ፈልግ

2020.05.12 speranza, croce, mani

እግዚአብሔር መሐሪ ጻድቅ እውነተኛም ነው

ነቢዮ ዳዊት እንደሚለው እግዚአብሔር መሐሪ ጻድቅ እውነተኛ ነው (መዝ. 114)፡፡ ይህ በአንድ በኩል እምነት ተስፋ በሌላ በኩል ደግሞ ጥንቃቄ ፍርሃትን ያሳድርብናል፡፡ እግዚአብሔር መሐሪ ስለሆነ እንደ ደግ ወዳጅ ደካማነታችንን አውቆ በደላችንን የተውልናል፡፡ ቅን ስለሆነ ደግሞ ወላጅ ግሣጼ ሲያስፈልገን ምን ጊዜም ወደ ኋላ አይልም፡፡ በመሆኑም ሁሉን ጥፋታችንን ዝም ብሎ አይመለከትም፡፡

የእዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ስለዚህ ምሕረት የሚያደርግበት ጊዜ አለ፤ ከዚህ ባሻገር ፍርድ የሚሰጥበትና የሚቀጣበት ጊዜ አለ፡፡ መሐሪ ብቻ ቢሆን እኛ እንዳልተቀጣ ሕፃን እንቀብጥና ተሞላቅቀን እንበላሽ ነበር፡፡ «ምንም አያደርገንም´ እያልን በኃጢአትን እናበዛ ነበር፡፡ በዚህ አኩያ ምሕረቴ ከሚጠቅመን ይልቅ ብዙ በጐዳን ነበር፡፡ ቅን ፈራጅ ብቻ ቢሆን ደግሞ ወደ ተስፋ መቁረጥ ስለሚያደርሰን ከምንቀርበውና ከምንጠጋው ይልቅ ፈርተነው ከእርሱ እንሸሽ ነበር፡፡ ምሕረቱን መስማት እንቢ ብንለው በቅን ፍርዱና በቅጣቱ ያስጠነቅቀናል፡፡ በዚህ ዓለም ምሕረቱን ያሳየናል፣ በወዲያኛው ዓለም ግን የሚያስፈራ ቅጣትን ያሳየናል፡፡ በምሕረቱ ብንቀልድ ለባልንጀራችን ይቅርታ ብንከለክለውና አውቀን በኃጢአት ላይ ብንወድቅ በክፋታችን አዝኖ ይጨክንብናል፡፡ ምሕረቱና ቅንነቱ ደግሞ ከሰው ልጅ ቅንነት ጋር ሊወዳደር አይችልም፡፡

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር በምሕረቱ በእውነተኛ ፍርድ ሲሄድ ምንም እንኳ በአእምሮ የተሻለምንና ከፍ ያለ ስጦታ የተቀዳጀን ብንሆንም በሕሊናችን ተመርተን ልንመላለስ በፍርሃት ሳይሆን በመረዳት ልንሄድ ይገባል፡፡ ከተሳሳትን ግን ባሕርያችን ብዙ አእምሮ ያለን በሕሊናችን የምንመራ ብንመስልም በውስጣችን በፍርሃት ተገደን እንጓዛለን፡፡

በሕይወታችን እንግዲህ የእግዚአብሔርን ምሕረትና እውነተኛ ፍርድ እየተመልከትን ልንሄድ ይገባናል፡፡ ከተሳሳትን በመሕረቱ ተማምነን ተጸጽተን በፍጥነት የእርሱን እውነተኛና መንገድ እንያዝ፡፡ በኃጢአት ከውደቃችን በፊት ደግሞ «በዚህ ኃጢአት እንደወደቅሁ የሞትኩ እንደሆን እንዴት እሆናለሁ; ምሕረቱን ነፍጐ ቅጣትን ቢያወርድብኝ ምን አደርጋለሁ;´ እያልን ኃጢአት ከማድረግ እንቆጠብ፤ በፈተና ወቅት እውነተኛና ቅን ፈራጅ የሆነውን እግዚአብሔርን ብናስታውስ ፈተናውን በድል በመወጣት እናሸንፋለን፡፡

05 June 2023, 11:28