የህንድ ግዛት በሆነችው ማኒፑር በተከሰተ የሃይማኖት ግጭት ምክንያት በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ስደት አሳስቦኛል አሉ የህንድ ሊቀ ጳጳስ
የዚህ ዜና አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ - አዲስ አበባ
የባንጋሎር የሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳስ አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ ፥ በማኒፑር ግዛት ውስጥ ብጥብጥ ከተነሳ በኋላ ክርስቲያኖችን ኢላማ ያደረገው ሃይማኖታዊ ጥቃት እና ስደት አሳሳቢ እንደሆነ አውስቷል።
ሊቀ ጳጳስ ፒተር ማቻዶ እንዳሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ትንኮሳ እያገረሸ መምጣቱን ነው አትኩሮት ሰጥተው የተናገሩት።
"እ.አ.አ. በ1974 የተገነቡ ሶስት አብያተ ክርስቲያናት እና አንዳንድ መኖሪያ ቤቶች እንደተቃጠሉ ፥ እንደዚሁም ህዝቡ ወደ ተሻለ ሠላም ያለበት ቦታዎች ለመሰደድ እንደተገደዱ ሪፖርቶች ደርሰውናል" ብለዋል።
በተጨማሪም ከ12 በላይ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውን ፣ በብዙዎቹም ላይ እርኩሰት እንደደረሰባቸው እና እንዲሁም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የኢየሱሳውያን ማህበር ካህናት ላይ ማስፈራሪያ እና ዛቻ እንደደረሰባቸው የሚገልጹ ዘገባዎችም ወጥተዋል።
ሊቀ ጳጳሱ አክለውም “ይህ የሚያሳየው በሃይማኖታዊ አመለካከት እና ልማዳቸው ኢላማ በሚደረግባቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰውን አደጋ አሳሳቢ መሆኑን ነው” ብለዋል።
"ሁኔታው በቁጥጥር ስር እንደሚውል ተስፋ እናደርጋለን ለዚህም አበክረን እንጸልያለን ፥ ለማኒፑር ህዝብም ሠላም እና በራስ መተማመን ይመለሳል" ብለዋል።
ሊቀ ጳጳሱ እንዳሉት የሃይማኖት ነፃነትን ማረጋገጥ የመንግስት ሃላፊነት እንደሆነ እና ፥ በተለይ ደግሞ ህዝቡ በስልጣን ላይ ላለው ፓርቲ አደራ መስጠቱን ጠቁመዋል።
የማኒፑሩ ግጭት
በማኒፑር ውስጥ ያለው ብጥብጥ የተነሳው እሮብ እለት በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ሲሆን ይህም በአብዛኛው ሂንዱዎችን እና ሙስሊሞችን ባቀፈው የሜቴይ ጎሳ ማህበረሰብ እና ባብዛኛው ክርስቲያን በሆኑ ናጋ ጎሳ መካከል ውጥረቱ እየጨመረ በመምጣቱ ነው።
በሁከቱ መሃል ወደ 9,000 የሚጠጉ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ፥ ነገር ግን በትክክል የጠፋው የሰው ህይወት ቁጥር እና የንብረት ውድመት እስካሁን አልተገለጸም።
የጠቡ ምንጭ የተባለዉም ባለፈው የሜይቲ ጎሳዎች ከስራ እና ከመሬት መብቶች አንፃር የተወሰኑ ጥቅማጥቅሞችን የሚያረጋግጥላቸው እና እውቅና እንዲሰጠው ያቀረቡትን ጥያቄ በመቃወም ነው የሜይቲ ጎሳ ያልሆኑት ቡድኖች ብጥብጡን ያስነሱት ተብሏል።
በማኒፑር ውስጥ ከ50% በላይ ህዝብ የሜይቲ ጎሳ አባል እንደሆነም ተዘግቧል።