ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ ዊሊያም ሎሪ ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒን እና ዶ/ር ናታሻ ጎቬካርን ታሪካዊ መኖሪያው ቤታቸውን ሲያስጎበኙ። ሊቀ ጳጳስ ዊሊያም ሎሪ ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒን እና ዶ/ር ናታሻ ጎቬካርን ታሪካዊ መኖሪያው ቤታቸውን ሲያስጎበኙ። 

ሊቀ ጳጳስ ሎሪ ፡- ‘የካቶሊክ ሚዲያ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የግንኙነት መረብ ሊያጠናክር ይችላል’

የካቶሊክ ሚዲያ ኮንፈረንስ በአሜሪካ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት የባልቲሞር ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ዊልያም ሎሪ እንደተናገሩት የካቶሊክ ጋዜጠኞች የጸሎት ምንጭን እንደ ስንቅ በመያዝ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም በህዝቡ መሃል ያለውን ክፍተት ለመሙላት እንደ አገናኝ ድልድይ ሆነው እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 2 2015 ዓ.ም. ለሚካሄደው ዓመታዊ የካቶሊክ ሚዲያ ኮንፈረንስ በመቶዎች የሚቆጠሩ የካቶሊክ ሚዲያ ባለሙያዎች በዚህ ሳምንት በአሜሪካ የባልቲሞር ከተማ ተሰብስበዋል።
ከተለያዩ የአሜሪካ አህጉረ ስብከት እና የካቶሊክ ሚዲያዎች የተውጣጡ ጋዜጠኞች ፣ አዘጋጆች እና የማህበራዊ ሚዲያ ስራ አስኪያጆች እርስ በእርስ ለመማማር እና ልምዳቸውን ለመካፈል ይፈልጋሉ።
የዚህን ዓመት ዝግጅት በሃገረ ስብከታችው ያስተናገዱት የባልቲሞር ሊቀ ጳጳስ ዊልያም ሎሪ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፥ ለካቶሊኮች ኮሚዩኒኬሽን ሠራተኞች ያላቸውን ተስፋ እና ምክር አጋርተዋል።


ከክርስቶስ ጋር በመነጋገር ለዘመናችን ብርሃንን መስጠት


የባልቲሞር ሊቀ ጳጳስ እንደገለፁት በዓለማችን እየጨመረ የመጣውን የግለኝነት ባህሪ እና የመከፋፈል አዝማሚያ ለመቀነስ የካቶሊክ የመገናኛ ብዙሃን እየሰሩት ያለውን ጠቃሚ ተልዕኮ እንደሚደግፉ ገልፀዋል።
“የካቶሊክ የመገናኛ ብዙሃን ከሁሉ በላይ ወንጌል የሚሰበክበት ፣ የምሥራቹን የምንካፈልበት ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን እውነት ፣ ጥሩነት እና በጎነት የምናስተላልፍበት መንገድ ነው” ብለዋል። በተመሳሳይ መልኩ ፥ የካቶሊክ ሚዲያ ባለሙያዎች በዘመናችን ሰዎች እና ክስተቶች ላይ ብርሃን የማፈንጥቅ እና ሰዎች የዘመኑን ምልክቶች በወንጌል ብርሃን እንዲያነቡ የመርዳት ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።


ጸሎት ሥራችንን ሊመራ ይገባል።


ሊቀ ጳጳስ ሎሪ አሁን ካሉበት የባልቲሞር ሃግረስብከት መሪነት በተጨማሪ ፥ የተለያዩ የሚዲያ ኤጀንሲዎችን ጨምሮ ለብዙ የካቶሊክ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት የሚታወቀው ‘የኮሎምበስ ናይትስ’ የበላይ ኃላፊ ሆኖውም እያገለገሉ ይገኛሉ።
ሊቀ ጳጳሱ ለካቶሊክ ሚዲያ ባለሙያዎች ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ነገሮች እንዴት ማደራጀት እንደሚችሉ ምክር ሰጥተዋል ፥ “የእያንዳንዳችን ቀዳሚ ጉዳይ በመጀመሪያ ከጌታ ጋር መነጋገር እና ጌታን ያለማቋረጥ በመንፈስ ቅዱስ እንዲሞላን መጠየቅ ነው ፥ ስለዚህም የክርስቶስን ማንነትን እና ምሥራቹን ከእኛ ጋር ልናቆየው እንችላለን ፥ ያኔ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን በእውነት በእኛ ውስጥ ያበራል” ብለዋል።


በጋራ መከባበር ውስጥ የግንኙነት ድልድዮችን መገንባት


ግንኙነቶችን መገንባት ሌላው የሚዲያ ባለሙያዎች ሥራ ጠቃሚ ነገር ነው። የካቶሊክ ዘጋቢዎችን ከዓለማዊ ሚዲያዎች እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩም ጥሪ አቅርበዉላቸዋል ፥ ነገር ግን ይህ በካቶሊክ እና ዓለማዊ ሚዲያዎች መካከል ያለው መስተጋብር አንዳንድ ጊዜ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችልም ያምናሉ።
“ይሁን እንጂ” ይላሉ ሊቀ ጳጳስ ሎሪ “ምንም እንኳን የምንሰጠው ፍቅር እና ክብር ከሌላኛው ወገን ምላሽ ባያገኝም እነዚህን ድልድዮች ለመገንባት የምናረገውን ጥረት በተደጋጋሚ መቀጠል አስፈላጊ ይመስለኛል” በማለት ሃሳባቸውን አጠናቀዋል።
 

09 June 2023, 10:55