ፈልግ

ወንድም ጋሌ ኮንዲት፣ የላሳላዊያን ክርስቲያን ወንድም ወንድም ጋሌ ኮንዲት፣ የላሳላዊያን ክርስቲያን ወንድም 

የላሳላዊያን ክርስቲያን ወንድም ቴክኖሎጂዎችን ለበጎ ነገር መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገለጹ።

ለ60 ዓመታት የላሳላዊያን ክርስቲያን ወንድም ሆነው ያገለገሉት ጋሌ ኮንዲት ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂውን ለበጎ ዓላማ የመጠቀም አስፈላጊነትን በመግለጽ ፥ ሰዎች በትምህርት ፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እና ቤተክርስቲያን በምትሰጠው አገልግሎቶች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
እ.አ.አ. ከ 1961 ጀምሮ የክርስቲያን ወንድም የሆኑት ጋሌ ኮንዲት የሊቀ ጳጳስ ሩሜል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፕሬዝዳንት ፣ የክርስቲያን ወንድሞች ትምህርት ቤት የወንድሞች ማህበረሰብ ዳይሬክተር እንዲሁም የቀድሞ የዴ ላ ሳሌ ኒው ኦርሊንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል። ስለ ጥሪያቸውም ሲናገሩ “እግዚአብሔር እየጠራኝ እንደነበር አምን ነበር ፥ ከዚያም ከክርስቲያን ወንድሞች ጋር ተገናኘሁ ፥ እነሱም ጋር የማህበረሰብ አገልግሎትን አስፈላጊነት እና ድሆችን የመርዳት መንገዶችን ተገነዘብኩ” በማለት ለቫቲካን ዜና ተናግረዋል።
ብዙ ወጣቶችን በማስተማር ያሳለፏቸውን ዓመታት በማስታወስ “ሁለቱንም ማለትም ወንድ እና ሴት ልጆችን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተምሬያለሁ እናም ሁሉንም እንደረዳኋቸው ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል። በመቀጠልም “አሁን ዕድሜዬ 80 ዓመት ነው ፥ ነገር ግን 80 ዓመት እንደሆንኩ አይሰማኝም ፥ ለዚህም እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስበው የተሳተፍኩባቸውን ነገሮች ሁሉ አስባለሁ ፥ በዚህም ደስተኛ ነኝ” ብለዋል።
የላሳላዊያን ክርስቲያን ወንድም መሆን ሰዎችን ማገልገል እንደሆነ ተናግረው ምክንያቱንም ሲገልፁ “ብዙ ሰዎችን መርዳት እንደ ክርስቲያን ወንድም የምታደርገው ነው። አንተ ለራስህ ብቻ ሳይሆን ለሰዎችም መኖር አለብህ ፥ በድክመታቸው እየጠነከሩ እንዲሄዱ እና እንዲማሩ ትረዳቸዋለህ” በማለት ገልጸዋል።


