራሱ እንደሆኑት አድርጎ በወደዳችሁ ነበር፤ ከዓለም ለይቼ ስለ መረጥኋችሁ የዓለም አይደላችሁም፤ ዓለም የሚጠላችሁም ስለ ዚሁ ነው። ‘አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም’ ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስታውሱ። እኔን አሳደውኝ ከሆነ፣ እናንተንም ያሳድዷችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው ከሆነም ቃላችሁን ይጠብቃሉ። የላከኝን ስለማያውቁ፣ በስሜ ምክንያት ይህን ያደርጉባችኋል። መጥቼ ባልነግራቸው ኖሮ ኀጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን ለኀጢአታቸው የሚሰጡት ምክንያት የላቸውም። እኔን የሚጠላ፣ አባቴንም ይጠላል። ሌላ ሰው ያላደረገውን በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ፣ ኀጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን እነዚህን ታምራት አይተዋል፤ ሆኖም እኔንም አባቴንም ጠልተዋል።ይህም፣ ‘ያለ ምክንያት ጠሉኝ’ ተብሎ በሕጋቸው የተጻፈው ቃል እንዲፈጸም ነው። “እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ፣ ከአብ የሚወጣው አጽናኙ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፣ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል። እናንተም ደግሞ፣ ከመጀመሪያው ከእኔ ጋር ስለ ነበራችሁ፣ ትመሰክራላችሁ።

የእለቱ የቃለ እግዚአብሔር ወንጌል አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ከጰራቅሊጦስ በኋላ ያለውን ሁለተኛ እለተ ሰንበት እናከብራለን። በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ የዕለቱ ንባባት አማካኝነት መልዕክቱን ያስተላልፍልናል። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክቱንም እንዲህ በማለት ይጀምራል፣ “ፍቅርን ተከታተሉ” ይለናል። ሁላችንም እንደምንረዳው ፍቅር የሁሉ ነገር መጀመሪያም መጨረሻም ነው። እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ምድር የላከው ለእኛ ለልጆቹ ካለው ፍቅር የተነሳ ነው፣ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስም ሕይወቱን አሳልፎ ለመስቀል የሰጠው ለአባቱና ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሳ ነው። ፍቅር ከሌለ ምንም የለም፣ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው የቆሮንጦስ መልዕክት ምዕራፍ 13፡1 ጀምሮ “ስለ ፍቅር” ብዙ ይናገራል እንዲህም ይላል፣ “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር  ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮህ ናስና እንደሚንሸዋሸው ጸናጽል ነኝ” ይላል። “ትንቢትም ቢኖረኝ ምስጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁል ባውቅ ተራሮችንም አስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” ይለናል። እንግዲህ ፍቅርን መከተል ማለት የፍቅር ውጤት የሆኑትን ነገሮች ሁሉ መያዝና በእነርሱም ውስጥ መኖር ማለት ነው። በፍቅር የሚኖር ሰው ይታገሳል በፍቅር የሚኖር ሰው ቸርነትን ያደርጋል በፍቅር የሚኖር ሰው አይቀናም፣ በፍቅር የሚኖር ሰው በራሱ ኃይል ብቻ አይመካም፣ አይታበይም በፍቅር የሚኖር ሰው የማይገባውን አያደርግም፣ አይበሳጭም፣ ተንኮል አያስብም። እንግዲህ ዛሬ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ  በቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት አድርጎ ይህንን ያሳስበናል። በመቀጠልም ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በልሳንና በትንቢት ስለመናገር ይናገራል። ሁለቱም ስጦታዎች ማለትም  በልሳን ወይም በትንቢት መናገር የሚመነጩት ከራሱ ከእግዚአብሔር ነው፣ “ሆኖም አንድ ሰው በልሳን ሲናገር ያንን ልሳን የሚተረጉም ሰው ከሌለ ያ የልሳን ቋንቋ የሚያበረታው የሚያፅናናው የሚያንፀው ያ በልሳን የተናገረውን ሰው ብቻ ነው”፣ ስለዚህ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለአብዛኛው ሰው መበረታታት መፅናናት መታነፅ ሲባል ልሳን ከመናገር በላይ  ትንቢት የመናገር ስጦታን ፈልጉ እሹ ይለናል። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በዚሁ በምዕራፍ 14፡5 ላይ እንዲህ ይለናል “ሁላችሁ በልሳን እንድትናገሩ እወድ ነበር፣ ትንቢትን ብትናገሩ ግን ልሳን ከመናገር የበለጠ እወድ ነበር፣ ምክንያቱም ማኅበሩ ይታነፅ ዘንድ ነው፣ ንግግሩም ባይተረጎም እንኳን በልሳን ከሚናገር ሰው ይልቅ ትንቢት የሚናገረው ይበልጣል” ይለናል። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ አንድ የሚጨምረው ነገር አለ፥ ይኸውም አንድ ሰው ልሳን ወይንም ትንቢት ከመናገሩ በፊት ሕይወቱ በፍጹም የተስተካከለና በእውነተኛ ክርስቲያናዊ መንፈስ የተገነባ ሊሆን ይገባዋል፣ ምክንያቱም የልሳንም ሆነ የትንቢት ሥጦታዎች ባለቤት ራሱ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ነው፣ ስለዚህ ማንኛውም ሰው ይህንን ጸጋ ከመቀበሉ በፊት ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር ቀጥተኛና የጠበቀ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል፣ ሕይወቱ በክርስቶስ መንፈስ የታነፀ ሊሆን ይገባል ።

