ፈልግ

2023.04.22 Partecipanti all'Assemblea Plenaria del Dicastero per i Laici, la Famiglia e la Vita

ደስታና ውበት በቤተሰብ ውስጥ

በጋብቻ ውስጥ፣ ደስታና ፍቅር ይዳብራሉ። ፍላጎት ሲበዛ ባሮች ያደርገናል፣ ሌሎች ፍላጎቶችን እንዳንለማመድ ይከለክለናል። በሌላ በኩል፣ ደስታ ፍላጎታችንን እንዲጨምር ያደርጋል፣ በአንዳንድ የሕይወት ጊዜያት አካላዊ ፍላጎት በሚረግብበት ወቅት እንኳ፣ በብዙ ነገሮች እንድንረካ ይረዳናል። ቅዱስ ቶማስ አኩናስ ‹‹ደስታ›› የሚለው ቃል የልብን ስፋት እንደሚያመለክት ይናገራል።የጋብቻ ደስታን በኀዘን ውስጥ እንኳ መለማመድ ይቻላል። ይህ የጋብቻ ደስታ ትዳርን የደስታና የትግል፣ የውጥረትና የዕረፍት፣ የሥቃይና የእፎይታ፣ የእርካታና የምኞት፣ የቁጣና የደስታ የማይቀር ድብልቅ ብቻ ሳይሆን፣ ሁልጊዜ ጥንዶችን እርስ በርስ እንዲተሳሰቡና ‹‹እንዲረዳዱ እንዲሁም አንዱ ሌላውን እንዲያገለግል›› በሚያደርግ የወዳጅነት ጎዳና የሚጓዝ ነው።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የወዳጅነት ፍቅር የሌላ ሰውን ‹‹ታላቅ ዋጋ›› ሲያስብና ሲያከብር ‹‹በጎ አድራጎት›› ተብሎ ይጠራል። ከአካላዊና ስነ ልቦናዊ መስብህነት የሚለየው ይህ ውበት፣ ያ ‹‹ታላቅ ዋጋ››፣ ለራሳችን ሳንሰስት የሰውን ክቡርነት እንድንቀበል ያደርገናል። በፍጆታ ባህል ላይ በተመሠረተ ህብረተ ሰብ ውስጥ የውበት ስሜት ጠፍቶአል፣ ደስታም ደብዝዞአል። በዚያ ሁሉም ነገር፣ ሰዎች ጭምር፣ እንደ ሸቀጥ ይሸመታል፣ በንብረትነት ይያዛል ወይም ለፍጆታ ይውላል።  በአንጻሩ፣ ደግነት ለራስ ብቻ ከሚል ስግብግብነት ነጻ የሆነ የፍቅር ምልክት ነው። ስለሆነም ደግነት ሰውን በታላቅ አክብሮትና ምንም ዐይነት ጉዳት እንዳናደርስበት ወይም ነጻነቱን እንዳንነካበት ተጠንቅቀን እንድንቀርበው ያደርገናል። ሌላውን ሰው መውደድ ከራሴ ፍላጎት በላይ የሆነውን የሌላ ሰውን ውስጣዊ ውበትና ክቡርነት በማሰላሰልና በማድነቅ መደሰትን ያካትታል። ይህም የራሴ ወገኖች ባይሆኑ እንኳ፣ ወይም አካላዊ ውበት ሳይኖራቸው ጥልቅ ባይና አናዳጅ ቢሆኑ እንኳ፣ የሰዎችን በጎ እንድሻ ያደርገኛል። ምክንያቱም     ‹‹አንድ ሰው ሌላውን ሰው የሚያስደስትበት ፍቅር የሚወሰነው አንድን ነገር በነጻነት በመስጠቱ ላይ ነው››።