ቴክኖሎጂ በዓለም ውስጥ


ወንድም ኮንዲት ክርስቲያን ወንድሞች የቴክኖሎጂን ትክክለኛ አጠቃቀም ለሰዎች እንዲያስገነዝቡ እና ሰዎችን ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ማሳሰብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
“ወንድሞች ቢበዙ ብዬ እመኛለሁ ፥ ግን አሁን ያሉት ወንድሞች ጥቂት ናቸው ፥ እያወራን ያለነው አሜሪካ ውስጥ ሆነን ነው ፥ የምንኖረውም በጣም ዓለማዊ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ነው ፥ አሁን ስለምናወራው ቴክኖሎጂ ከዬት እንደመጣም ታውቃላችሁ እናም እዚህ ያሉ ብዙ ሰዎች እኔ እግዚያብሄር አያስፈልገኝም ብለው ያስባሉ” ብለው አሁን ስላሉበት ማህበረሰብም ሁኔታ ገልጸዋል።
“በዚህ ዓለም ውስጥ ስንመላለስ ለራሳችን ብቻ አይደለንም ፥ እኔ በምሰራው እና በምናገረው ነገር እንደምጸና ላሳያቸው እሞክራለሁ። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ስለዚያ ነገር ለማሰብ ትንሽ ጊዜ ይወስዳሉ ፥ በተለይ ዛሬ ሁሉም ነገር ኦንላይን በሆነበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው” ብለው ስለወቅቱም ተናግረዋል።
የክርስቲያን ወንድም የሆነው ኮንዲት ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ተናግሯል። “አሁን ያለንበት ዓለም እንደበፊቱ አይደለም ፥ ሁሉም ሰው በእጁ ስልክ አለው ፥ ሁሉም ነገር አዲስ ነው ፥ ለሰዎች ይህ መሆኑ መጥፎ እንዳልሆነ ነገር ግን ቴክኖሎጂዉን ስንጠቀም በአግባቡ መሆን እንዳለበት መንገር አለብን ፥ እንደዛ ካልሆነ እግዚያብሄርን ታጣለህ ፥ እሱ ሁል ጊዜ ከጎንህ ነው ነገር ግን እሱን መምረጥ አለብህ ሲሉ አሳስበዋል። አክለውም “አሁን የምንኖረው በተለየ ዓለም ውስጥ ነው። ይህ ሁሉ ቴክኖሎጂ በሕይወታችን ላይ እያደረገ ያለው እና በሕይወታችን ውስጥ የምንኖረው እንዴት እንደሆነ ዓለምን የሚረዱ ወንድሞች እንዲኖሩን የበለጠ ምክንያት ይሆናል። ቴክኖሎጂን በመጥፎ የአጠቃቀም ዘይቤ መጠቀማችን የቤተሰባችንን የአንድነት ህይወት እየቀየረ ለከፍተኛ ብቸኝነት ፣ ድብርት እንዲሁም ብዙ ወጣቶች የማህበራዊ ድረ-ገጾችን በብዛት እየተጠቀሙ ስለሆነ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ገልጸው ፥ በመሆኑም ሰዎች ትክክለኛ የደስታ ምንጭ ከዚህ እንዳልሆነ ለሰዎች እንዲያስገነዝቡ ብዙ ወንድሞችን የምንፈልግበት ትልቁ ምክንንያት ይሆናል” ብለዋል።
ሰዎች ቴክኖሎጂን እንዳይጠቀሙ ማገድ እንደማይፈልጉ ነገር ግን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት መርዳት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ይህን ሲያብራሩ “ነገር ግን ለእነርሱ እንደዛ ሊሰማቸው ቢችልም ፥ እኔ እንዳይጠቀሙበት እየነገርኳቸው ሳይሆን እንዴት እንደሚጠቀሙበት እና ምን ማድረግ እንደሌለባቸው ብሎም ለምን መጠቀም እንዳለባቸው እንዲገነዘቡ እየረዳኋቸው ነው” ብለዋል።
ወንድም ኮንዲት በተጨማሪም ‘እግዚአብሔር እንድታደርጉ የሚፈልገውን ማወቅ’ እንደሚያስፈልግም ገልጸው ፥ ለአንተም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ጥሩ ባልሆኑ ነገሮች ውስጥ እየገባህ ነፍስህ ዋጋ አታሳጣት ፥ ለብቃት ፣ ለመፍጠን እና ለስኬት ብቻ አትኑር። ከዚህ የበለጠ ሕይወት አለና” ብለዋል።