በዛሬው በሁለተኛ መልዕክት ቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያ መልዕክቱ በምዕራፍ አራት ከቁጥር አንድ ጀምሮ ሐሰተኛ ነቢያቶች እንዳሉና ከበፊትም ጀምሮ እንደነበሩ መልካምና ከእግዚአብሔር የሆነውን እንደሚናገሩ አስመስለው የሐሰት ትምህርትን በመዝራት የሰይጣንን መንገድ እንደሚያስፋፉ ይነግረናል።

አንድ ሰው ትንቢት ወይንም ልሳን በሚናገርበት ጊዜ ያ የሚናገረው ቃል ቤተክርስቲያንን የሚያንጽ የሚያበረታ የሚያስተምር ከሆነና ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የአብ አንድ ልጅ መሆኑን የሚመሰክር ሰውም ሆኖ ወደ እኛ መምጣቱንና ከኃጢአታችንም ደሙን በማፍሰስ እንዳዳነን የሚመሰክር ከሆነ በእርግጥም ያ መንፈስ ከእግዚአብሔር መሆኑን ልንረዳ ይገባናል። ምናልባት ከዚህ በተቃራኒው የሚሄድ ከሆነ ደግሞ ትንቢቱም ሆነ በልሳን መናገሩ የሐሰት መሆኑን ተረድተን ልናወግዘው ይገባናል፣ ከዚህ ከሃሰት ትምህርት ልንሸሽ ይገባል። ይህንን በማስመልከት ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ በሁለተኛ መልዕክቱ እንዲህ ይለናል፣ “እንግዲህ እናንተ ወዳጆቼ ሆይ ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ በአመፀኞች ስህተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ፅናት እንዳትርዱ ተጠንቀቁ፣ ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በእየሱስ ክርስቶስ ፀጋና እውቀት እደጉ” ይለናል፣ ይህንንም ማለቱ በሌላ አነጋገር ከሐሰተኞች ነቢያት ራሳችሁን ጠብቁ በሐሰተኛ ትምህርታቸውም ተስባችሁ በእምነታችሁ አትሰናከሉ ማለቱ ነው። በመቀጠልም ቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ እግዚአብሔር  የፍቅር አባት የፍቅር መገለጫና እርሱ ራሱ ፍቅር ነው፥ ስለዚህ እኛም በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረናልና ከእግዚአብሔር ምንጋራው ነገር አለና እርስ በርሳችን እንዋደድ እንፋቀር በማለት ሐሳቡን ያካፍለናል። እውነት ነው እግዚአብሔርን የሚያውቅ ሰው በፍቅር ይኖራል በፍቅር ይመላለሳል፣ እርስ በርሱም ይከባበራል፣ ይተሳሰባል፣ ፍቅር በሞላበት መልኩ ደግሞ ይተራረማልም። ይህ ነው የእግዚአብሔርን ፍቅር በተግባር ላይ ማዋል፣ አለበለዚያ እንደው ለአፋችን ብቻ እግዚአብሔርን እንወዳለን ብለን ተግባራችን ግን ከዛ የተለየ ከሆነ፣ ገና በእርግጠም ይህ የእግዚአብሔር ፍቅር በውስጣችን አልገባም ማለት ነው። ቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያ መልዕክቱ 3፡18 ላይ እንዲህ ይለናል “ወዳጆቼ ሆይ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበታችን ብቻ አንዋደድ” ይለናል። ምክንያቱም በውስጣችን አለን የምንለው ፍቅር አንደው ለታይታና ለይስሙላ ብቻ ከሆነ፣ የያዝነው መስመር የተስተካከለ አይደለም፣ በዚህም እውነተኛ ደስታም ሆነ የመንፈስ እርካታ ልናገኘ አንችልም፣ ስለዚህ በፍጥነት ከዚህ አመለካከታችን ልንታረምና ወደ ትክክለኛ መስመር ልንመለስ ይገባናል። እግዚአብሔርን ማወቅ ይህ ነው በእግዚአብሔር ፍቅር መመላለስ ማለት ይህ ነው። በዛሬው በተነበበው በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 15 ላይም ቀደም ሲል በተነበቡት በቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲሁም በቅዱስ ሐዋርያው ዮሐንስ መልዕክት ላይ ስለ ፍቅር ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጠናል። “እርስ በርሳችን እንድንዋደድ” ይመክረናል። እርስ በርስ መዋደድ ማለት በመካከላችን ምንም ዓይነት ክፍተት አይፈጠር ማለት አይደለም፣ ቢሆን መልካም ነበር፣ ነገር ግን ልክ እንደመልካችን አስተሳሰባችንም የተለያየ ነውና፣ የተለያየ ሐሳብ የተለያየ አመለካከት ሊኖረን ይችላል፣ ነገር ግን በተረጋጋ መንፈስ በመነጋገር ችግሮችን ማስወገድ፣ ልዩነቶችን ማጥበብ፣ አንድነታችንን ማሳደግ፣ ይህ ነው እርስ በእርስ መዋደድ ማለት፣ ይህ ነው በእግዚአብሔር ፍቅር መመላለስ ማለት። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ፍቅር መኖር ቀላል ነገር እንዳልሆነ ይነግረናል፣ በውስጡ ብዙ መሰናክሎች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን እንዚህን ሁሉ በጽናት ማለፍ ያስፈልጋል ይለናል። ሰው በእግዚአብሔር ፍቅር ለመመላለስ ሲጣጣር ብዙ መከራና ግፍ ሊገጥመው ይችላል፣ ነገር ግን ይህም ቢሆን በተርጋጋ መንፈስ ማሳለፍ እንደሚገባ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ያሰምርበታል፣ እንዲህም ይለናል “እኔን እንዳሳደዱኝ እንዲሁም እናንተንም ያሳድዷችኋል” ይለናል። ስለ ክርስቶስ ብሎ መሰደድ ሁላችንን የእርሱ ስቃይ የእርሱ መከራ ተካፋዮች ያደርገናል፣ በዚህም ምክንያት የመከራው ተካፋዮች ሆነናልና በመጨረሻም የክብሩና የደስታውም ተካፋዮች እንሆናለን፣ በእግዚአብሔርም ቤት በደስታና በፍቅር እንኖራለን። እመቤታችን ድንግል ማርያም ዘወትር የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ለመፈጸም ትተጋ እንደነበር ዛሬ ደግሞ እኛ ልክ እንደሷ የልጇን ቃል ለመጠበቅና በቃሉም መሠረት ለመኖር የምንችልበትን ጸጋና በረከት ከአንድያ ልጇ ታማልደን፣ የሰማነውን ቃል በልባችን እንድንይዝ በተግባር እንድናውለውም የምያስችለንን ብርታት ታሰጠን።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ ሬዲዮ ቫቲካን

 

 

17 June 2023, 15:57