ፈልግ

መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ  ዴ ላ ሳሌ ልጅ ይዞ የሚያሳይ ሐውልት መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ዴ ላ ሳሌ ልጅ ይዞ የሚያሳይ ሐውልት 

ላሳሊያውያን በፊሊፒንስ የህግ ቁጥጥር ስር ያሉ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን እያገዘ መሆኑ ተገለጸ

በፊሊፒንስ የሚገኘው ‘ላ ሳሌ ባሃይ ፓግ-ሳ’ የሚባለው አጋዥ የሌላቸው እና የህግ ቁጥጥር ሥር የዋሉ እና አጋዥ የሚያስፈልጋቸው ህፃናት ማቆያ እና የለውጥ ማእከል ዳይሬክተሮች እነዚህን ታዳጊዎች ሁሉም ሰው እንዲረዳቸው እና በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነው እንዲያድጉ ትምህርት እና እድሎችን በመስጠት ተስፋ እንዲኖራቸው ያበረታታሉ።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ይህ ‘የተስፋ ቤት’ (በታጋሎግኛ “ባሃይ ፓግ-አሳ”) የሚባለው ተቋም ከሕግ ቁጥጥር ውስጥ ያሉ ሕፃናት የሚቆዩበት የለውጥ ማዕከል ነው። በፍርድ ቤት ትዕዛዝ አቤቱታ የቀረበባቸው ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት የሚረዱበት ማዕከሎች የተገነቡት እና የሚገኙት ፊሊፒንስ ውስጥ በሚገኙ በሁለት የካቶሊክ ላ ሳሌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው።
የላሳሊያን አባል የሆነው ወንድም ጓስ ቦከር ፥ ባኮሎድ ከተማ የሚገኘው የቅዱስ ላ ሳሌ ዩኒቨርሲቲ እና ዳስማሪናስ ከተማ ዉስጥ የሚገኘው የዲ ላ ሳሌ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የሆነ እና የእነዚህ የተስፋ ቤት የሚባሉት በፊሊፒንስ ሃገር ውስጥ የሚገኙት ተቋማት መስራቾች ውስጥ አንዱ ነው።
ባኮሎድ ከተማ ዉስጥ ያለው የቅዱስ ላ ሳሌ ዩኒቨርሲቲ የወጣቶች ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ፊሊፒናዊት ወይዘሮ አና ቤሳ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለፁት ለ11 ዓመታት ተስፋ ቤት በሚባለው በዚሁ ተቋም ውስጥ እንዳገለገሉ ተናግረዋል።
“ማዕከሉ እ.አ.አ. በ 2002 የተመሰረተ ሲሆን ፥ አሁን ያሉት የወጣቶች ፍትህ ማሻሻያ ህጎች ገና አልነበሩም ነበር ፥ ስለዚህም ብዙ ቁጥር ያላቸው ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህጻናት ብዙውን ጊዜ አዋቂዎች የሚታረሙበት እና የሚቆዩበት ስብስብ ውስጥ ይታሰሩ ነበር” ብለው በመቀጠልም “ይህ የወጣቶች ማዕከል ሲቋቋም ትልቅ እፎይታን አስገኝቶ ነበር። በፊሊፒንስ ያሉ የማህበራዊ እና የፖለቲካ መሪዎች የህግ ጥላ ሥር መሆን የሚገባቸው ህጻናትን ከእስር ቤት የሚያስወግድ ህግ ለማፅደቅ እና ማህበረሰቡን መሰረት ያደረገ አሰራር እንዲሁም የወጣት አጥፊዎችን ለመጠበቅ ፣ ለመምራት እና አቅጣጫ ለማስያዝ የጣልቃ ገብነት እና የማገገሚያ ፕሮግራሞችን ለማቋቋም እየሰሩ ነበር።
ዳስማሪናስ ውስጥ የሚገኘው የወጣቶች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የሆነው ፊሊፒናዊው አቶ ጆሴ ሪቼ ቦንግካሮን ልጆቹን መንከባከብ ወሳኝ ነገር እንደሆነ ሲያብራሩ “ህፃናቱን ከማሰር ይልቅ ሁለንተናዊ የወደፊት ህይወታቸውን የሚቀይር ፕሮግራም ዉስጥ እንዲያዙ ፣ ብቁ እና ቁርጠኛ የሆነ የህግ ድጋፍ እንዲሰጣቸው እና ከእስር ከተፈቱ በኋላ ማዕከሉ ውስጥ ያገኙትን የስልጠና ፕሮግራም እንዲተገብሩ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው” ሲሉ ለቫቲካን ዜና ተናግረዋል።