የእግዚአብሔርን ጥሪ ማወቅ


እንደ ላሳላዊያን ክርስቲያን ወንድም ሆነው ባሳለፉት የ60 ዓመታት አገልግሎት አንፃር ወንድም ኮንዲት አንድ ነገር ተረድቻለሁ ይላሉ ፥ ይህንንም ሲገልጹ “ትክክለኛ ውሳኔ እንድናደርግ የሚረዳን አምላክ ከእኛ ጋር ይገናኛል” ብለዋል። “ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ከባድ የሆነውን ነገር ግን ትክክለኛውን ነገር እንድታደርግ ይጠይቅሃል ፥ ይህም ለጥሩ ምክንያት ነው። ምናልባት አንድ ቀን እግዚያብሄር ለምን እንዳደረገው እና አንድን ሰው እንዴት እንደረዳሀው ታውቅ ይሆናል” ብለዋል።
ወንድም ኮንዲት የእሳቸው ጥሪ በማህበረሰቡ ውስጥ ሰዎችን ለማገልገል እና ድሆችን ለመርዳት እንደሆነም ገልጸዋል።
“ጥሪዬ ከእኔ ጋር በጣም ጠንካራ ነው ፥ የማህበረሰብ አገልግሎትን አስፈላጊነት እና ተማሪዎችን የምታግዝበት መንገድ ድሆችን የምትረዳበት መንገድ ውስጥ እንደሚካተት ተገንዝቤያለሁ” ብለው በመቀጠልም ፥ “በምስጋና ቀን ሰዎችን ለመርዳት እና ተማሪዎቼ ድሆችን እንዲመግቡልኝ በማድረግ እጠቀማለሁ። ያጠናሁት ማህበራዊ ሳይንስ ነው በዛም ዲግሪ አለኝ። እኔ ከልጆች ጋር ወደ ማህበረሰቡ ውስጥ በመግባት እንዴት መርዳት እንደሚችሉ አሳያቸዋለሁ ምክንያቱም ብዙዎቹ ምን መደረግ እንዳለበት እንኳን በትክክል አያውቁም። አረጋውያንን እንዴት መርዳት እንደሚችሉም ለልጆቹ ልምዴን አጋራቸዋለው። አብዛኛዎቹ ተረጂዎች በ1930ቹ ተወላጅ ስለሆኑ ልጆቹን 1930ቹን ልብሶች ለብሰው እንዲመጡ በመጋበዝ ፥ ተማሪዎቹ አረጋዊያኑን አሪፍ የሆኑ ካፍቴሪያ ይወስዷቸዋል እዛም አብረው ጥሩ የሆነ ጊዜ ያሳልፋሉ” በማለት ልምዳቸውን አጋርተዋል።
ወንድም ኮንዲት እንደሚሉት “ስለ አረጋውያን ማወቅ እና መጥተው ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉ በመጋበዝ ዉስጥ ይህ የማህበረሰብ አገልግሎት ጥሩ ምሳሌ ነው ፥ ብዙ አረጋውያን ብቻቸውን ናቸው ፥ አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቦቻቸው አይመጡም ፥ ስለዚህም እዚህ ይጋበዙና ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉ እናረጋለን” ብለዋል።
ተማሪዎችም አረጋውያንን መፃፍ እንዲችሉ እንደሚያግዟቸው እና ጸሎትም አብረው እንደሚጸልዩ ተናግረዋል።


