ፈልግ

የሚያዝያ 29/2015 ዓ.ም. ዘትንሣኤ 4ኛ እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል እና አስተንትኖ የሚያዝያ 29/2015 ዓ.ም. ዘትንሣኤ 4ኛ እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል እና አስተንትኖ   (©paul - stock.adobe.com)

የሚያዝያ 29/2015 ዓ.ም. ዘትንሣኤ 4ኛ እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል እና አስተንትኖ

የዕለቱ ምንባባት፦

1.    ቆላ 3፥3-17

2.   1ኛ ጴጥ 3፥15-22

3.   ሐዋ 11፥1-18

4.   ሉቃ 24፥33-44

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

በዚያኑም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በዚያ በአንድነት ተሰብስበው አገኟቸው፤ “እነርሱም ጌታ በርግጥ ተነሥቷል! ለስምዖንም ታይቷል” ይባባሉ ነበር። ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርት ተገለጠ

ይህን እየተነጋገሩ ሳሉ፣ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሀት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለምን ትጨነቃላችሁ? ለምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ይገባል? እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ እኔው ራሴ ነኝ። ደግሞም ንኩኝና እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና ዐጥንት የለውምና።”

ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። 41እነርሱም ከመደሰትና ከመገረም የተነሣ ገና ሳያምኑ፣ “በዚያ ቦታ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቍራሽ ሰጡት፤ 43እርሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ። እርሱም፣ “ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፣ ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል’ ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” አላቸው (ሉቃስ 24፡33-44)።

የእለቱ አስተንትኖ

 

 

“እነርሱም ጌታ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል”

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ደንብ መሰረት የትንሣኤ አራተኛ ሰንበት እናከብራለን። በዚህም ዕለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ንባባት አማካኝነት ይገናኘናል፣ ያስተምረናል፣ ይገስጽናል፥ እንዲሁም ደግሞ የእርሱን መንፈስ በእኛ ላይ በመሳደር ፍጹም ታዛዦች የእውነት ወዳጆችና መስካሪዎች ያደርገናል። ለዚህም ነው ዛሬ በመጀመሪያው ንባብ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስያስ ሰዎች ሲፅፍላቸው “ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሳቱን በማየታችንና በማመናችን ምክንያት ከሞት ወደ ሕይወት ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣን ባርነት ወደ ዘለዓለማዊ ነፃነት ተሸጋግረናል” የሚለው።

እንግዲህ “ከጨለማ ወደ ብርሃን ተሸጋግረናል” ካልን ጨለማንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ክደን ተለይተናል ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ በሌላ መልኩ ወደ ጨለማ የሚወስዱ የዚህን ዓለም ክፋትና ማብለጭለጭ ራስወዳድነትና በስሜት መመራት የሚሉትን ነገሮች ሁሉ አሽቀንጥረን ጥለናል ማለት ነው። በዚህ መልኩ ከምንምና ከሁሉ በላይ በሕይወታችን ቦታ ሊሰጠው የሚገባውን አምላክ ቦታ ሰጥተናል ክብር ሰጠተናል ማለት ነው።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ዛሬ በቆላስያስ ሰዎች በኩል አድርጎ ለሁላችን ምክሩን ይለግሳል፣ እንዲህም ይለናል “በክርስቶስ እየሱስ ባገኘነው አዲስ ሕይወት አማካኝነት አዲስ አእምሮና አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል” ይላል። ታዲያ በዚህ አዲስ አእምሮ መልካምና የተቀደሱ ሃሳቦችን ብቻ በማፍለቅ እውነትም የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ሕይወታችንን በአዲስ እንዳደሰው ፣ በአዲስ እንደቀየረው ለማረጋገጥ በየትኛውም ቦታ ምስክር ሆነን ልንቆም ይገባል።