ተስፋን ማዳበር

የቅዱስ ላ ሳሌ ዩኒቨርሲቲ የወጣቶች ማዕከል ፊሊፒናዊቷ ዳይሬክተር እንዳሉት በልጆች ማመን እና ለእነሱ እድሎችን መፍጠር ለወደፊቱ ተስፋን ይሰጣል በማለት ገልፀው “ልጆች እና ወጣቶች ምግብ እና መጠለያ የሚያስፈልጋቸውን ያህል ተስፋን አበክረው ይፈልጋሉ” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። “ተስፋ በርትተን እንድንታገል እና ዓለም የሚፈልጋቸውን ሰዎች አይነት እንድንሆን ምክንያት ይሰጣል ፥ ተስፋ ህይወታችን ትርጉም እንዲኖረው ያደርጋል ፥ እንዲሁም በጨለማው ውስጥ ብርሃንን እንድናይ ያደርገናል” ብለዋል።
በማዕከሉ ዉስጥ ያሉ ልጆች የሚሉትን መሪ ቃል የሆነውን ደግመው ተናግረዋል ፥ “ተስፋ እግዚአብሔር ህይወታችንን የሚመራበት እና እያንዳንዳችንን እንዲሁም ዓለምን የሚያሻግርበት ዕቅድ እንዳለው የሚገልጽበት የእምነት ቃል ኪዳን ነው። የባሃይ ፓግ-አሳ ነዋሪዎች የህይወት መሪ ቃል የሆነውም እንደሚያሳየው “ያለፈውን መለወጥ አንችልም ነገር ግን የወደፊቱን መለወጥ እንችላለን” ይላል።
ወይዘሮ ቤሳ አክለውም “ልጆች በድህነት ፣ በእኩዮች ተጽዕኖ ፣ በተቋረጠ ወይም በቂ ትምህርት ባለማግኘታቸው እና ሥራ በሌላቸው ቤተሰቦች ተፅእኖ ምክንያት በህገ ወጥ ተግባራት ውስጥ ይሳተፋሉ ፥ እነዚህን ልዩ የወጣት ቡድኖች መርዳት አስፈላጊ ነው ምክንያቱም እነሱም የሁኔታዎች ሰለባ በመሆናቸው ህግን አክባሪ ፣ ውጤታማ እና በራስ የሚተማመኑ ግለሰቦች ለመሆን ሁለተኛ እድል ሊሰጣቸው ይገባቸዋል” በማለትም አብራርተዋል።
ዳስማሪናስ ከተማ ዲ ላ ሳሌ ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ ያለው ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ቦንግካሮን በማህበረሰቡ ውስጥ ተስፋን ማስፋፋት ያለውን አስፈላጊነት ገልጸዋል። “ወጣቶችን ተስፋ እናደርጋለን ፥ ምክንያቱም እነሱ ራሳቸው የተስፋ ተሸካሚዎች ናቸውና ፥ ይህም ተቋም የተመሰረተው በአንድ ምክንያት ብቻ ነው ፥ ለወጣቶች ተስፋ ለመስጠት ነው ፥ አንዴ ወደ ማዕከሉ ከመጡ ፥ ተስፋ እንዲኖራቸው እናደርጋለን” ብለዋል። አክለውም “ተቋሙ ለሰዎች ተስፋ ለመስጠት የእግዚአብሄርን ቃል ይከተላል” ብለዋል። “ኢየሱስ በምሕረቱ እና በፍቅሩ ለሰው ልጆች የሚያመጣው መልእክት ተስፋ ነው” ብለዋል አቶ ቦንግካርን። “ተስፋን በጽናት መጠበቅ በክብር እና በአክብሮት ወደ ፊት እንድንጓዝ የሚያደርገን ነው። ለተቸገሩ ሰዎች ፣ በአካባቢው የመጨረሻ ደረጃ ላይ ላሉ ሰዎች ምላሽ እንድንሰጥ የሚረዳን ተስፋ ነው
የወጣቶች ማዕከሉ መቋቋም ህብረተሰቡ ሁል ጊዜ ህጻናትን እንዲጠብቅ መንገዱን ከፍቷል ፥ በተለይም የህግ ጥሰት ቢፈጽሙም በአብዛኛው የቤት ውስጥ ችግሮች ሰለባ ስለሆኑ እነዚህን ጥሰቶች እንዲፈጽሙ ምክንያት ሆኗቸዋል” በማለት ተናግረዋል። “ማዕከሉ ህብረተሰቡ አንድ ነገር ለማድረግ -በተለይ በትምህርት - የህጻናትን መብት ለማስከበር እና ተስፋ እንዳይቆርጥ አይን መክፈቻ ሆኖ አገልግሏል”

