ፈልግ

የኮንሶላታ ሚሲዮናዊያን የኮንሶላታ ሚሲዮናዊያን  

የኮንሶላታ ሚሲዮናዊያን አፍሪካዊ ካኅንን የማኅበራቸው የመጀመሪያ አለቃ አድርገው መረጡ

ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም አገራት ውስጥ በወንጌል ተልዕኮ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የአጽናኟ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “ኮንሶላታ” ሚሲዮናውያን አፍሪካዊ ተወላጅ የሆኑትን አባ ጄምስ ሌንጋሪንን የማኅበራቸው ጠቅላይ አለቃ አድርገው መርጠዋል። ሮም በሚገኝ ጠቅላይ ቤታቸው ለሳምንታት ያህል ጠቅላላ ስብሰባቸውን ያካሄዱት የማኅበሩ አባላት ሰኔ 5/2015 ዓ. ም. ኬንያዊውን ተወላጅ አባ ጄምስ የገዳማቸው አሥረኛው ጠቅላይ አለቃ አድረገው መርጠዋቸዋል። አባ ጄምስ በዚህ የጠቅላይ አለቃነት አገልግሎት እስከ 2021 ዓ. ም. ድረስ እንደሚቆዩ የተገለጸ ሲሆን ከምርጫ በኋላ ባደረጉት ንግግር "በተሰጠኝ የአገልግሎት አደራ ማኅበራቸውን እና ቤተ ክርስቲያን በትጋት ለማገልገል እሞክራለሁ" ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሰኞ ሰኔ 5/2015 ዓ. ም. ጠዋት የማኅበራቸው የጠቅላላ ምዕራፍ ስብሰባን ለማካሄድ የተሰበሰቡት 40 አባላት በአሥራ አራተኛው የጠቅላላ ምዕራፍ ስብሰባ ኬንያዊ ተወላጅ የሆኑ አባ ጄምስ ቦላ ሌንጋሪንን በኮንሶላታ ሚሲዮናውያን ታሪክ አሥረኛ ጠቅላይ አለቃ አድርገው መርጠዋል። አባ ጄምስ የኮንሶላታ ሚሲዮናውያን ማኅበር በብጹዕ አባ ጁሴፔ አላማኖ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1901 ዓ. ም. ከተመሠረተ ወዲህ ለጠቅላይ አለቃነት የተመረጡ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሲሆኑ፥ ከ2015 እስከ 2021 ዓ. ም. (እ. ኢ. አ) ድረስ የሚቆየውን የጠቅላይ ሃላፊነት አደራን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ማኅበርን እና ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል

“ከሁሉ አስቀድሜ ሕይወትን ለሰጠኝ እግዚአብሔር ምስጋና አቀርባለሁ፤ በሕይወት ለሌሉት ወላጆቼ እና የኮንሶላታ ሚሲዮናውያን የጥሪ ጸጋ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብለዋል። አባ ጄምስ አክለውም "ዛሬ ወንድሞቼ ይህን አገልግሎት በአደራ ሰጥተውኛል፤ ስለዚህ ማኅበርን እና ቤተ ክርስቲያን እንዳገለግል የተሰጠኝን አደራ በጥሩ ሁኔታ ለመወጣት እሞክራለሁ፥ ለጣሉብኝ እምነትም አመሰግናለሁ፤ ሁሉም ሰው ለእኔ እና ለመላው ማኅበር እንዲጸልይ እጠይቃለሁ” ካሉ በኋላ ዘመኑን በሚገባ በመረዳት እግዚአብሔር የሰጠንን ሰዎች ድምጽ ማድመጥ እንቀጥላለን” ብለዋል። ማኅበሩ አባ ጄምስን በአገልግሎት የሚያግዙ አራት አማካሪዎችን በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ መርጦ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

ዓለም አቀፍ የገዳማውያን ማኅበር ነው!

