ፈልግ

ሰው ክብሩን አላወቀም ሰው ክብሩን አላወቀም 

ሰው ክብሩን አላወቀም

እስቲ የፍጥረታችንን ማዕረግ እስብ፤ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው ከመላእክት ጥቂት አሳንሶ ከግዑዙ ፍጥረቶች ግን ከፍ አድርጐ በመልኩ ፈጠረው። መንፈሳዊና ሥጋዊ ሀብቶችን አደለው። ከእርሱ በታች ሆኖ ምድራዊ ፍጥረት ሁሉ እንዲገዛለት አደረገ፣ በምድር እርሱን አገልግሎ በሰማይ ከእርሱ ጋር ለዘለዓለም እንዲነግሥ ወሰነ። ግን ሰው በጥጋቡ ይህን የሚያስቀና ፍጥረቱን አበላሸው «ሰው ክቡር መሆኑን አላወቀም አእምሮውም ፍጥረቶችን መሰለ እንደ እንስሳ ሆነ፣ ሰው የሥን ፍጥረት እንደሆነ አልተረዳውም፣ በገዛ ፈቃዱ ራሱን አዋረደ፣ ባርያ ሆነ፣ ሊገዙት የማይገባቸው ጌቶች ሆነው ገዙት ቀጠቀጡት።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ሰውስ ሀብታም ፍጥረት መሆኑ አልታወቀውም፣ በፈቃዱ ራሱን አደኸየ፣ ሥጋውን አስራበ፣ ነፍሱን አስጠማ፣ ሰው ብርሃን ለብሶ ሳለ ራቁቱን ወጣ፣ ከተከለከለ ዛፍ ፍሬ ቀንጥሶ በላ፣ ዓመጸኛ እጅን ዘርግቶ በድፍረት የፈጣሪውን ትዕዛዝ አፈረሰ´።

«ጌታ ሆይ አንተ ስለ ሰው ምንድነው ያላደረግኸው፣ ሕይወትንና ሞትን አሳየኸው እርሱ ግን በገዛ ፈቃዱ ሕይወትን ትቶ ሞትን መረጠ። ይህ ደግሞ «ጊዜያዊ ሞት አይደለም ዘለዓለማዊ ሞት ነው» ይላል ቅዱስ አትናቴዎስ። ሰውስ ክቡር እንደሆነ አልታወቀውም። ይህ አሳዛኝ ውድቀት በቀድሞ ወላጆቻችን በአዳምና በሔዋን የተጀመረ አሁን በእኛ እየቀጠለና እየባሰ በመሄድ ላይ ነው። እኛም በጊዜ ልዑል ማዕረግ ጥለን ወደ እንስሳት ኑሮ እንወርዳለን፤ ነፍሳችንን ስናበላሽ ፈጣሪያችንን ስናሳዝን አንገኛለን። ክብራችንን የሚያስረሳን ግርማ ሞገሳችንንና ሀብታችንን የሚገፈን ኃጢአት ነው። ኃጢአት ስናደርግ ከክቡር ማዕረጋችን ወደ ታች ዝቅ ብለን ወደ ሰይጣን ክፉ ባርነት እንወድቃለን።

ኃጢአት ማድረግ ማለት የፈጣሪህን ተቃራኒ ሥራ መሥራት ማለት ነው። ኃጢአት የመንፈስ ስንፍናን ያሳያል። ኅጢአት በነፍስና በሥጋ ያዋርደናል፣ ያሰቃየና፣ በፈጣሪና በፍጡር ፊት ቸልተኞች እንድንሆን ይገፋፋናል። ኃጢአት ስናደርግ ከብርሃን ወደ ጨለማ ከሀብት ወደ ድኸነት፣ ከነጻነት ወደ ባርነት፣ ከደስታ ወደ ሐዘን እንሸጋገራለን፣ በመከበር ፈንታ የውርደት ተሸካሚዋች እንሆናለን፣ ኑሮአችን በጣም ይከፋል። ኃጢአት እንስሳት የሚያስመስለን ብቻ አይደለም፣ ከእነርሱም የባሰ ዝቅ ያደርገናል። ምክንያቱም እነርሱ በተፈጥሮአቸው ምን እንደሆኑና ምን እንደሚያደርጉ አያውቁም፣ እኛ ሁሉን አጣርተን እያወቅን ክፉውን ሥራ በማድረግ አምላካችንና ነፍሰችንን እንበድላለን። በዚህም ክብራችንን እንጥላለን፣ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት እንሆናለን፣ ከዚህ ይሰውረን እግዚብሔር የሰጠንን ልዑል ማዕረግ እንጠብቅ እርሱ የሰጠንን ሀብትና ሽልማት አጣርተን እንወቀው፣ አክብረን እንያዘው፣ ክቡር ፍጥረታችንን የሚያበላሸው ኃጢአት በመሆኑ ከእርሱ እንጠንቀቅ እንራቅ።

 

05 May 2023, 16:12