ለልጆች ትምህርት እና እንክብካቤ

ዳይሬክተሮቹ በወጣት ማዕከሉ ውስጥ ያሉ ህጻናትን በማስተማር ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል። “እንደ ላስሊያን ተቋም ትምህርትን ለነዋሪዎች የምናበረክተው በጣም አስፈላጊው ስጦታችን ነው። ሁሉም ነዋሪዎች የመማር እድል ተሰጥቷቸዋል” ብለዋል ሚስተር ቦንግካሮን። “እንደ አጠቃላይ የሌሎች መርሃ ግብሮች አካል ፥ ከየራሳቸው ማህበረሰቦች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር እንደገና ለመዋሃድ ዝግጁ ሲሆኑ እና እንዲዘጋጁ ለመርዳት በተለያዩ ስልጠናዎች ውስጥ ያልፋሉ” ብለዋል።
የፊሊፒንስ ዳይሬክተሩ አክለውም “ህብረተሰቦች ውጤታማ ፣ ሰብአዊነት ያላቸው እና የወደፊት ተኮር እንዲሆኑ ለማድረግ ልንሳተፍባቸው የምንችላቸው የህጻናት እና ወጣቶች ትምህርት እና እንክብካቤ በጣም አስፈላጊ ሥራዎች ናቸው" ብለዋል።
አቶ ቦንግካሮን የማዕከሉ ስራዎች የሚያንጸባርቁት የላስሊያን ካቶሊካዊያን ማንነት ፣ ሌሎችን የመውደድ እና በማገልገል ጥሪ የሚኖሩበት መንገድ ነው ብለው ያምናሉ። እንደ የትምህርት ተቋም ግባችን ተማሪዎቻችንን ማስተማር ብቻ ሳይሆን እንዲያገለግሉ እና የአብሮነት ተግባራትን እንዲያሳዩ እድሎችን መስጠት ነው።
ተቋሙ እርስ በርሳችን የመተሳሰብ ሚናንም ጎላ አድርጎ ገልጿል ፥ “ምክንያቱም እኛ በተፈጥሯችን እርስ በርሳችን እንድንተሳሰብ ነው የተፈጠርነው ፥ ይህ ጥሪያችን ነው። የመውደድ እና የመተሳሰብ ጥሪያችን ከግብ የሚደርሰው የሁሉንም ሰው ክብር እንደ እግዚአብሄር አምሳል እና አምሳያ የተፈጠሩትን ፍጡራንን ከጠበቅን ብቻ ነው” ይላሉ።
ወይዘሮ ቤሳ የሰው ልጅን የመንከባከብን አስፈላጊነትንም እንዲህ በማለት ጠቁመዋል “የግለሰቦችን ህይወት እንደ አዲስ ለመፍጠር ይረዳል ፥ ሌሎችንም ከፍ ወዳለ ደረጃ ያሸጋግራል ፥ በዚህ መንገድ ነው የማህበረሰቦች ለሰው ልጅ ዕድገት እና ፍፃሜ የሚረዱ አዎንታዊ አስተሳሰቦች የሚዳብሩት” ሲሉም ተናግረዋል። “ሰዎች እንደመሆናችን መጠን የእግዚአብሔር ወንድ ልጆች እና ሴቶች ልጆች ነን ፥ ስለዚህም በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታወቅ ክብር አለን ለሚለው እምነት ምላሽ የሚሰጠው ይህን በማድረጋችን ነው” በማለትም ሃሳባቸውን አጠናክረዋል።

