የፊሊፒንስ ጳጳስ፡ በፊሊፒንስ ውስጥ ያለው መሠረታዊ ደመወዝ 'ፍትሃዊ ያልሆነ' ነው አሉ።
ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
የሳን ካርሎስ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጄራርዶ አልሚናዛ የፊሊፒንስ ሠራተኞችን ሁኔታ በቁጭት ገልጸው ፥ የዋጋ ግሽበቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየቀነሰ ቢመጣም በሀገሪቱ የሸቀጦች ዋጋ ጨምሮ በነበረበት ዋጋ ቀጥሏል ሲሉ ተናግረዋል።
ጳጳሱ ማክሰኞ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በፊሊፒንስ ‘ዝቅተኛ ደመወዝ’ ብለን የምንጠራው ፍትሃዊ ደሞዝ ወይም የሚያኖር ደሞዝ ወይም ለቤተሰብ የሚሆን ደሞዝ አይደለም ብለዋል።
የፊሊፒንስ ብሄራዊ ደሞዝ እና ምርታማነት ኮሚሽን መረጃ እንደሚያሳየው በሃገሪቱ ለአንድ ሰው የሚከፈለው አማካይ ወራዊ ደሞዝ 8,902 ፔሶ ሲሆን ይህም ወደ ዩሮ ሲቀየር 145 ዩሮ መሆኑ ነው።
በአንፃሩ የፊሊፒንስ ስታትስቲክስ ባለስልጣን እ.አ.አ. በ 2021 እንደዘገበው አምስት ሰዎች ላለው የቤተሰብ አባላት መሠረታዊ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ መስፈርቶችን ለማሟላት የሚያስፈልገው አነስተኛ ወርሃዊ ገቢ 12,030 ፔሶ (196.45 ዩሮ) ነው። ይህ ማለት ግን እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በቀን በ80 ፔሶ (1.31 ዩሮ) መኖር አለበት ማለት ነው።
እየተባባሰ ያለው ችግር
የሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ ፥ ፊሊፒናውያን የደመወዛቸው ትክክለኛ ዋጋ እየቀነሰ ስለሚሄድ አንድን ነገር መክፈል በሚችሉት አቅም ለማግኘት አዳጋች ሆኖባቸዋል።
ጳጳሱ አክለውም በሀገሪቱ ውስጥ እየተከፈለ ያለው ደሞዝ ከዋጋ ጭማሪው ጋር አልተዛመዱም ብለዋል ።
“አብዛኞቹ ሠራተኞች ለድህነት ተዳርገዋል ፥ ስለዚህ ባለፉት ዓመታት የሰራተኞች ሁኔታ እንዴት ነው ብለህ ብትጠይቀኝ በእርግጥም ተባብሷል” ሲሉም አክለዋል።
ጳጳሱ በቂ ካልሆነው ዝቅተኛ ክፍያ በተጨማሪ አንዳንድ ሰራተኞች ጥቅማ ጥቅሞች እና የቆይታ ጊዜ ዋስትና እንደሌላቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ‘የቤተክርስቲያን ሰዎች የሠራተኞች ህብረት’ (CWS) ሊቀመንበር የሆኑት ጳጳስ አልሚናዛ ፥ በፊሊፒንስ የግብርና ዘርፍ ላይ የተሰማራው እና ምግብ የሚያመርተው የህብረተሰብ ክፍል ከደሃውም እጅግ የከፋ ደሃ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኤጲስ ቆጶሱ እንደተናገሩት በሀገሪቱ ውስጥ የደመወዝ ጭማሪን ለማድረግ ሃሳብ ላላቸው ሁለት የኮንግረስ ሰነዶች ማህበሩ (CWS) ድጋፉን አሳይቷል። እነዚህም የ 750 ፔሶ የዝቅተኛ ደመወዝ ላይ ጭማሪ ለማድረግ ሀሳብ ያለው ‘የቤት ሰነድ ቁጥር 7568’ የሚባለው እና ‘የሴኔት ሰነድ ቁጥር 2002’ የተባለው 150 ፔሶ ጭማሪ ለማድረግ ጥረት የሚያደርገው እንደሆነም ታውቋል።
“ለሠራተኞቹ የሚገባቸውን መስጠት አለብን ፥ ፍትህን ለመስጠት ይህ የልግስና እና የፍቅር መሰረታዊ መስፈርት ነው” ሲሉ ጳጳሱ ተናግረዋል።
የፍራቴሊ ቱቲ 'Fratelli tutti' ጽንሰ ሃሳብ በደመወዝ ላይ
ጳጳሱ በሰጡት መግለጫ ፥ ደመወዝ ‘አስፈላጊ እና ፍትሐዊ’ እንደሆነና እንዲሁም ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስተምርሆም መሠረታዊ ነገር ነው ፥ ምክንያቱም ከሰው ልጅ ክብር ጋር የተቆራኘ ነውና” ብለዋል።
“ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደገው የአናጺ ልጅ ሆኖ ነበር ፥ እሱ የአናጢው ልጅ ተብሎ ተጠርቷል ፥ ስለዚህም ለሥራ የሚሰጠውን ክብርን ያመጣው ኢየሱስ ነበር” በማለት በመንፈሳዊ ጎኑ ያለውን እምድምታ አብራርተዋል።
ጳጳሱ አክለውም “የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ ትምህርት የሠራተኞችን ክብር ማስጠበቅ ነው” ብለዋል።
ነገር ግን ኤጲስ ቆጶስ አልሚናዛ እንዳሉት በደመወዝ እና በጉልበት ሠራተኛው ላይ ያሏቸው አቋም አጠቃላይ መሠረት ያደረገው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ኢንሳይክሊካል ፍራቴሊ ቱቲ (ሁላችንም ወንድማማቾች ነን እንደማለት ነው) ላይ እንደሆነ በመግለጽ “እኛ ወንድማማቾች እና እህትማማቾች ነን ስለሆነም በቤተሰብ ውስጥ ከሆንን በቤተሰቡ ዉስጥ ያለዉን ማንኛውንም ነገር እንካፈላለን ፤ እርስ በርሳችን እንረዳዳለን ፣ እንጠብቃለን ፥ ነገር ግን ይህ በሥራ ቦታ እየሆነ አይደለም” ብለዋል።
የፊሊፒንስ ሰራተኞች እንክብካቤ እንደማይደረግላቸው እና ብዙ ጊዜ በደካማ እና ጨቋኝ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሚሰሩም አክለዋል። በመቀጠልም ኩባንያዎች ሰራተኞቻቸውን እንደ ቤተሰብ እንዲያስቡ ጥሪ አቅርበዋል ፥ ምክንያቱም ደግሞ ይላሉ ‘የጉልበት ሠራተኛ የሌለበት ኢኮኖሚ በጭራሽ አያድግም’ ሲሉ ጳጳሱ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በርካታ ቡድኖች በፊሊፒንስ የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግ ጠይቀዋል ፥ ሆኖም እ.አ.አ. ከ1986 ጀምሮ ከነበሩት ስድስት አስተዳደሮች መካከል ዝቅተኛ የደመወዝ ጭማሪ የተደረገው በቀድሞው ፕሬዝዳንት ሮድሪጎ ዱቴርቴ አስተዳደር ሲሆን ይህም ከ2016 እስከ 2022 በነበረው ዝቅተኛ ደመወዝ ላይ 16.1 በመቶ ጭማሪ ብቻ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ማርኮስ ጁኒየር ምንም አይነት የደመወዝ ጭማሪ እንዳልፈቀዱ ታውቋል።