ፈልግ

“ፍቅር ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት” የተባለ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ “ፍቅር ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት” የተባለ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ  

ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ እንቅስቃሴ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሚደረገውን ድጋፍ እንደሚያበረታታ ገለጸ

በፊሊፒን “ፍቅር ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት” የተባለ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ሰብሳቢ አቶ ፊሊፒኖ ጆሴ ማሪዮ ማክሲሚያኖ እንቅስቃሴያቸው ለዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሚደረገውን ድጋፍ እንደሚያበረታቱ ገለጹ። አቶ ማክሲሚያኖ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ የእንቅስቃሴያቸው ግብ መላውን ካቶሊካዊ ምዕምናን እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማት በመድረስ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ለእያንዳንዱ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ድጋፍ እንዲሰጡ ማበራታታት እንደሆነ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በፊሊፒንስ መዲና ማኒላ የሚገኘው “ፍቅር ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት” የተባለ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ሰብሳቢ አቶ ማክሲሚያኖ ሰኔ 8/2015 ዓ. ም. ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ከመሠረት የጀመረው ዓለም አቀፍ የካቶሊክ እንቅስቃሴ በጳጳሶቻቸው እየተመሩ በሲኖዶሳዊ ሂደት ላይ የሚገኙ ቀሳውስትን፣ ገዳማውያንን እና ገዳማውያትን፣ የምዕመናን መሪዎችን እና ወጣቶችን እንደሚያሳትፍ ገልጸዋል።

አቶ ማክሲሚያኖ አክለውም እንቅስቃሴያቸው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዕድገት ለምዕመናን ለማስተዋወቅ እና ለማስረዳት ሁሉንም ዓይነት አወንታዊ ልምዶችን፣ መንፈሳዊ ሥፍራዎችን እና ዘዴዎችን እንደሚጠቀም ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በተመለከተ፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ፣ “ከፍቅር የሚገኝ ደስታ” “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ፣ “የባሕል ጠባቂዎች” ፣ “ወንጌልን ለአህዛብ ስበኩ” የሚሉትን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናትን እና ሲኖዶሳዊነትን በማስመልከት ያቀረቡትን አስተምህሮችን እንዲሁም ሌሎችንም ወደ ሁሉ ዘንድ ማድረስ እንደሆነ አስረድተዋል። የዓለም አቀፍ እንቅስቃሴያቸው ሌላኛው አስፈላጊነት ክርስቲያን ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ ያላቸውን ሚና እና ተሳትፎ ማሳወቅ እንደሆነ አቶ ማክሲሚያኖ ገልጸዋል።

እንቅስቃሴያቸው ከሲኖዶሳዊነት እንደ ጀመረ የገለጹት አቶ ማክስሚያኖ፥ “ፍቅር ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት” የተባለ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2021 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከተጀመረው የሲኖዶሳዊነት ሂደት ጠቃሚ ፍሬዎች መካከል አንዱ እና በኅብረት የመጓዝን ታላቅነት የሚደግፍ መሆኑን ገልጸው፥ በሲኖዶሳዊ ሂደት ውስጥ ዘመኑን በሚገባ መገንዘብ እና ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ መኖር እንደሚያስፈልግ መሰማታቸውን ተናግረው፥ ከመሠረት የጀመረው እንቅስቃሴያቸው ምዕመናንን ማዕከል ማድረጉን አስረድተዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን

እንቅስቃሴው በፊሊፒንስ መጀመሩን የገለጹት አቶ ማክሲሚያኖ፥ የእንቅስቃሴውን ግቦች ለማሳካት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ሰዎች በኅብረት እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል። በእንቅስቃሴው ውስጥ ከጃፓን፣ ከፓፑዋ ኒው ጊኒ እና ከፊሊፒንስ የተወጣጡ አማካሪ ጳጳሳት የሚገኙበት መሆኑን ገልጸው፥ ከጣሊያን፣ ከስፔን፣ ከፖርቱጋል፣ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከኢንዶኔዢያ እና ከኒውዚላንድ የተመረጡ በርካታ ሰብሳቢዎችን ጨምሮ አንድ የማኅበር ጠቅላይ አለቃ፣ ሦስት የማኅበር የአውራጃ አለቆች፣ በርካታ የብሔራዊ ካቶሊክ ድርጅቶች ፕሬዚዳንቶች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

የእንቅስቃሴው ሰብሳቢዎች፣ አጋሮች፣ በጎ ፈቃደኞች እና አማካሪዎች ለቅድስት እናታችን ቤተ ክርስቲያን ክብር ያላቸው፣ ለቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ለሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ንፁህ ፍቅር እና ጥልቅ አክብሮት ያላቸው፣ የሮም ጳጳስን ከመውደድ እና ከመደገፍ በቀር ከግል ፍላጎት እና ምኞት ነፃ መሆናቸውን አስረድተዋል። እንቅስቃሴው ትምህርታዊ የሆኑ ሐዋርያዊ አስተምህሮዎችን ለሌሎች በማካፈል፣ ርኅራሄን በማሳየት እና የጸሎት ድጋፎችን በማድረግ የእምነት ብርሃን በመሆን ለብዙ ክርስቲያን አማኞች ትልቅ የእምነት፣ የተስፋ እና የአብሮነት ችቦ ሆኖ እንደሚያገለግል አቶ ማክሲሚያኖ ገልጸው፥ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለው የጋራ ጥረት ለካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አባት ብዙ ደስታን እንደሚሰጥ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ሕዝቦችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መምራት

ዓለም አቀፋዊ  እንቅስቃሴው ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያበረታታ መሆኑን የተናገሩት አቶ ማክሲሚያኖ፥ “ከአራቱ ዓላማዎች መካከል አንዱ ዶክትሪን ወይም የእምነት አስተምህሮ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህም ምዕመናኑን በትምህርት፣ በስልጠና እና በአዲሱ የወንጌል ስርጭት መምራት እና በእንቅስቃሴው ሂደት የምእመናን አባላት ለምን መሳተፍ እንዳለባቸው እና ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ማስረዳት እንደሆነ ተናግረዋል። "የዓላማችን አንዱ አካል፥ ከታች የሚገኙ ዝምተኛ፣ ግራ የተጋቡ የሚመስሉ እና በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ላይ ጥርጣሬ ያደረባቸው ምዕመናን የኢየሱስ ክርስቶስ አደራ ተሸካሚ ለሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ድጋፍ እንዲሆኑ ማሳመን ነው" ብለዋል። 

ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴው በፍቅር መነሳሳቱ ያስታወቁት አቶ ማክሲሚያኖ፥ ዓላማቸው ብዙ ሰዎች እግዚአብሔርን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን እንዲወዱ ማድረግ እንደሆነ ተናግረው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን መውደድ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ፍቅር በተጨባጭ መንገድ የምናሳይበት እንደሆነ አስረድተዋል።    በእንቅስቃሴው ውስጥ ያለው ፍቅር በቃላት እና በተግባር የሚገለጽ መሆኑን የተናገሩት አቶ ማክሲሚያኖ፥ ሌሎችም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በየዕለቱ ፍቅርን እንዲያሰራጩ እና የተቸገሩትን እንዲደግፉ፣ ልብን እንዲማርኩ እና ነፍሳትን እንዲነኩ በመጋበዝ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር የነበራቸውን ቃለ ምልልስ ደምድመዋል።

17 June 2023, 17:29