የወጣቶችን እምነት ማጠናከር

የማዕከላቱ ዳይሬክተሮች የህፃናትን የካቶሊክ እምነት ስለማጠናከርም ተወያይተዋል።
ፊልፒናዊው የማእከሉ ተባባሪ ዳይሬክተር እንዳሉት “የወጣቶች ማዕከሉ ሁልጊዜም ቤተክርስቲያኒቱ ስለመረዳዳት እና ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች በተለይም ኢየሱስ ስለሚወዳቸው ልጆች በሚያስተምረው ነገር ይመራሉ” ሲሉ አጋርተዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም ልጆች እግዚአብሔር በሚወደው ሥራ ውስጥ እንዲሳተፉ እድል እንደሚሰጡ ተናግረዋል ፥ ምክንያቱንም ይላሉ “የቤተክርስቲያን ትምህርቶች በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆነ መልኩ በማዕከሉ ሥራ ውስጥ እየተተገበሩ ናቸው ፥ እያንዳንዱ የመርሃ ግብሩ ክፍል የእያንዳንዱ ነዋሪ መንፈሳዊ እድገት ነው” በማለት ተቋሙም ከቤተክርስቲያኒቷ ጋር የተዋሃደ መሆኑንም ጠቁመዋል።
“የቅዱስ ላ ሳሌ ዩኒቨርሲቲ የተስፋ ቤት ተግባራት የካቶሊካዊነት አካላዊ እና መንፈሳዊ የምሕረት ሥራዎች ቀጥተኛ መገለጫ ነው። ለሚያገለግላቸው ወጣቶች እና እነዚያን አገልግሎቶች ለሚሰጡ ሰራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች የመዳን መንገድን ይሰጣል። የእምነት ማስረጃ ሆኖም ይቆማል” በማለት ወይዘሮ ቤሳ አብራርተዋል።
“የማዕከሉ መርሃ ግብሮች እና ተግባራት እያንዳንዱ ነዋሪ በእምነት እና በመንፈሳዊነት እንዲያድግ እድል ይሰጣል ፥ የመንፈስ ቅዱስን የለውጥ ተግባር ለሚመሰክሩት ለትልቁ ማህበረሰብ አባላትም ተመሳሳይ እድገትን ይሰጣል” ብለዋል።

