በቅድስት ሀገር ያሉ የቤተክርስቲያን መሪዎች ፍትሃዊ ሠላም እንዲሰፍን ተማጽነዋል
አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ፍልስጤማውያን የአል-ናክባ (የጥፋት አደጋ) 75ኛ ዓመትን ሲያከብሩ ፥ እ.ኤ.አ. በ1948 የእስራኤል መንግሥት እንደ ሃገር በተፈጠረበት ቀን ከትውልድ አገራቸው በግዳጅ የተባረሩበትን ቀን በማሰብ በኢየሩሳሌም የሚገኘው የሃይማኖት አባቶች እና የአብያተ ክርስቲያናት ሓላፊዎች በቅድስት ሀገር ፍትሐዊና ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን የአብያተ ክርስቲያናትን ጥሪ በድጋሚ ገልፀዋል።
መከባበር ሠላምን ለማስፈን አንዱ መንገድ ነው።
“እምነታችን የሚያስተምረን ሁላችንም እንደ ሰው ልጅ ወንድማማቾች እና እህቶች መሆናችንን እና ሠላምን ፣ መቻቻልን እና ፍትህን ለማስፈን ተባብረን መስራት እንዳለብን ነው” ሲል ሰኞ ዕለት የተለቀቀው መግለጫ አስነብቧል። መግለጫው በማከልም “ፍቅር ፣ ርህራሄ እና መከባበር በዓለም ላይ ሠላምን የምናመጣበት መንገድ መሆናቸውን ክርስትና አስተምሮናል ፥ እናም ይህ በተለይ ለተወዳጅዋ ቅድስት ሀገራችን ተግባራዊ መሆን አለበት” ይላል።
ናክባ እ.አ.አ. በ1948 ከ 700,000 በላይ ፍልስጤማውያን የተሰደዱበትን ወይም ከቤታቸው የተፈናቀሉበትን ወቅት ያስታውሳል። የእነዚህ በመካከለኛው ምስራቅ ከ 5 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱት ስደተኞች እና የዘሮቻቸው እጣ ፈንታ ፥ በመካሄድ ላይ ባለው የአረብ-እስራኤል ግጭት ውስጥ ትልቅ አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል። እስራኤልም እነዚህ ስደተኞች በጅምላ ቅድመ አያቶቻቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ሲኖሩባቸው ወደ ነበሩበት ቤቶች ወይም አከባቢዎች እንዲመለሱ የቀረበላትን ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች።
ያገረሸው የእስራኤል እና የፍልስጤም ጥቃት
በዚህ ዓመቱ ክብረ በዓል የሚከበረው ፥ ከጥር ወር ጀምሮ ከ 140 በላይ ፍልስጤማውያን እና ቢያንስ 19 እስራኤላውያን እንዲሁም የውጭ ዜጎች የሞቱበት የእስራኤል እና የፍልስጤም ብጥብጥ ዳራ ላይ ነው።
በእስራኤል ፍልስጤማዊያን በሚታሰሩበት እስር ቤት ውስጥ እስረኞቹ ባደረጉት የረሃብ አድማ ምክንያት በሞቱት ፍልስጤማዊያን ሰበብ ፥ በግንቦት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ ብጥብጡ ተባብሷል። በዚህም የተነሳ የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ (በጋዛ ሰርጥ ከሃማስ ቀጥሎ ሁለተኛው ትልቁ ታጣቂ ቡድን) እና ሌሎች ቡድኖች በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ100 በላይ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ተኩሰዋል። ይህም የሮኬት ጥቃት የተደረገው እስራኤል በሃማስ እና ኢስላሚክ ጂሃድ ኢላማዎች ላይ የፈጸመችውን ገዳይ የአየር ጥቃት ተከትሎ ነው።
እ.አ.አ. ከነሐሴ 2022 ወዲህ በእስራኤል ኃይሎች እና በፍልስጤም ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛው የተባለ ጦርነት ባለፈው ሳምንት ተካሂዷል።
የሰብአዊ መብቶች እና የዓለም አቀፍ ህጎች መከበር
የኢየሩሳሌም ፓትርያርኮች በመግለጫቸው “ሠላም የሚረጋገጠው በፍትሃዊነት የሰብአዊ መብቶች እና የዓለም አቀፍ ህጎች ሲከበሩ ብቻ ነው” ብለው “ሁሉም ሰው የተሻለ እና የበለጠ ሰብአዊነት ያለው የወደፊት ህይወት ለመገንባት በጋራ እንዲሰራም” በድጋሚ አሳስበዋል።
“ፍትህ እና ሠላም ለቀጣናው መረጋጋት እና ብልጽግና ቁልፍ ሚና አላቸው ብለን እናምናለን እናም እነዚህን መልካም ግቦች ለማሳካት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናችንን እንገልፃለን”
ለቅዱስ ቦታዎች እና ለነባራዊ ሁኔታዎች ክብር መስጠት
መግለጫው በቅርቡ በእስራኤል ጽንፈኞች በአብያተ ክርስቲያናት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እና በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን አካላዊ እና ሞራላዊ ጥቃት በተዘዋዋሪ በመጥቀስ ፥ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማህበረሰቦች የሚደረገውን ጥበቃ በመደገፍ እና ቅዱሳን ቦታዎችን እንዲሁም አሁን ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታን በመጠበቅ ረገድ የላቀ ሚና እንዲጫወት ጠይቋል።
የቤተ ክርስቲያን መሪዎቹ እግዚአብሔር ለፍልስጤም ህዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ፣ የሃገረ መንግስት ግንባታ እና የብልጽግና መብት እንዲሰጣቸው እንዲሁም በቅድስት ሀገር ውስጥ ያሉ ህዝቦች በሙሉ በሠላም ፣ በክብር እና በብልጽግና መኖር እንዲችሉ በመጸለይ ተጠናቋል።