በማኅበሩ ደንብ ቁ. 117 መሠረት፥ “የማኅበሩ መሥራች አባትን በመተካት በእያንዳንዱ ሚስዮናዊ፣ በማኅበሩ አካሄድ፣ በየአገራቱ በሚገኙ የማኅበሩ አባላት እና ሥራዎቻቸው ላይ ሥልጣን ያለው፤ የተቋሙን ቤተ ክህነታዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎትን በመወከል፥ የእያንዳንዱ ሚሲዮናዊ እና የማኅበር አንድነት፣ መንፈሳዊ ሕይወት እና ሐዋርያዊ ተግባርን የማሳደግ ኃላፊነት ያለበት ነው። የኮንሶላታ ሚሲዮናውያን ማኅበር በ122 ዓመታት ታሪኩ ዛሬ ከ30 ሀገራት የተውጣጡ 906 ሚስዮናውያን ያሉት እና በ231 የማኅበሩ ቤቶች ውስጥ ማለትም በአፍሪካ፣ አሜሪካ፣ በእስያ እና በአውሮፓ ውስጥ በሚገኙ 29 አገራት ውስጥ የሚገኝ ዓለም አቀፍ ማኅበር እንደሆነ ይታወቃል።

አዲስ የተመረጡት “የኮንሶላታ” ማኅበር ጠቅላይ አለቃ አባ ጀምስ ቦላ ሌንጋሪን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሚያዝያ 15/1971 ዓ. ም. ኬንያ ውስጥ ማራላል በተባለ አካባቢ ተወለዱ ሲሆን፥ የ “ኮንሶላታ” ሚሲዮናውያን ማኅበርን በመቀላቀል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1990 እስከ 1993 ዓ. ም. ድረስ ናይሮቢ በሚገኘው የ “ኮንሶላታ” ዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት ገብተው የፍልስፍና ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ነሐሴ 6/1994 ዓ. ም. በኬንያ ሳጋና የአንድ ዓመት የሙከራ ጊዜን ከጨረሱ በኋላ የመጀመሪያ መሃላ አድርገዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1994 እስከ 1997 ዓ. ም. በእንግሊዝ ቶቴሪጅ የነገረ መለኮት ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ ከዚያም ሮም በሚገኝ ጎርጎሮሳዊ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በሚሲዮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያን ሐምሌ 18/1999 ዓ. ም. ዋምባ በተባለ የኬንያ ግዛት የክኅነት ማዕረግን ተቀብለዋል። ጣሊያን ውስጥ ባደረጉት የመጀመሪያ የአገልግሎት ዓመታት ውስጥ ሚሲዮናዊ ተንከባካቢ እና ሮም ውስጥ በሚገኝ በብራቬታ ዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት ውስጥ የተማሪዎች የክኅነት ጥሪ መሪ በመሆን አገልግለዋል።

በኋላም ወደ ትውልድ አገራቸው ኬንያ ተመልሰው በማታሪ በሚገኝ የክኅነት ትምህርት ጀማሪዎች ቤት አለቃ እና የቋንቋ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል። ቀጥለውም ኬንያ ውስጥ ለምትገኛ የአጽናኟ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መቅደስ ዋና አስተዳዳሪ እና የማኅበራቸው የኬንያ ክልል አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል።ያለፈው የመጨረሻ ጠቅላላ ምዕራፍ ጉባኤ ከተካሄደበት ከ2017 ዓ. ም. እስከ 2023 ዓ. ም. ድረስ የማኅበሩ ምክትል የበላይ አለቃ በመሆን ማገልገላቸው ታውቋል። ሮም በሚገኝ ጠቅላይ ቤታቸው ውስጥ ለሳምንታት ሲካሄድ የቆየው ጠቅላላ ጉባኤ ሰኔ 5/2015 ዓ. ም. ኬንያዊ ተወላጅ አባ ጄምስ ሌንጋሪንን የኮንሶላታ ዓለም አቀፍ ማኅበር አሥረኛው ጠቅላይ አለቃ አድርጎ መርጧቸዋል።

13 June 2023, 17:19