ፈልግ

እስማኤል የቤት እንስሳትን ሲንከባከብ እስማኤል የቤት እንስሳትን ሲንከባከብ  ታሪክ

“ስለ ፍጥረታት ጉዳት በመመስከር የግል ሕይወትን መለወጥ”

የዚህ ታሪክ ዋና ተዋናይ እስማኤል የተባለ ወጣት ነው። በስፔን ካታሎኒያ ክፍለ ሀገር የሚኖር ካቶሊካዊ የማኅበረሰብ አንቂ ነው። በአካባቢው ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች እና እንስሳት መጠለያን በማዘጋጀት እንደ አሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ የድህነት ሕይወት ለመኖር የቆረጠ ወጣት ነው። በኋላ ከሁለት ዓመታት በፊት ተለይቶት ወደቆየው እምነቱ ተመልሶ ለፍጥረታት በሙሉ እንክብካቤን ለማድረግ ወስኗል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እንደ አሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ዘመን በግ እና ተኩላ በአንድነት በሚሰማሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ መኖር ምን ሊመስለን ይችላል? እስማኤል ስፔን ውስጥ ከጋያ ቤተ መቅደስ ፋውንዴሽን ጋር ግንኙነትን በመፍጠር በአካባቢው የደረሰውን የስነ ምሕዳር መመናመን በቅርብ ከተመለከተ በኋላ በተለይም ከእርሻዎች፣ ከመኖሪያ ቤቶች እና ከምግብ ኢንዱስትሪዎች የሚገኙ ተረፈ ምርቶችን በመሰብሰብ፣ መኖን በማጣት የተጎሳቆሉ የቤት ውስጥ እንስሳትን እህዮችን፣ ፈረሶችን፣ ላሞችን፣ ፍየሎችን፣ ዓሳማዎችን እና የዶሮ ጫጩቶችን ለመመገብ እና ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ ወሰነ። ይህን ሁሉ እያደረገ ሳለ ድንገት አንዱ ቢሞትበት፣ ምንም ቢሆን ነፍስ ነውና በተከበረ ቦታ መሞቱን ያረጋግጣል።

የፋውንዴሽኑን ኢስታግራም የተሰኘ ማኅበራዊ ሚዲያን ከሚከታተሉ 300,000 ደንበኞች መካከል 94,000 የሚደርሱት የእስማኤል ደንበኞች ናቸው። እነዚህ ደንበኞች በማኅበራዊ ሚዲያው አካይነት ስለ ፋውንዲሽኑ እና እስማኤል ስለሚንከባከባቸው እንስሳት በየጊዜው በቂ መረጃን ያገኛሉ። እስማኤል ከዚህም በተጨማሪ ስለ ሥራው የሚናገሩ እና ለሦስተኛ ጊዜ ለሕትመት የበቁ ሁለት መጽሐፍትን ጽፏል። “ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ ችግሮች እና መሰናክሎች በርካቶች ናቸው” የሚለው እስማኤል፣ አገልግሎቱ እንዳይቋረጥበት የሚረዱ ክፍያዎችን መሸፈን፣ የቦታ ጥበት እና የዕርዳታ እጆችን ፈልጎ ማግኘት ከባድ ቢሆንም “እግዚአብሔር በፍፁም አይተወኝም! ለዚህም ነው ይህ ሥራ የእግዚአብሔር ነው የምለው” በማለት ተናግሯል። 

ወደ እምነቱ መመለስ

እስማኤል በእምነቱ ጠንካራ አልነበረም። ከአንድ ዓመት በፊት ወደ እግዚአብሔር ቤት መመለሱን የሚናገረው እስማኤል፣ በአሥራ አራት ዕድሜው በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በመታቀፍ  የክርስትና ሕይወትን እየተለማመደ ከቆየ በኋላ ሰዎች በሚሠሩት ኃጢአት ምክንያት ተደናቅፎ ማቋረጡን ተናግሯል። በሃያ ዓመት ዕድሜው ከቤተ ክርስቲያን ፍጹም ርቆ ከቆየ በኋላ ራሴን ከሌሎች የተሻልኩ አለመሆኔን ተገነዘብኩ ይላል። በወንድሜ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ የምመለከት፣ በራሴ ላይ ያለውን ግንድ የማላስተውል ሰው ነበርኩ ይላል።

እስማኤል ይህን ተገንዝቦ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዲመለስ ያደረጉት በአካባቢው የሚመለከታቸው እንስሳት ናቸው። “ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ወደ አፍሪካ ለመሄድ ወሰንኩ። እዚያ እያለሁ አንድ ዝሆን ጭንቅላቱን በግንባሬ ላይ ባደረገ ጊዜ ወደ ልቤ አንድ ቃል መጣ፤ 'ፍቅር!' የሚል። ይህ ቃል በጣም ኃይለኛ እና በተግባር ለማዋል እጅግ አስቸጋሪ ነው። “ ‘ባልንጀራህን ውደድ!’ ፣ ‘የማታውቀው እንግዳ ሰውን ውደድ!’ ፣ ‘ጠላትህን ውደድ!’ ፣ ‘ሁሉንም ውደድ!’ ፣ ‘ሕይወትህን እንኳ ቢሆን አሳልፈህ ለመስጠት ወደኋላ አትበል!’ የሚለውን ከ 20 ዓመታት በፊት ሰምቼ ነበር። ነገር ግን ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነ መገመት ይቻላል። ከአፍሪካ ከተመልስኩ በኋላ በውስጤ ሙሉ በሙሉ እንደተለወጥኩ ተሰማኝ። በዙሪያዬ ባሉ ነገሮች ሁሉ፣ በምድር እና በውስጧ በሚኖሩት ፍጥረታት ሁሉ ውስጥ እግዚአብሔርን ማየት ጀመርኩ” በማለት ተናግሯል።

