ፈልግ

 ፊሊፒንስ ፥  በነጭ አሸዋ የተሸፈነው የቦራካይ ደሴት ባህር ዳርቻ ፊሊፒንስ ፥ በነጭ አሸዋ የተሸፈነው የቦራካይ ደሴት ባህር ዳርቻ  

የፊሊፒንስ ጳጳሳት ‘አልሚዎች ቦራካይ ደሴት ላይ የሚኖሩ አቲሶችን ያክብሩ’ ማለታቸው ተነገረ።

በፊሊፒንስ ያሉ የካቶሊክ ጳጳሳት በቦራካይ ደሴት የሚኖሩትን የአገሬው ነባር ተወላጆች ቡድን የሆኑትን የአቲስ ማህበረሰቦችን እንዲያከብሩ የመንግስት እና የግል አልሚዎችን ተማጽነዋል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
‘የነባር ተወላጆች የኤጲስ ቆጶሳት ኮሚሽን’ (ECIP) የተባለው የጳጳሳት ስብስብ እንደገለፀው በቦራካይ ደሴት ውስጥ የሚገኙ የፊሊፒንስ መንግስት እና የግል አልሚዎች በአካባቢው ለሚኖሩ የአቲ ጎሳ ተወላጆች የተሰጣቸውን የመሬት ባለቤትነት መብት እንዲያውቁ እና እንዲያከብሩ አሳስቧል።
እ.አ.አ. በ 2018 መንግስት ለአከባቢው ጎሳ ተወላጆች ‘የነባር ተወላጆች የኤጲስ ቆጶሳት ኮሚሽን’ በሚል ፥ ለፍትህ እና ድህነትን የመቅረፍ መርሃ ግብር አካል በሆነው አሰራር የመሬት ይዞታዎችን ሰጥቷቸው እንደነበር ይታወቃል። የካሊቦ ጳጳስ የሆኑት ጆሴ ኮራዞን ታላ-ኦክ እንዳሉት “አቲሶች የእነዚህ የመሬት ይዞታዎች ህጋዊ ባለቤቶች መሆናቸውን እናረጋግጣለን” ብለዋል።
የአቲ ህዝብ በግብርናው ላይ በተካሄደው ሪፎርም ተጠቃሚ ቢሆኑም ፥ ‘መሬቶቹ ለግብርና የማይመቹ ናቸው’ በሚል ሰበብ መሬታቸውን የማጣት አደጋ ተጋርጦባቸዋል። ኤጲስ ቆጶስ ታላ ኦክ ለግብርና ሪፎርም ዲፓርትመንት እንዳስታወቁት የአገሬው ተወላጅ ቡድን መሬቱን በማልማት ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ እንዳዋለው አበክረው ተናግረዋል።
ጳጳሱ እንደሚሉት ከሆነ “በርካታ የአቲ ማህበረሰብ አባላት የተሰጣቸውን መሬት እያረሱ ፣ የእርሻ ሰብሎችን በማምረት ላይ ይገኛሉ” ብለዋል። በማከልም “የቦራኬ አቲስ ማህበረሰቦች ለፍትህ እያለቀሱ ነው ፥ እኛም ከእነሱ ጋር ቆመናል” ብለዋል።
በነጭ አሸዋ የተሸፈነችው የባህር ዳርቻዋ እና በተፈጥሮ ውበቷ የምትታወቀው ቦራካይ ደሴት በፊሊፒንስ ታዋቂ የቱሪስት መዳረሻ ናት።
የቱሪዝም ልማት መስፋፋት እና እየተሰሩ ባሉ ፈጣን ግንባታዎች ምክንያት የደሴቲቱ የመጀመሪያ ነባር ነዋሪዎች ለነበሩት ለአቲ ጎሳዎች ተግዳሮቶችን ፈጥረዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአቲ ህዝቦች ከላይ በተገለፀው ምክንያት የመሬት እጦት ስላጋጠሟቸው ወይም መሬት አልባ ስለሆኑ የአያት ቅድመ አያቶቻቸውን አከባቢ ለቀው መውጣት ጀምረዋል። መፈናቀላቸውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የፊሊፒንስ መንግሥት በግሪጎሳዊያኑ አቆጣጠር በ2018 ከጠቅላላው የደሴቲቱ ስፋት 1 በመቶውን የሚሸፍነውን 3.2 ሄክታር መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። ሆኖም እነዚህ የመሬት ይዞታዎች አሁን ላይ በአዳዲስ የግንባታ ፕሮጀክቶች ምክንያት ክርክር ዉስጥ ገብተዋል።
 

09 June 2023, 14:16