 ሰው መንፈሳዊ አካሄዱ የተስተካከለ እንዲሆንለት ያለ አንዳች ጥርጣሬ የሕይወት ምንጭና የሕይወት መነሻ እንዲሁም መድረሻ ወደሆነው ወደ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ መቅረብና ሕብረት መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሁሉ ነገር በሙላት ከእርሱ ዘንድ ይገኛልና። ልባችንና አእምሮአችን የሚያርፈው እውነተኛ ሰላምን የሚያገኘው ብዙ ሃብትና ንብረት ስላከማቸን ሳይሆን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ላይ ማረፍ ስንችል ብቻ ነው። የእኛ የሆነ ሁሉ ከእርሱ መልካም ፈቃድ የመነጨ መሆኑን በመገንዘብ ለእርሱ መገዛት ስንችል ብቻ ነው። ሁል ጊዜ የኃጢአት ማመንጫ ቦታ ወይ ልባችን ወይ አእምሮአችን ነው። ከዛ በኋላ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ተግባራዊ እናደርገዋለን። ስለዚህ ከሁሉ አስቀድመን ልባችንና አእምሮአችን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ላይ ካሳረፍን ልባችንና አእምሮአችን የሚያሰላስሉት ፣ የሚያውጠነጥኑትና ይሚያመነጩት መልካምና የተቀደሰ ሃሳብ ብቻ ይሆናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚለን በአንዳንድ ክፉ ኃጢአቶች ሥር አዘውትረን መውደቃችን የሚያመልክተው ልባችንና አእምሮአችን ገና ሙሉ በሙሉ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ላይ አለማረፋቸውን ነው። ስለዚህ ወንጌላዊው ማርቆስ በምዕራፍ 9 ላይ እንደሚለን “የኃጢአት ምክንያት ከሚሆኑብን ሁለት እጃችንንም ሆነ እግራችንን መቁረጡ” ይሻለናል። በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከማመናችንና ሙሉ እኛነታችንን በእርሱ ላይ ከማሳረፋችን በፊት በመንፈሳዊ ሕይወታችን የሞትን ነበርን፣ በዚህም ምክንያት ከኃጢአት ጋር የተሳሰርን ነበረን፣ አሁን ግን በጸጋው አማካኝነት ሕያዋን ስላደረገን አዲስ መንፈሳዊ ልብስን ስላለበሰን አዲስ ሕይወት ስለሰጠን ለኃጢአት ሁሉ በመሞት ከእርሱ ጋር አዲስና ዘለዓለማዊ የሆነ ጉዞ ጀምረናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ “አዲስ ልብስ ለብሰናል” ብሎ ሲናገር የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች የሆኑትን ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትህትናን፣ ገርነትን፣ ትዕግሥን እና የመሳሰሉትን ሁሉ ይዘን አዲስ ጉዞ ጀምረናል ማለቱ ነው። ይህንንም የምናደርገው በኤፌሶን 1፥4 ላይ አንደሚናገረው “በእግዚአብሔር ፊት ቅዱሳንና ነውር የሌለብን ሆነን በፍቅር መመላለስ እንችል ዘንድ” ነው። ሌሎች ይቅር እንዲሉን እንደምንፈልገው ሁሉ እኛም ሌሎችን ከአፋችን ሳይሆን ከልባችን ይቅር ማለት እንችል ዘንድ ነው። እንዲሁም በማቴ 6፥14-15 እንደተገለፀው “የእግዚአብሔር ፍቅርና ምሕረትን” እናገኝ ዘንድ በይቅርታ ሕይወት እንድንለማመድ ይጋብዘናል።

ይህ ለሌሎች ከልብ ይቅርታን የማድረግ ጉዳይ በብዙ ሰዎች ዘንድ ከባድ እንደሆነ ይነገራል። ነገር ግን እግዚአብሔር ለእኛ ምን ያህል ምሕረት እንዳደረገልን ስንመለከትና የእኛን ልበ ደንዳናነት ስናስተውል በእርግጥም ገና የቅድስና ጉዞአችንን እንዳልጀመርን ያስገነዝበናል። “በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አዲስ መንፈሳዊ ልብስ ለብሼ አዲስ ጉዞ ጀምሬአለሁ” የሚል ሰው ሁል ጊዜም ለሌሎች ይቅርታ ለማድረግ ልቡ የተዘጋጀ ሰው ነው። በኤፌሶን 4፥32 ላይ እንደምናገኘው እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳለን እርሱም ለሌሎች ይቅር ለማለት ልቡ የተዘጋጀ ሰው ነው። ከዚህም በተጨማሪ ዛሬ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ የእግዚአብሔርና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ባሕሪ የሆነውን ፍቅርን እንድንለብስ አበክሮ ያሳስበናል። ምክንያቱም ፍቅር እነዚህን ነግሮች ሁሉ እንደ ገመድ አስተሳስሮ የሚይዝ ነው ይለናል። ፍቅር ባለበት ቦታ ሁሉ ሰላም አለ። ሰላም ባለበት ቦታ ሁሉ ፍቅር አለ። ስለዚህ ፍቅርን ከምንም ነገር በላይ አብልጠን ልንይዝ ይገባናል። ምክንያቱም ከክርስቶስ ጋር አንድ በመሆናችን በሁሉም ዘርፍ የእርሱ አምባሳደሮች ነን። ስለዚህ ከራሳችን ቤተሰብ ጀምሮ በምንሄድበት ቦታ ሁሉ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችን ይዘን እንድንጓዝና እንድንኖርበት ለሌሎችም እንድናስተላልፍ ያስፈልጋል።