“ውዳሴ ላንተ ይሁን!” የሚለው ቃለ ምዕዳን ያመጣው ተጽዕኖ

እስማኤል በሕይወቱ ለውጥን ካመጣ በኋላ ወደ ተለመደው ተግባራቱ፣ ወደ ሥራው እና የዕለት ተዕለት የኑሮ ትርምስ ውስጥ መመለስ ነበረበት። አመለካከቱ እና ልቡ በጥልቅ ተለውጠዋል። “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችኮስ ቃለ ምዕዳን በአጋጣሚ እንዳነበበ የሚናገረው እስማኤል፣ ጽሑፋቸው ወደ እግዚአብሔር እንዲቀርብ ማድረጉን ገልጿል። የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ንቅናቄ አባላትን እንዳገኛቸው እና ምድራችንን፣ እንስሳትን፣ ድሆችን እና ስነ-ምህዳርን በመንከባከብ ረገድ ምን ያህል ጠንክረው እንደሚሠሩ ማየቱን አክሎ ተናግሯል። ይህን ከተመለከተ በኋላ የመጨረሻውን እርምጃ ለመውሰድ እና ኢየሱስ ክርስቶስን እንደገና ለመከተል መወሰኑን ገልጾ፣ እምነት ዕለታዊ ተግባሩን የሚመራ መሆኑን እንደሚያምን፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ለሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ምስጋናቸውን የሚያቀርቡ፣ ለማንበብም ከፍተኛ ምኞት ያደረባቸው እና ለመደገፍም የወሰኑ በርካታ አማኝ ያልሆኑ ጓደኞች እንዳሉት ተናግሯል።

የካቶሊክ እምነት ተከታይ በመሆኑ ምክንያት የሚዘባበቱት እና ጥቃትን የሚሰነዝሩ አንዳንድ ማኅበራዊ አውታረ መረቦች መኖራቸውን የገለጸው እስማኤል፣ ሆኖም ግን በእርሱ ምሳሌነት ሌሎች ሰዎችም የጋራ መኖሪያ ምድርን በመንከባከብ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ማነሳሳቱን እና የመቁጠሪያ ጸሎት ማድረስ ሲጀምር አማኝ ያልሆኑትም በጸሎቱ እንደሚሳተፉ ገልጿል። ፍቅርን በሚጋራባቸው በእነዚያ ጊዜያት ብዙዎች እንደ ቤተ ክርስቲያን ተሰምቷቸው ወደ ልቦናቸው መመለሳቸውን አስረድቷል። “ፍጥረታቱ በሆኑ እንስሳት አማካይነት ክርስቲያናዊ ሕይወትን መምራት እንዳለብን እግዚአብሔር ያስተምረናል” ያለው እስማኤል፣ "እግዚአብሔር በሚናገርበት ቦታ ዝም ማለትን መማር፤ ምክንያቱም እርሱ በአቅመ ደካሞች እና ዝቅተኞች አማካይነት አንዳንዴም በእንስሳት በኩል ይናገረናል” ብሏል።

የአሲሲው ቅዱስ ፍራንሲስን የሚመስል የአኗኗር ዘይቤ

“ውዳሴ ላንተ ይሁን!” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በጥልቅ መማረኩን እና ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፍተኛ ፍቅር እንዳለው የገለጸው እስማኤል፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ችግሮች በበዙበት በዚህ ዘመን ውስጥ ቤተ ክርስቲያን እና መላው ዓለም የሚፈልጓቸው ተወዳጅ ጳጳስ ናቸው” ብሏል። የአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከፍጥረታት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንደነበረው እና ፍቅርም እንዳለው እስማኤል አስታውሶ፣ እንደ ቅዱስ ፍራንችኮስ ሁሉ እስማኤልም “እግዚአብሔር በእኛና በተፈጥሮ መካከል አዲስ ቃል ኪዳን እንድንሠራ ክርስቲያኖችን እየጠየቀ እንዳለ እርግጠኛ ነኝ። ከባድ ሥራ ቢጠብቀንም በዓለማችን ውስጥ ለውጥን ለማምጣት እና በቤተ ክርስቲያንም የመታደስ ጊዜን ስለተሰጠን ደስተኛ ነኝ” ብሏል።

በዩክሬን ውስጥ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ወደዚያች የምሥራቃዊ አውሮፓ አገር በመሄድ ስደተኞችን ለመርዳት እና እንስሳትን ለመንከባከብ እስማኤል ጥሪ ተሰምቶታል። የዕርዳታ እጆቻቸውን የዘረጉ ሰዎችን በሙሉ የሚያመሰግነው እስማኤል፣ በዩክሬን ከጦርነት ቀጠና ወጣ ብለው በሚገኙ ሆቴሎች ውስጥ ማረፊያ አግኝተው ለተቀመቱ ተፈናቃዮች በየሳምንቱ ዕርዳታን መላክ እንደቻለ፣ 200 መቶ የሚደርሱ ዩክሬናውያንን ወደ ስፔን እንዲመጡ ማድረግ መቻሉን እና በጦርነቱ ምክንያት ጠባቂ ላጡ 250 የቤት ውስጥ እንስሳት እንክብካቤን ማድረግ መቻሉን ገልጿል። እስማኤል በመጨረሻም የዕርዳታ ጥሪውን የሰሙት በሙሉ የድጋፋቸውን መጠን ሳይመለከቱ ለፍጥረታቱ ካላቸው ፍቅር የተነሳ ፈጣን እርምጃን እንዲወስዱ በማሳሰብ ለውጥ ፈላጊ እንዲሆኑም አደራ ብሏል።   

10 May 2023, 16:39