ፈልግ

በፊሊፒንስ መዲና ማኒላ በሚገኝ አንድ ቁምስና ወጣቶች ከመሪ ካኅን ጋር በሲኖዶሳዊነት ሂደት ላይ በፊሊፒንስ መዲና ማኒላ በሚገኝ አንድ ቁምስና ወጣቶች ከመሪ ካኅን ጋር በሲኖዶሳዊነት ሂደት ላይ  (PymQuiapo)

ሲኖዶሳዊነት ወጣቶችን ወደ እግዚአብሔር በመምራት እርሱን እንዲሰሙት እንደሚያደርግ ተገለጸ

በፊሊፒንስ የካቶሊካዊ ቁምስና መሪ ካኅን አባ ቫልዴዝ፣ ወጣቶች ኢየሱስ ክርስቶስን ለማዳመጥ እና ከእርሱ ጋር የመግባባት አስፈላጊነትን ለመገንዘብ በቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ተልዕኮ ውስጥ እንዲሳተፉ ጥሪ በማቅረብ፣ ሲኖዶሳዊነት ወጣቶችን ወደ እግዚአብሔር በመምራት እርሱን እንዲሰሙት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በፊሊፒንስ መዲና ማኒላ ውስጥ በሚገኝ አንድ ቁምስና የወጣቶች መሪ ካኅን የሆኑት አባ ኤርል ቫልዴዝ ዋና አገልግሎታቸው ወጣቶች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲገናኙ ማስተማር እንደሆነ ገልጸዋል። እንደ ካህን አገልግሎታቸው እና ቀዳሚ ሥራቸው ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያውቁ ማስተማር እንደሆነ ገልጸው፣ በቀዳሚነት የክህነት አገልግሎትን እንደ ስጦታ እንደሚመለከቱት ገልጸዋል። እግዚአብሔር ለካህናት በሚሰጣቸው የአገልግሎት ስጦታ አማካይነት ራሱን ለሌሎች እንደሚገልጽ አባ ቫልዴዝ ተናግረዋል።

አባ ቫልዴዝ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት የክኅነት የጸጋ ስጦታ እና በሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ያላቸው አመለካከት ወጣቶችን ለማካተት እና ለማስተማር ያነሳሳቸው መሆኑን ገልጸው፣ ጥሪያቸውም ወጣቶቻችን ማነጽ እንደሆነ፣ የክርስቶስን ትምህርት ከማስተማር እና የቤተ ክርስቲያን የጋራ አምልኮ እና ተግባራት በተጨማሪ ሁለንተናዊ መታነጽን ማምጣት እንደሆነ ተናግረዋል።

ሲኖዶሳዊነት የአንድነት ምንነት እና የወጣቶች ተሳትፎ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን ጠቀሜታ እንደሚያሳይ የገለጹት አባ ቫልዴዝ፣ ሲኖዶሳዊነት የዕለት ተዕለት ኑሮአችን በባህሪው ሲኖዶሳዊ እና አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት የምናስተምረው ብቻ ሳይሆን፣  ከትምህርተ ክርስቶስ ጋር እና ከማነጽ ሥራ ጋር በተጨባጭ የተገናኘ ስለሆነ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ቁምስናዎች ወጣቶች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር በየእሁዱ በመገናኘት መጽሐፍ ቅዱስን በማካፈል እና በመዝሙር አገልግሎት ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ በማስተማር እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

ቁምስናዎች ወጣቶችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲሆኑ ከማነሳሳት በተጨማሪ ሁለገብ ዕውቀትን እንደሚሰጡ ተናግረዋል። ወጣቶች የመሪነት ግዴታዎችን እንዲያውቁ እና የአመራር ሥራዎችን በመመካከር፣ በመደማመጥ እና በመምራት እንዲለማመዱት፣ እንደ ካኅን እና የወጣቶች አስተባባሪ እንደመሆናቸው፣ ቁምስናዎች ለወጣቶች ሕይወት አወንታዊ አስተዋፅዖን ለማድረግ የበለጠ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። አባ ቫልዴዝ በማከልም በቁምስና ደረጃ ብዙ ሥራዎችን እንደሚሠሩ ገልጸው፣ “ከወጣቶች ጋር መነጋገር፣ ወጣቶችን ማዳመጥ፣ ከየት እንደሚመጡ መረዳት ያስፈልጋል" ብሏል።

የማዳመጥ ሃላፊነት

ወጣቶች እርስ በርሳቸው እንዲደማመጡ የመርዳት አስፈላጊነት የተናገሩት አባ ቫልዴዝ፣ “ከሲኖዶሳዊነት አንፃር እነዚያን አስቸጋሪ የመደማመጥ ሂደቶችን ለመሻገር መዘጋጀት እንደሚገባ ገልጸው፣ ማዳመጥ በዝምታ ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው ትክክለኛ የሆኑ እርምጃዎችን እንዲወስድ እና የሚያስፈልጋቸውን ትክክለኛ ሃሳቦችን እንዲቀበል የማዘጋጀት ግዴታን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። “ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊት ናት ስንል የሕይወት አካሄዳችንን መግለጻችን ይመስለኛል” በማለት የቤተ ክርስቲያንን ወሳኝ ሚና አብራርተዋል። እንደ የወጣቶች አገልግሎት አስተባባሪ፣ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ወጣቶችን በማሳተፍ እና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲቀርቡ መርዳትን እንደምትቀጥልበት፣ በወጣቶች መካከል የበለጠ መስተጋብር እንዲኖር እንደምታደርግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ወጣቶች ከመሪ ካኅናቸው ጋር በሲኖዶሳዊነት ሂደት ስብሰባ ላይ
ወጣቶች ከመሪ ካኅናቸው ጋር በሲኖዶሳዊነት ሂደት ስብሰባ ላይ

ከኢየሱስ ጋር መኖር

በፊሊፒንስ የሚኖሩ ወጣቶች በእግዚብሔር ላይ ያላቸውን እምነት እንደሚገነዘቡት የተናገሩት አባ ቫልዴዝ፣ የፊሊፒንስ ወጣቶች የእምነታቸውን እሴት ማየት እንደሚችሉ ተናግረዋል። ሲኖዶሳዊ ጉዞን የተቀላቀሉት እና የሚቀላቀሉት ወጣቶች የቤተ ክርስቲያን አካል መሆን ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን እንደሚቆዩ ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ፣ በቤተ ክርስቲያን የሲኖዶሳዊነት ጉዞ ሁሉም ሰው የበኩሉን እንዲወጣ በማበረታታት፣ በጥረታቸው የተሻለ ሕይወትን ለመሞከር እና ለመገንባት ደረጃ በደርጃ መራመድ እንደሚቻል አባ ቫልዴዝ ተናግረው፣ ሲኖዶሳዊነት በማንነታችን ላይ የተሻለ ዕይታ እንዲኖረን የሚያደርግ መሆኑን በማስረዳት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አጠናቀዋል።

23 May 2023, 16:35