የክርስቲያን ወንድሞች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ


ወንድም ኮንዲት በኅብረተሰቡ ውስጥ ብዙ ወንድሞች እንደሚያስፈልጉ አጽንዖት ሰጥተው ይናገራሉ።
“የእኛ ማህበረሰብ ብዙ ወንድሞችን ይፈልጋል። ካቶሊኮችም ሆኑ ካቶሊኮች ያልሆኑ ሰዎች ወንድሞችን ይፈልጋሉ ፥ እነዚህ ሁሉ ሰዎች አምላክ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማወቅ እንዲችሉ እንዲረዷቸው ወንድሞችን ይፈልጋሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ክርስቲያን ወንድሞች ከ340 ለሚበልጡ ዓመታት ሲያገለግሉ እንደነበር ገልጸው “ይህ እጅግ ብዙ ዓመት ነው ፥ ነገር ግን ወጣቶችን ትክክለኛ እሴቶች እንዲያስተምሩ እና ትክክለኛ ተምሳሌት ሆነው እንዲያነሳሱ እንዲሁም ልንረዳቸው የምንችለውን ሁሉ በማድረግ ከእነሱ ጋር በመሆን ግንኙነቶችን እንዲያዳብሩ እና ጥሩ ሰዎች እንዲሆኑ አሁንም ብዙ ወንዶች ያስፈልጉናል። ብዙዎቹ ትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ እንደ ዋና አስተዳዳሪ ብዙ ወንድሞች ዬሉንም ፥ ምክንያቱም እኛ እነዚህን ነገሮች ማድረግ የማይችሉ ጥቂት ወንድሞችና አረጋዊያን ወንድሞች ብቻ ነው ያሉን ፥ ስለዚህ ወንዶች እንፈልጋለን ፥ ብዙ ቢኖረን እመኛለሁ” በማለት አሁን ላይ እያጋጠመ ያልውን የወንድሞች እጥረት ገልጸዋል።
“ቤተክርስቲያኒቷ ብዙ ወንድሞችን እንደሚያስፈልጓት ይታወቃል ነገር ግን እንደ ላሳላዊያን ክርስቲያን ወንድም ለመሆን የሚቀላቀሉት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለቤተክርስቲያኑ ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል” በማለትም ሃሳባቸውን አካፍለዋል።
“ይህ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሲከሰት የመጀመሪያው አይደለም ፥ ከዚህ በፊት ነበር ፥ ተመልሶም ሊመጣ ይችላል ይላሉ። እነሱን ሳላገኛቸው በፊት እና ከወጣቶች ጋር ብዙ የማስተማር እና የመስራት እድል እንዳለኝ ሳይነግሩኝ በፊት ስለ ክርስቲያን ወንድሞች አላውቅም ነበር። ለዚህም ቅዱስ ዮሐንስ ባፕቲስት ዴ ላ ሳሌ እና ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ለእኔ ጥሩ ምሳሌዎች ነበሩ” ብለዋል።
“ብዙ ወንድሞች እንደሚያስፈልጉ ምንም ጥርጥር የለውም። ምንም ጥያቄ የለውም” በማለት አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። የላሳሊያው ክርስቲያን ወንድም ‘የወንድማማች ማኅበር አባል’ መሆንህ ብዙ መልካም ነገሮችን እንድታደርግ እድሎችን ይፈጥርልሃል” ብለዋል።
ወንድም ኮንዲት ሰዎችን እንዴት ተልዕኮውን እንዲቀላቀሉ እንደሚጋብዙም ሲናገሩ ፥ “መጀመሪያ እንዲመጡ እጋብዛቸዋለሁ ፣ከዚያም በመሃከላችን ጥሩ ግንኙነትን እገነባለሁ ፥ ከበራሪ ወረቀትም በላይ ነው ፥ ጥሩ በራሪ ወረቀት ሊሆን ይችላል ነገር ግን ወንድሞችን ፊት ለፊት ከመገናኘት ጋር አንድ አይነት አይደለም። በግሌ ይህ ትልቅ ልዩነት አለው” በማለት አክለውም “የትም ብሄድ ስለጸሎትን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥቼ እናገራለሁ ፥ ወንድም የመሆንን አስፈላጊነት በመጥቀስ ፥ ወደ አምላክ መቅረብ እንዳለብንም እናገራለሁ” ብለዋል።