የፍቅር ውበት የሚገለጸው፣ አካል ጉዳተኛ፣ አረጋዊ ወይም መልከ ጥፉ ቢሆኑም እንኳ፣ ሌሎች ሰዎችን በራሳቸው እንደ ግብ አድርጎ በሚያስብ ‹‹እይታ›› ነው። የአድናቆት እይታ ትልቅ ጠቀሜታ ስላለው፣ በእርሱ መቆጨት ብዙውን ጊዜ ያሳምማል።  ጥንዶችና ልጆች አንዳንድ  ጊዜ እይታን ለመሳብ ሲሉ ብዙ ነገሮችን ያደርጋሉ። እርስ በርስ መተያየት ስናቆም ብዙ መከፋትና ችግር ይደርሳል። ብዙውን ጊዜ በቤተሰቦች ውስጥ ከሚያጋጥሙ ስሞታዎችና ቅሬታዎች በስተ ጀርባ ያለው ይህ ነው፡-‹‹ ባሌ ፊት ለፊት አያየኝም፤ እኔ የማልታይ እመስለዋለሁ››። ‹‹እኔ ስናገርህ እባክህ እየኝ!››። ‹‹ሚስቴ እኔን ማየት አቁማለች፣ ለእርስዋ የምታዩዋት ልጆቻችን ብቻ ናቸው››። ‹‹ በቤቴ ለእኔ የሚያስብልኝ ማንም የለም፤ እንዲያውም ጨርሶ አያዩኝም፤ ያለሁም አይመስላቸውም›› ይባላል። ስለዚህ፣ ፍቅር ዐይናችንን ይገልጣል፣ ከሁሉ በላይ፣ የሰውን ታላቅ ዋጋ እንድናይ ያደርገናል።

ይህ የፍቅር ደስታ ሊዳብር ይገባል። የተፈጠርነው ለመውደድ ስለ ሆነ፣መልካም ነገሮችን ከመጋራት የበለጠ አስደሳች ነገር እንደሌለ እናውቃለን። ‹‹ስጥ፣ ውሰድ፣ ሰውነትህን ደስ አሰኛት›› (ሲራክ 14፡16)። በሕይወት ውስጥ ትልቁ ደስታ የሚመነጨው የመንግሥተ ሰማይ ተምሳሌት ይሆን ዘንድ ለሌሎች ደስታን መስጠት ስንችል ነው። ባበቴ በዓል (Babette’s feast) የተሰኘውን ደስ የሚል ፊልም ማሰብ እንችላለን፤ ወጥበተኛዋ ለጋስ እቅፍና ምሥጋና ከተቀበለች በኋላ "ወይ ጉድ እንዴት መላእክትን ማስደሰት ትችላለህ!″ ያለችውን ማሰብ ይቻላል። ለሌሎች ደስታን ማስገኘትና እነርሱንም ሲደሰቱ ማየት ትልቅ ደስታና መጽናናትን ይሰጣል።  የወንድማማችነት ፍሬ የሆነው ይህ ደስታ ከንቱና ራስን ማእከል ያደረገ ሳይሆን፣ በሚወዱት ሰው በጎ የሚደሰቱ፣ ለእነርሱም በነጻነት የሚሰጡና መልካም ፍሬ የሚያፈሩ ፍቅረኛሞች የሚሰማቸው ደስታ ነው።

በሌላ በኩል፣ ፍቅር የሚያድገው በሥቃይና በኀዘን ውሰጥ ጭምር ነው። ቅዱስ አጉስጢኖስ እንደተናገረው፣ ‹‹ በውጊያ ውስጥ   የአደጋ ስጋት ሲጨምር ድል የማድረግ ደስታም ይጨምራል››። የትዳር አጋሮች ከጋራ ሥቃይና ትግል በኋላ ሥቃዩንና መከራውን መቀበሉ ተገቢ መሆኑን ይረዳሉ፣ ምክንያቱም አንድ መልካም ነገር አግኝተዋል፣ እንደ ጥንድ አንድ ነገር ተምረዋል፣ ወይም ያላቸውን ለማድነቅ በቅተዋል። እርስ በርስ የሚዋደዱና ከታላቅ የጋራ ጥረት በኋላ አንዳች ውጤት ያገኙ ሁለት ሰዎች የሚሰማቸውን ጥልቅና አጓጊ ደስታ የሚያህሉ የሰው ልጅ ደስታዎች ጥቂት ናቸው።

03 May 2023, 11:30