በዚህ መልኩ እንግዲህ በቤተሰብም ውስጥ ባል ከሚስቱ ሚስት ከባሏ ባልና ሚስት ከልጆቻቸው ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር በመነጋገርና በመወያየት በመተራረምም ጭምር ይህንን የተቀበሉትን የአምባሳደርነትን አገልግሎት ተግባራዊ እንዲያደርጉት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ያሳስባል።

በዛሬ በሁለተኛ መልዕክትም ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ የልባችን ገዢ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እንጂ እኛ መሆን እንደሌለብን ይነግረናል። ምክንያቱም እኛ የዓለም ንጉሥ የሆነው የክርስቶስ አምባሳደሮች ነን ካልን በልባችን የምንይዘውና ለሌሎችም የምናስተላልፈው የእኛ የሆነውን ነገር ሳይሆን ከእርሱ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተቀበልነውን ሊሆን ይገባል። በእርግጥም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ንጹህና መልካም ሕሊና እንዲኖረን ይገባል። ምናልባትም መልካም በማድረጋችንና የክርስቶስ ተገዢ በመሆናችን ብዙ መከራ ሊደርስብን እንድሚችል ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ በመልዕክቱ ይገልፃል ነገር ግን በ1ኛ ጴጥ 2፥19-20 ላይ እንድምናገኘው “መልካም በማድረጋችን መከራ ቢደርስብን ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ብዙ ጸጋና በረከትን ያስገኝልናል”። ጌታችን እየሱስ ከርስቶስ ራሱ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌአችን ነው መልካም በማድረጉ ተሰቃየ መልካም በማድረጉ ተሰቀለ መልካም በማድረጉ ሞተ መልካም በማድረጉ ተቀበረ እግዚአብሔር አምላክ ግን ከሙታን አስነሣው በቀኙም አስቀመጠው ከሥም ሁሉ የሚበልጠውንም ሥም ሰጠው። እኛም ክርስቲያኖች ሁላችን ይህ ሞቶ በተነሣው ክርስቶስ አማካኝነት ልክ በኖህ መርከብ ተሳፍረው ከዘለዓለማዊ ጥፋት እንደዳኑት ሁሉ እንድናለን የዘለዓለማዊ ሕይወትም ትቋዳሾች እንሆናለን።

በዛሬው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 24፥33-44 ላይ ሲነበብ እንደሰማነው የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አሁንም የእርሱን ከሞት መነሣት ይጠራጠሩ ነበር እርሱ ግን ቀርቦ በምስማር የተቸነከረበትን ቁስሎቹን በጦር የተወጋ ጎኑን አሳያችው እንደውም ሙሉ በሙሉ ጥርጣሬአቸውን ለማስወገድና የሙት መንፈስ እንዳልሆነ ሊያረጋግጥላቸው የሚበላ ነገር ጠየቃቸው እነርሱም አቀረቡለት እርሱም በፊታቸው በላ በዚህ ጊዜ በእርግጥም የሙት መንፈስ እንዳልሆነ አረጋገጡ። እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነው ደቀ መዛምርቱ ጥርጣሬኣቸው ተወግዶ ውስጣቸው በተስፋ የተሞላው። ሁልጊዜም ቢሆን ውስጡ በጥርጣሬ የተሞላ ሰው በሙሉ እምነት ለመጓዝ ይቸገራል ምክንያቱም ሙሉ እምነት ባለበት ቦታ ብቻ ነው ራስን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ መስጠት የሚቻለው ራስን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ ማስገዛትም የሚቻለው። ስለዚህ እኛም ይህ የጥርጣሬ ሓሳብ ካለን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ በ 1ኛ ቆሮንጦስ ምዕራፍ 15 ላይ እንደሚለው በስተመጨረሻ ልክ እንደ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አዲስ መንፈሳዊ አካል በመልበስ በዘለዓለማዊ ሕይወት ውስጥ ተሳታፊዎች እንድንሆን ያስፈልጋል። በዚህ የዘለዓለማዊ ጥሪ ውስጥ በሙላትና በእርግጠኝነት ተሳታፊዎች እንድንሆን የዘወትር አጋዣችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ይህንን ጸጋና በረከት ታማልደን ዘወትር በእግዚአብሔርም ፊት ጠበቃ ሁናም ትቁምልን።

ምንጭ፡ የቫቲካን ራዲዮ፣ የአማርኛው ክፍል

የእዚህ ዝግጅት አቅራብ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

05 May 2023, 15:46