የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ክርስቲያኖች 'በዋጋ የማይገመት' ትዉፊቶችን አቆይተውልናል ተባለ።
ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
“የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ ጠቀሜታ ያለው የማይለካ ውድ ሀብት ይዛ ትገኛለች” ሲሉ በኔዘርላንድ ውስጥ በግሮኒንገን ዩኒቨርሲቲ የቲኦሎጂ እና የሃይማኖት ጥናቶች ፋኩልቲ ውስጥ የዶክትሬት ተማሪ የሆኑት አልቤርቶ አልፍሬዶ ዊንተርበርግ ተናግረዋል።
የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ታዎድሮስ 2ኛ በቫቲካን የሚያደርጉትን ጉብኝት አስቀድሞ አቶ ዊንተርበርግ የቫቲካን ዜና ባልደረባ ከሆኑት ቶማስ ማቲካ ጋር በግብፅ የነበሩት እና አሁንም ድረስ ስላሉት ጥንታዊ ክርስቲያኖች ወግ እና ባህል ተነጋግረዋል።
“ኮፕቲኮች ከጥንት ጀምሮ ከፈርዖናዊ ግብፃውያን የዘር ሃረግ የሚመዘዝ እና ሥር መሰረታቸው የግብፅ ተወላጅ የሆኑ አናሳ ቁጥር ያላቸው ክርስቲያኖች ናቸው” ሲልም ገልጿል።
በቅዱስ ማርቆስ የተመሰረተ
የኮፕቲክ ክርስትያኖች አናሳ ቁጥር ያላቸው ሲሆኑ ከጠቅላላው የግብፅ ህዝብ ብዛት ከስምንት እስከ አስር በመቶው ይደርሳሉ ፥ አብዛኛዎቹም የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባል ናቸው ። እንደ ትውፊት ፥መነሻውን የቅዱስ ጴጥሮስ ደቀ መዝሙር በሆነው በወንጌላዊው በቅዱስ ማርቆስ የተመሰረተ የአሌክሳንደሪያው ቅድስት መንበር እምነት ነው።
አቶ ዊንተርበርግ እንደሚገልፁት ልዩ የሆነው የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምስረታ “በ451 ከተካሄደው የኬልቄዶን ጉባኤ ማግስት የተከናወነ ረጅም ሂደት ነበር” ሲሉ ያስረዳሉ። ምንም እንኳን በጉባኤው ላይ የተከሰቱት አለመግባባቶች ምክንያት ግንባር ቀደም የሆነው የክርስቶሎጂ ወይንም ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥያቄዎች ቢሆኑም ፥ አቶ ዊንተርበርግ እንደሚሉት በአሌክሳንድሪያ ቤተክርስቲያን እና በሮማ ቤተክርስቲያን መካከል ያለው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ይጠቅሳሉ።
ግብፅ ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ በእስላማዊ ኃይሎች በተወረረች ጊዜ የግብፅ ክርስቲያኖች ወይ እስልምናን እንዲቀበሉ ወይም ከባድ ግብር እንዲከፍሉ ተገደዱ። “በረጅም የኢኮኖሚ ገደቦች ፣ ህዝቡን በማዋረድ ፣ ሃይማኖታዊ ይዘት በነበረው ግድያ እና በወራሪዎቹ ገዥዎች በኮፕቲኮች ላይ በደረሰው ኃይለኛ ስደት ምክንያት የቀድሞ የክርስትና እምነት ተከታዮች ወደ አናሳነት ተቀይረዋል። ይሁን እንጂ እስከ ዛሬ ድረስ በሕይወት ተርፈዋል።
የሰማዕታት ቤተ ክርስቲያን
አቶ ዊንተርበርግ የኮፕቲክ ክርስትና ለሰፊው ቤተ ክርስቲያን ያበረከተውን አስተዋፅዖ ሲያብራሩ በመጀመሪያ ላይ የሚያስቀምጡት ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን የገዳማዊነት ተቋም መሆኗን ነው ፥ ይህም ከጥንቷ ሶርያ ጋርም የተያያዘ ነው ይላሉ። የምዕራባውያን ምንኩስናን መስራች በሆነችው በቅድስት ቤነዲክት ላይ ጠቃሚ ተጽእኖዎችን ያሳደሩትን የኮፕቲክ ቅዱሳን የሆኑትን የበረሃው አባቶች መካከል በተለይም ታላቁ ቅዱስ እንጦንዮስ እና ቅዱስ ፓኮሚየስን ማስታወስ አስፈላጊ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
አቶ ዊንተርበርግ በጥንቷ ቤተክርስቲያን በግብፃውያን ክርስቲያኖች ላይ የደረሰውንም የስደት ታሪክ አስታውሰዋል። “ከኮፕቲክ መነኮሳት እና መናኞች ታላቅ ታሪክ በተጨማሪ የሮማ ግዛት በነበረችው ግብፅ በንጉሠ ነገሥት ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በክርስቲያኖች ላይ በደረሰው እንግልት እና ስደት በጣም ከተጎዱት መካከል አንዱ ነው” ብለዋል። “በመሆኑም የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን የራሷን የቀን አቆጣጠርም በአፄ ዲዮቅልጥያኖስ ዘመነ መንግስት በ284 ዓ.ም. የጀመረች እና ራሷንም እንደ ሰማዕት ቤተክርስቲያን ትገልጻለች ብለዋል።
ክርስቲያናዊ እና ሥነ-መለኮታዊ ውይይት
በአሁኑ ጊዜ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የአሌክሳንድርያ ፓትርያርክ በሆኑት ሊቀ ጳጳስ ታዎድሮስ ዳግማዊ የሚመራ ሲሆን ፥ በስሯም ወደ አሥር ሚሊዮን የሚጠጉ ምእመናን አሏት። ከግብፅ እና ከመካከለኛው ምስራቅ በተጨማሪ ፥ በአሜሪካ ፣ በካናዳ ፣ በአውስትራሊያ ፣ በፈረንሳይ እና በጀርመን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኦርቶዶክስ ኮፕቲኮች ይገኛሉ።
ከ50 ዓመታት በፊት እ.አ.አ ግንቦት 10 ቀን 1973 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እና ጳጳስ ሺኑዳ ሳልሳዊ በቫቲካን ተገናኝተው በነበረበት ወቅት ታሪካዊ “የክርስቲያናዊ የጋራ ሰነድ” Joint Christological Declaration የተባለውን ሰነድ ፈርመዋል። መግለጫው ወይም ሰነዱ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤን ተከትሎ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ለዓመታት ሲካሄድ የቆየውን የክርስትና እና ሥነ-መለኮታዊ ውይይት ተከትሎ ነበር።