እምነት እና ተግባር

ወንድም ኮንዲት በአኗኗራቸው የካቶሊክ እምነትን የህይወት ዘይቤ ለማካተት እንደሚሞክሩም አጋርተዋል። ይህንንም ሲገልፁ “ለሰዎች በምሳሌ ለማሳየት እሞክራለሁ ምክንያቱም ተግባር ከቃላት በላይ ይናገራልና” ሲሉ ያብራራሉ።
የጸሎትን እና በእግዚአብሔር መታመንን አስፈላጊነትንም ገልጸዋል።
“አንዳንዶች ‘ይህን በራሴ ማድረግ እችላለሁ’ ይላሉ ፥ ግን አይችሉም። እግዚአብሔር ያስፈልግሃል። ወደ እግዚአብሔርም ቤት እሄድና ‘ቃላቶችህ የምከተለውን መንገድ እንዳውቅ ብርሃን ይሁኑልኝ’ እላለሁ። ዛሬ ራሴን እንዲህ ስል አገኘሁት ‘ጌታን ታምኛለሁ ፥ አንተን ማመን እፈልጋለሁ ፥ እንዳምንህ እርዳኝ’ እላለሁ” ብለው በማከልም “ይህ አስፈላጊ ነው ምክንያቱም የካቶሊክ እምነት የእግዚአብሔር ቃል ነው” ብለዋል።
አሁን የ80 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ናቸው። እንዲህም አሉ “እድሜህ እየገፋ ሲሄድ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ አትችልም። ፍጥነት መቀነስ አለብህ ፥ ነገር ግን ምንም ሳላደርግ የህይወት ዘመኔን መጨረስ ስለማልፈልግ አሁንም ነገሮችን ማድረግ እችላለሁ” ብለዋል።
ከወጣቶች ጋር የመገናኘት እና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችን ለመፍታት አንዳንድ ተጨማሪ መንገዶችን መከተል እንደሚያስፈልግ ተስፋ ያደርጋሉ። ይህንንም እንዲህ ብለው ይናገራሉ ፥ “በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ የምክር ቤት አባል ነበርኩ ፥ በዚያን ጊዜ የአደንዛዥ ዕፅ ችግሮች ነበሩ ፥ ከዚያም በኒው ኦርሊንስ ውስጥ ሙሉ የበጋ ወቅት በአደዛዥ ዕፅ ላይ ከሚሰራው ክፍል ጋር ለመስራት ከኒው ኦርሊንስ ፖሊስ መምሪያ ፈቃድ አግኝቻለሁ ፥ ይህ በአደንዛዥ ዕፅ ችግር ውስጥ ያሉትን ልጆች እንድገነዘብ ረድቶኛል። ልጆቹን ‘እራሳቸውን ለማሻሻል ብዙ እድሎች እንዳሏቸው እና ለዚህም ብዙ ትምህርቶች እንዳሉ እነግራቸው ነበር ብለዋል።
በሰብአዊ መብት እና ፅንስ ማቋረጥ ላይ ያላቸውን አቋም በመግለጽ ሰዎች እርስ በርስ መተሳሰብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
“በሰብአዊ መብት በኩል ሰዎች ተገቢ ፍትህ ሊሰጣቸው ይገባል እላለሁ። ያ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው ፥ ይህን ስል ደግሞ ስለ ፅንስ ማስወረድ እያልኩ አይደለም። ለእንደነዚህ ያሉ ልዩ ጉዳዮች ድምፄን አሰማለሁ። ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው አስፈላጊ ነው” ብለው በመቀጠልም “በጣም የሚበረታታ ጉዳይ አይደለም ፥ እግዚአብሔርን እንፈልጋለን። ሰዎች ከሚፈልጓቸው ሰዎች ይልቅ ለራሳቸው የሚያስቡ ሲሆኑ አይቻለሁ” ብለዋል።
ቃለ ምልልሱን ሲያጠቃልሉትም ሁሉም ሰው “በእውነታው ላይ እንዲሳተፍ እና ሰዎች እውነታውን እንዲረዱ በመርዳት እና ሰዎች ስለ እነዚያ ጉዳዮች እንዲያስቡ እንዲሁም ስለ ጉዳዩ አንድ ነገር በጥሩ መንገድ ብቻ እንዲሰሩ እመክራለሁ” በማለት አጥብቀው አስገንዝበዋል።
 

15 June 2023, 15:54