እርስ በርስ መረዳዳት

ዳይሬክተሮቹ እንደተናገሩት ማዕከላቱ ህጻናትን ለመርዳት እና ለመምራት እንደ ተቋሙ ሠራተኞች ፣ ማህበራዊ ሠራተኞች ፣ የደህንነት ሠራተኞች ፣ አስተማሪዎች ፣ የላሳሊያን ወንድሞች ፣ በጎ ፈቃደኞች እና ሌሎችም ሆነው በሚያገለግሉ በተለያዩ ሰዎች የሚተዳደሩ መሆናቸዉንም ገልጸዋል።
አቶ ቦንግካሮን አክለው “ይህ ተቋም ሰዎች እኛ ለእነዚህ ልጆች የምንሰጠውን አገልግሎት ለራሳቸው መጥተው እንዲያዩ ይፈቅድላቸዋል ፥ ለነዋሪዎች ፕሮግራሞቻችንን ለማጠናከር በሚረዱ መንገዶች ድጋፍ እንዲሆኑ እና እንዲረዷቸው እድሎችን እንሰጣቸዋለን” ብለዋል።
ዳይሬክተሮቹ በአሁኑ ወቅት በማዕከላቱ ውስጥ እያጋጠሟቸው ያለውን ተግዳሮቶችንም አካፍለዋል።
ወይዘሮ ቤሳ እንዳሉት ባካሎድ ከተማ በቅዱስ ላ ሳሌ ዩኒቨርሲቲ ስር ስላለው ተቋማቸው ሲያስረዱ “ማዕከሉ ለ22 ዓመታት ሲሠራ የቆየ ሲሆን ከተለያዩ የኔግሮስ ኦክሳይደንታል ከተሞች እና ማዘጋጃ ቤቶች ወደ 200 የሚጠጉ ነዋሪዎችን ረድቷል። ማዕከሉ ካሉባቸው ተግዳሮቶች መካከል የምግብ ፣ የህክምና ፍላጎቶች እና ትምህርታዊ አገልግሎቶች ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ ነው ፥ ምክንያቱም ክንዋኔያችን ሁሉ በዕርዳታ ላይ የተመሰረተ ነው። እስካሁን ድረስ ማዕከሉ በዩኒቨርሲቲው በኩል የምግብ ወጪውን ለመሸፈን የሚረዱ መደበኛ ለጋሾችን እየፈለገ ይገኛል” ብለዋል።
ዳስማሪናስ ከተማ የሚገኘው የዲ ላ ሳሌ ዩኒቨርሲቲ ‘የተስፋ ቤት’ ዳይሬክተር የሆኑት ቦንግካሮ ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች ሲገልፁ ፥ “ይህ ተቋም ለ11 ዓመታት ሲሰራ እንደቆየ እና እንክብካቤ እንዲሰጣቸው ለመጡ የአከባቢው ነዋሪዎች የመለወጥ እድሎችን ለመስጠት ቁርጠኛ ቢሆንም ፥ በአጠቃላይ ሥራዎቹ ላይ ተግዳሮቶች አጋጥሞታል ፥ እኛ የምንተዳደረው በፊሊፒንስ የህጻናትን ጥቅም በሚያስጠብቁ በፊሊፒንስ ህጎች ነው ፥ በማህበራዊ ደህንነት እና ልማት ዲፓርትመንት በኩል - እንዲሁም ተቋሞቻችንን በጥሩ ሁኔታ ማቆየት እና ፕሮግራሞቻችንን የነዋሪዎች ፍላጎት በዘላቂነት ለመፍታት መትጋት እንደሚያስፈልገን ተገንዝበናል” በማለት አብራርተዋል።


ለወደፊት ትውልድ መንገዶችን ማመቻቸት


ሚስተር ቦንግካሮን እንዳሉት ተቋሙ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት እና ተስፋውን የበለጠ ለማስፋት እንደሚሰሩ ገልፀው ፥ “ከአሁኑ የተቋሙ ፕሬዝዳንት ከሆኑት ወንድም ፍራንሲስኮ ዴ ላ ሮሳ ስድስተኛ ጋር በመሆን ወንድም ጉስ የጀመሩትን የተስፋ ሌጋሲያቸውን ለመደገፍ እና ለማስቀጠል ቁርጠኛ ነኝ ፥ በተቋሙ በኩል ተስፋ እና እምነትን ለማስፋፋት የማያቋርጥ የእድሎች አቅርቦት እንደሚኖር እርግጠኞች ነን” በማለት አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
“ለልጆች የምናደርገው መልካም ነገር ፥ ለህብረተሰቡ እና ለቤተክርስትያን እንዳደረግን ይቆጠራል” ሲሉም አጋርተዋል።
ወይዘሮ ቤሳ ሌሎችም ልጆችን በመርዳት ላይ እንዲሳተፉ ይጋብዛሉ።
“እዚህ የተጀመረውን ሥራ በእምነት እና በከፍተኛ ፍላጎት በመቀጠል የወደፊቱን ተስፋ እና እምነት የበለጠ ማስፋፋት እንችላለን” ሲሉም ያበረታታሉ። የህግ ቁጥጥር ስር የገቡ ህጻናትን ለመርዳት የተደረገውን ጥሪ በመመለስ እና ከልምዶቻችን እና የተስፋ ታሪኮች ውጪ ያሉ ህብረተሰቦች ጋር በመነጋገር ሁላችንም እዚህ ያገኘነውን ተስፋ እና እምነት ከአከባቢያችን ባሻገር ማሰራጨት እንችላለን”
ወጣቶችን ለማሻገር ባለን ተልዕኮ ውስጥ ሌሎችን የማካተት እና የማቀፍ ተግባርን እንሻ” በማለት ቃለ ምልልሱን አጠናቀዋል።
 

13 June 2023, 15:52